Friday, August 30, 2013

ይኸው ‹‹ሽብርተኛው›› አንዷለም አራጌ

ይኸው ‹‹ሽብርተኛው›› አንዷለም አራጌ

ሽብርተኝነት ወይም ሽብርተኛ ማለት ምን ማለት ይሆን?የዚህን ጥያቄ አለም አቀፍ ትርጉም ለመፈለግ ከኢትዮጵያ ከወጣን የምናገኘው ምላሽ ‹‹The unlawful use or threatened use of force or violence by a person or an organized group against people or property with the intention of intimidating or coercing societies or governments, often for ideological or political reasons.››የሚል ይሆናል፡፡ይህንን ትርጉም በመያዝ ኢትዮጵያ እስር ቤት ውስጥ ሽብርተኛ ብንፈልግ የምናገኘው በሰላማዊ ትግል የቆረበውን አንዷለም አራጌን ነው፡፡የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ የሆነው አንዷለም ባለትዳርና የልጆች አባት ነው፡፡ለልጆቹ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማምጣት ካለው ጽኑ ፍላጎት በመነሳት ከደም የራቀ የፖለቲካ አቋም በማራመድ መንግስትን በሰላማዊ መንገድ ሲታገል ቆይቷል፡፡
አንዷለም በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለውም ቀበና ከሚገኘው የፓርቲው ጽ/ቤት በመውጣት ላይ እያለ ነበር፡፡ሰው እንዴት ሽጉጥ ታጥቆ ይሄዳል በማለት በአግራሞት ይጠይቅ የነበረው ሰላማዊው ታጋይ በሽብርተኝነት ተከሶና ‹‹ምስክሮች›› ቀርበውበት እድሜ ልክ ተፈርዶበት በቃሊቲ ቅጣት ቤት ተወርውሯል፡፡አንድነትን የተሻለ ፓርቲ የማድረግ ርዕይ ሰንቆ የነበረውን አንዷለምን አለም በተስማማበት የሽብርተኝነት ትርጓሜ ውስጥ ብንፈልገው ባናገኘውም የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ሽብርተኛ በማለት ፈርጆታል፡፡
አንዷለም ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ ለንባብ በበቃችው ፋክት መጽኄት ‹‹የሐምሌ ጨረቃ ››የሚል ድንቅ ጽሁፍ አስነብቦናል፡፡መቼም ኦሳማ ቢላደን ፣ታሊባኖች ፣አልቃይዳ፣አልሻባብና ሌሎች ሽብርተኛ የተባሉ ቡድኖች መልእክት ሲያስተላልፉ የመልእክታቸው ጭብጥ ምን እንደሚሆን መገመት አያስቸግርም፡፡ጅሃድ ያውጃሉ፣ስለ ግድያ ያወራሉ፣የተወሰዱ ጥቃቶችን ሃላፊነት የምንወስድ እኛ ነን ይላሉ፣በቀጣይም ሌሎች ጥቃቶችን እንደሚያደርሱ ይዝታሉ፡፡እነዚህን ንግግሮች በድርጅቶቹና በድርጅቶቹ ውስጥ ካሉ ሽብርተኞች እስኪሰለቸን ሰምተናል፡፡
በኢትዮጵያ እስር ቤት ተወረወረ ያልኩት አንዷለም ግን ‹‹ከቅጣት ቤት››ያስተላለፈው መልእክት የካቶሊኩ ፖፕ ከሚያስተላልፉት የሰላም መልእክት በላይ ሰላምን፣መቻቻልን፣ይቅርታንና መተባበርን የሚሰብክ ነው፡፡አንዷለም በሀምሌ ጨረቃ ድብዳቤው እንዲህ ይላል‹‹የአሁኖቹ ገዢዎች እንደ ቀድሞዎቹ ሁሉ የተሳሳተ የፖለቲካ ባህላችን ያበቀላቸው መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡የፖለቲካ ባህላችንና አስተሳሰባችን ካልተቀየረ እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ ሌሎች አምባገነኖችንም ማብቀሉን ይቀጥላል፡፡
በአምስት አመት ውስጥ ማዕከላዊ ሁለት ጊዜ ስታሰር ሃላፊዎች ተለዋውጠው ባገኛቸውም የሁለቱም ዋና ሃላፊዎች ቃልና ተግባር ግን ትንሽ እንኳ ልዮነት አልነበረውም፡፡በሚገርም ሁኔታ ሁለቱም እንዳገኙኝ የጠየቁኝ አንድ አይነት ጥያቄ ነበር፡፡‹‹ወንድ ከሆንክ ለምን ጫካ አትገባም? ››የሚል፡፡
ወንድነት ማለት አፈ ሙዝን በማይናወጥ የፍቅርና የወንድማማችነት መንገድ መጋፈጥ ፣ተጋፍጦም ሳይገድሉ መሞት ነው ወይስ በራሳችን ጥላ ሳይቀር እየደነበርን ንጹሃንን መግደል? የሚገርመው እኮ ለአፈ ሙዝ ፍልሚያ የጥሪ ካርድ የሚበትኑት ወገኖች የደሃ ኢትዮጵያዊያን ወንድማማቾችን ደም ለማፋሰስ እንጂ እነርሱማ ከመኪና ተደግፈው ለመውረድ ምንም የማይቀራቸው ናቸው፡፡››
ይህ ሰው የሰላምን የኖቤል ሽልማት መሸለም ሲገባው ‹‹ወንድ ከሆንክ ለምን ጫካ አትገባም ››እየተባለና እየተገፋ እንኳን እንደሌሎች ሰላማዊ ትግል የትም አያደርስም አላለም ፡፡ከዚህ ይልቅ ‹‹አሳሪዎቹን ወንድሞቼና እህቶቼ››በማለት ይጠራቸዋል፡፡እንግዲህ በኢትዮጵያ ሽብርተኛ የተባለው አንዷለም ይህ ነው

No comments: