በአንዋር መስጂድ ፖሊስ ሙስሊም ሴቶች ላይ ከፍተኛ ድብደባ ፈጸመ! ጁምአ
August 23, 2013
ድምፃችን ይሰማ
ጭንቅላታቸው የተፈነከተና ደም ይፈሳቸው የነበሩ ሴቶች ታይተዋል!
ጥቂት የማይባሉ እናቶችና እህቶች ሰላታቸውን ሳይሰግዱ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ተገደዋል!
ዛሬ የጅምአን ሰላት ለመስገድ በተገኙ እናቶች ላይ ፖሊስ ድብደባ መፈጸሙ ታወቀ፡፡ በመርካቶ አንዋር መስጂድ የዛሬውን የጁምአ ሰላት ለመፈጸም የተገኙ በርካታ እናቶችና እህቶች በፖሊስ አባላት ከፍተኛ ድብደባ ተፈጸመባቸው፡፡ እነዚሁ ለጸሎት የተሰባሰቡ እናቶች ድብደባ የተፈጸመባቸው ከመስጂዱ ግቢ ውጪ አንጥፋችሁ መስገድ አትችሉም በሚል ነው፡፡
ታላቁ አንዋር መስጂድና ሌሎችም መስጂዶች በጁምአ እለት የሚመጣውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ማስተናገድ ስለሚሳናቸውና ስለሚሞሉ ህብረተሰቡ ውጪ አንጥፎ መስገዱ ባለፉት 15 ዓመታት የተለመደና የሚታወቅ ሀቅ ቢሆንም በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ ብሄራዊ ጭቆናን እያሰፈነ ያለው መንግስት ሙስሊሞችን በሁሉም አቅጣጫ ለማጥቃት በማለም የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር በተለይም ሴቶች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ቀጥሎበታል፡፡
በዛሬው ድብደባ ጭንቅላታቸው የተፈነከተና ደም ይፈሳቸው የነበሩ ሴቶች እንደነበሩ የታወቀ ሲሆን ጥቂት የማይባሉ እናቶችና እህቶች ሰላታቸውን ሳይሰግዱ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ተገደዋል፡፡ መንግስት የሃይማኖት አክራሪነትን እታገላለሁ በሚል ስም በሙስሊሙ ላይ ብሔራዊ ጭቆና በማስፈን ላይ ይገኛል፡፡ የዚህ ጭቆና ዒላዎችም ልክ ዛሬ እንደታየው አረጋውያን እናቶችና እህቶች ሆነዋል፡፡
የእምነት ነጻነትን አክብሪያለሁ እያለ ደጋግሞ በሚዲያ የሚናገረው መንግስት በሕገ መንግስቱ የተቀመጡትን የእምነት ነጻነት መብቶች በመጣስ ሙስሊሙ ላይ ከፍተኛ በደል በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ የራሱ የእምት ተቋም እንዳይኖረው ከማድረግ አንስቶ አዲስ እምነት በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ በኃይል መጫን፣ የሙስሊሙን ማህበረሰብ መሪዎች ማሰርና ማሰቃየት፣ የመብት ጥያቄ ያነሱ ሰላማዊና ያልታጠቁ ዜጎችን መግደል፣ መስጂዶችን ማሸግ፣ ኢማሞችን ያለ ሕዝቡ ፍላጎት ከስራቸው ማፈናቀልና በራሱ ፍላጎት መንግስታዊ ኢማሞችን መተካት እና ሌሎችም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሊፈጸሙ የማይችሉ ተግባራትን መንግስት ያለ ምንም ሀፍረት ሲፈጽም ቆይቷል፡፡
አሁን ደግሞ በክልሎች ሲካሄድ እንደነበረው ሁሉ ሙስሊሙን ሕብረተሰብ ከሰላት ለማቀብና ለማሸማቀቅ ለመስገድ ወደ መስጂድ የሄዱ ሙስሊሞችን ለጸሎት በተቀመጡበት ድብደባ ሲፈጸምባቸው እየተመለከትን ነው፡፡ የዚህ አይነቱ ተግባር በኢትዮጵያ ታሪክ ቢያንስ ባለፉት 90 ዓመታት እንኳ ያልታየ ድርጊት የእምነት ነጻነት በሕገ መንግስት ደረጃ በተደነገበት በዚህ ወቅት እየተፈጸመ መሆኑ ሙስሊሙ ህብረተሰብ የመንግስትን አላማና ግብ በአንክሮ አንዲያጤነው የሚጋብዝ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በደሴ ሸዋ በር መስጂድ መስጂድ የሞላባቸው የከተማው ሙስሊሞች ውጪ አንጥፋችሁ ሰግዳቹሀል በሚል ፖሊስ ከፍተኛ ጥቃት ሰንዝሮ በርካቶችን ለእስርና አሰቃቂ ድብዳባ መዳረጉ ይታወሳል፡፡
መንግስት መሰል ሁኔታዎችን ኹከት ለመፍጠር የሚጠቀምባቸው በመሆኑ ሁኔታዎችን በትእግስት ከማሳለፍ በዘለለ ድርጊቱ ሲፈጸም ፎቶ ግራፍና ቪዲዮ ማንሳት ሊዘነጋ የማይገባ ተግባር መሆኑን ማስታወስ ያሻል፡፡
አላሁ አክበር!
No comments:
Post a Comment