Saturday, August 31, 2013

ሰላማዊ ሰልፉ ያለፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል- ፖሊስ

ሰላማዊ ሰልፉ ያለፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል- ፖሊስ


በሃይማኖት ሽፋን የሚደረገውን የአክራሪነት እንቅስቃሴ ለመቃወም የአዲስ አበባ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ጉባኤ ነገ ነሃሴ 26 የጠራው የሰላማዊ ሰልፍ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማድረግ መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅም የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮማንድ ፖስት አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቋል ብለዋል፡፡

ሰልፉን ለማካሄድ እውቅና ያገኘው የከተማዋ የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ጉባዔ ብቻ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ሰማያዊ ፓርቲ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት እንዳላገኘና በእለቱም ፓርቲው ሰልፉን ማካሄድ እንደማይችል ገልፀዋል፡፡

በፓርቲው ስም ሰልፍ ለማካሄድ ከተሞከረ ፖሊስ ሰልፉን እንደሚያስቆምና ህጉን ተላልፈው ሰልፉን ባካሄዱት ላይም ፖሊስ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡

ለሰላማዊ ሰልፉ ሲባልም ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ ሰልፉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ወደ መስቀል አደባባይ የሚያስገቡ መንገዶች ዝግ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

ዝግ የሚሆኑትም መንገዶች ከኡራዔል ወደ ባንቢስ እና መስቀል አደባባይ፤ ከቤተ መንግስት ወደ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን እና መስቀል አደባባይ፤ ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ ለገሃር እና መስቀል አደባባይ፤ ከቦሌ መንገድ ወደ መስቀል አደባባይ፤ ከተክለሃይማኖት ሰንጋ ተራ ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከቴዎድሮስ አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስዱት መንገዶች ናቸው፡፡

ህብረተሰቡም ይህንን ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያካሂድ እውቅና ከተሰጠው የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ጉባዔ ውጭ በእለቱ ሰልፍም ሆነ ስብሰባ እንዲያደርግ እውቅና ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ የሌለ መሆኑን ተገንዝቦ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ኮሚሽኑ ጠይቋል፡፡




ሪፖርተር፤ አበበ ባዩ


No comments: