የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ለኢንዱስትሪዎችና ለዜጎች ፈተና ሆኗል
-በድንገት የሚለቀቅ ኃይል ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው
‹‹የተጋነኑ ባይሆኑም ችግሮች አሉ›› የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን
የኤሌክትሪክ ኃይል እየሰጡ ከሚገኙት ግልገል ጊቤ አንድና ሁለት፣ ጣና በለስ፣ ተከዜ፣ ቆቃና መልካ ዋከና እንዲሁም ከሌሎች ማመንጫዎች አራት ሺሕ ሜጋ ዋት የሚደርስ የኤሌክትሪክ ኃይል ቢሰራጭም፣
የኃይል እጥረት ሊከሰት ቀርቶ ለጎረቤት አገር ጭምር ቢሸጥም፣ እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ በመላው አገሪቱ እየተከሰተ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ ለዜጎች ፈተና ሆኖ መቀጠሉ አሳሳቢ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መሥሪያ ቤቶች መቀመጫ ከመሆኗ አንፃር፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥ ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡ ደግሞ ከሰዓታት ወደ ቀናትና እንዲሁም ወደ ሳምንታት እየተሸጋገረ መምጣቱ የተለመደ ቢሆንም፣ በክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ አነስተኛና መለስተኛ ኢንዱስትሪዎች ግን፣ ችግሩን መቋቋም እየተሳናቸውና ሥራቸውን እስከማቆም እየደረሱ መሆኑን በተለይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ፣ በደሴ፣ በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በጂማ፣ በናዝሬት፣ በደብረ ዘይት፣ በነቀምት፣ በአሰላና ሌሎችም ከተሞች በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አምራቾች እንደገለጹት፣ በውድ ዋጋ የገዙትን ጥሬ ዕቃ ወደ ምርት ለመለወጥ በመሥራት ላይ እያሉ ድንገት ኃይል ይቋረጣል፡፡ አንዳንድ መለስተኛ ማሽኖች እየሠሩ እያሉ ኃይል ሲቋረጥ፣ የማሽኖቹ ጥርሶች እርስ በርሳቸው ተጣብቀው ይቀራሉ፡፡ እሱን ለማላቀቅ ሌላ ኃይል ከማስፈለጉም በተጨማሪ በቀላሉ የሚላቀቅ አይደለም ይላሉ፡፡ በዚህ መሀል በድንገት ኃይል ስለሚለቀቅ ተቆላልፈው የነበሩ ማሽኖች ስለሚቃጠሉ፣ የነበረውን ችግር ከነማስረጃው ይዘው በቅርባቸው ወደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዲስትሪክት ጽሕፈት ቤት ሄደው ሲያመለክቱ፣ ፎርም ተሰጥቷቸው እንዲሞሉ ከመደረጋቸው ውጪ ምንም ስለማያገኙ መጉላላት እየገጠማቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በመገናኛ ብዙኃን ሁሉም ነገር እንደተሟላና ለማንኛቸውም በከፍተኛ ኢንዱስትሪም ሆነ በአነስተኛና በመካከለኛ ኢንዱስትሪ ሥራ ላይ ለሚሰማራ ግለሰብም ሆነ ሌላ አካል በቂ የሆነ ኃይል እንደሚያቀርብ ሲናገር ቢደመጥም፣ የሚያስፈልገውን ያህል የኃይል አቅርቦት ቀርቶ፣ ኃይል ሲቋረጥ ሲደወልለት እንኳን በአግባቡ ምላሽ የሚሰጥ ሠራተኛ የሌለው መሆኑን ደንበኞቹ በምሬት ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ እንኳን ማሽን ቀርቶ የማሽን ብሎን ለመግዛት ምን ያህል ወጪ እንደሚጠይቅና በየቀኑ ያለውን ጭማሪ ኮርፖሬሽኑ በደንብ እንደሚረዳው የገለጹት ደንበኞች፣ ችግሩን አውጥቶ መናገር የሚያስከትለውን ችግር በመፍራት እንጂ፣ በስርጭት ላይ የሚሠራ ብቃት ያለው አመራርም ሆነ ሥራውን በደንብ የሚያውቀው ሠራተኛ ያለው እንደማይመስላቸው ደንበኞች ገልጸዋል፡፡
በየዲስትሪክቱ በኃላፊነት ተሹመው የተመደቡ ኃላፊዎችን ለማነጋገር በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ ወደ ቢሯቸው ሲሄዱ፣ ከዓመት ዓመት የማይቋጭ ‹‹ስብሰባ ላይ ናቸው፤ የመስክ ሥራ ላይ ናቸው፤ ወደ ክልል ሄደዋል፤ ወደ አዲስ አበባ ሄደዋል…›› የሚሉ ሰበቦችን በመደርደር የበታች ሠራተኞች ሊያገናኟቸው ስላልቻሉ፣ ሥራቸውን ሳይወዱ በግድ ለመተው ወይም የኤሌክትሪክ ኃይል የማያስፈልገው ሥራ ቀይረው ለመሥራት በማሰብ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አንዳንዶቹ የኮርፖሬሽኑ ደንበኞች እንደገለጹት፣ አሁን የሚፈልጉት የመጨረሻዎቹን የኮርፖሬሽኑን ኃላፊዎች ማለትም ዋና ሥራ አስፈጻሚውንና የቦርድ ሰብሳቢውን ማነጋገር ነው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ፣ ‹‹እውነት የእኛ ችግር ይነገራቸዋል? ወይስ በበታች ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተዳፍኖ ይቀራል?›› የሚለውን አውቀው፣ የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኃላፊዎቹ በመገናኛ ብዙኃን የሚያስተላልፉትን መግለጫና ማሳሰቢያ እንደሚያዳምጡ ሁሉ፣ የእነሱንም አንብበውና አዳምጠው ምላሽ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡
ነዋሪዎች የሚያነሱት ቅሬታ የሚያገኙት የኃይል መጠንና በድንገት ሲቋረጥ እየደረሰባቸው ያለውን የንብረት ጉዳት ሲሆን፣ በተደጋጋሚ እንደሚያወሱት ኮርፖሬሽኑ አቅም ከሌለው፣ አቅም የሚገኝበትን ጊዜ ነግሯቸው እስከዚያው ድረስ ሌላ የኃይል አማራጭ እንዲጠቀሙ እንዲያሳውቃቸው ነው፡፡
ወ/ሮ ትዕግስት ለማ የሚባሉ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪ እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ ከነዋሪዎች ጋር ድብብቆሽ ጀምሯል፡፡ ‹‹ሁሉም ነዋሪ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ቀን ቀን እንዳቅሙና የሥራ መደቡ ሲባትል በሚውልበት ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ይለቀቃል፡፡ ማታ ወደ ቤቱ ሲገባ ደግሞ ይጠፋል፡፡ ኃይል መምጣት አለመምጣቱን ለማረጋገጥ ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች ማብሪያ ማጥፊያውን በማብራት ሳያጠፉት እንደሚሄዱ፣ ሶኬቶች ተሰክተው ሳይነቀሉ ስለሚረሱ በሌሉበት ሰዓት (ቀን) ኃይል ሲለቀቅ ተቃጥለው ያገኙታል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
የተቃጠለባቸውን ፍሪጅ ወይም የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ይዘው ወደ ኮርፖሬሽኑ ሲያመሩ የተቃጠለውን ዕቃ የገዙበትን ደረሰኝ ከመጠየቃቸውም በተጨማሪ፣ ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎችን በማቅረብ አመልካቹ እንዲማረርና ደግሞ እንዳይጠይቅ እንደሚያደርጉና ምንም ዓይነት አጥጋቢ ምላሽ እንደማይገኝ ወ/ሮ ትዕግስት ገልጸዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ ትዕግስት ሁሉ ሌሎቹም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና በክልል የሚገኙ ነዋሪዎች በኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን አስረድተው፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካልና የኮርፖሬሽኑ የበላይ ኃላፊዎች የዲስትሪክት ኃላፊዎችን፣ የመስመር ላይ ሠራተኞችንና በተለይ ኃይል ሲቋረጥ ስልክ ሲደወልላቸው ስልክ የሚያነሱ ሠራተኞችን በሚመለከት ምላሽ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡ የድንገተኛ ጥገና ሠራተኞች ተብለው የሚሰማሩ ሠራተኞች ከሚያውቁት አካባቢ ውጪ አፋጣኝ ምላሽ እንደማይሰጡ የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለአስቸኳይ ጥገና በሚል ኅብረተሰቡ እንዲደውልባቸው ይፋ የተደረጉ በ011646 የሚጀምሩ ስልኮችን የሚያነሱ ሠራተኞች አሠራራቸው ሊፈተሽ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በፌዴራልና በክልል ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችና ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን በሚመለከት ስላነሷቸው ችግሮች ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የኮሙዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ፣ ‹‹የተጋነነ ባይሆንም ችግር እንዳለ እናውቃለን፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ደንበኞች እንደሚያነሱት ኮርፖሬሽኑ የአቅርቦትና የፍላጎት ክፍተት እንደሌለበት የገለጹት ኃላፊው፣ በአሁኑ ጊዜ የኃይል መቆራረጥ እየደረሰ ያለው ወቅቱ ክረምት በመሆኑና ከሚዘንበው ከፍተኛ ዝናብና ከፍተኛ ንፋስ ጋር የተገናኘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ችግሩ ተፈጥሯዊ መሆኑን ቢናገሩም፣ በኃይል ማሰራጫዎችም ላይ የአቅም ውስንነት እንዳለ አልሸሸጉም፡፡ በመሬት ውስጥና በላይ 185 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመር በመዘርጋት ኮርፖሬሽኑ አቅሙን በማሳደግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች የአቅም ማሳደግ ሥራውን ሙሉ በሙሉ አዳርሶ እንዳልጨረሰ የገለጹት ኃላፊው፣ ኃይል መጨመር የሚያስፈልጋቸው ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተጠንተው ማለቃቸውንና 19 ማሰራጫ ጣቢያዎች ተለይተው ወደ ሥራ መገባቱንም አስረድተዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በአራቱም አቅጣጫ የሥራ አስፈጻሚ ቡድኖች የሚከታተሉትና የሚደግፉት የሰው ኃይል በተሽከርካሪ ታግዞ እየሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ምስክር፣ ችግሮቹ በተለይ በለገጣፎ፣ በቃሊቲ አቃቂ፣ በጉለሌ፣ በልደታ፣ በየካ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በጎፋ፣ በባልደራስና በሌሎች አካባቢዎች እየተከሰቱ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ምሽት ላይ ኃይል የሚያንሳቸውም ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት ስለሚበዛ መሆኑ ስለታወቀም፣ የቴክኒክ ክፍሉ ዕርምጃ እንዲወስድ መታዘዙን አክለዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ውጭ በአማራ ክልል በአዘዞ፣ በወልዲያ፣ በደሴ፣ በሐይቅ፣ በመርሳና በውጫሌ አካባቢ ከሁለት ሳምንት በፊት ችግር ተከስቶ እንደነበር የጠቆሙት ኃላፊው፣ ከተሞቹ እንዳይቸገሩ ኮርፖሬሽኑ ከሌላ መስመር ኃይል እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በባህር ዳር ዙሪያ ጭልጋና ገልጂ አካባቢ ያሉ የገጠር ከተሞች ኮርፖሬሽኑ ኃይል እንዲያገኙ በማመቻቸት ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ ችግሩን ለማስወገድ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ለየብቻ በማድረግ ኃይል የማሳደግ ሥራ መሠራቱንና በአብዛኛው ችግሩ እየተፈታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ዞኖችና በክልል ያሉ ኢንዱስትሪዎች በቀጥታ ኃይል የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸና እያገኙ መሆኑን አቶ ምስክር ገልጸዋል፡፡ በዋና ሥራ አስፈጻሚው ሰብሳቢነት በየሳምንቱ ሰኞ ሰኞ የኢንዱስትሪ ዞኖችን በሚመለከት ውይይት መኖሩንና ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
‹‹ቅሬታ ለመቅረፍ ተከፋፍለን እየሠራን ነው፤›› ያሉት አቶ ምስክር፣ በመርህ ደረጃ ደንበኞች የሚያነሱት ጥያቄ ትክክል በመሆኑ በክልል 11 ሪጅኖችና በአዲስ አበባ አራት ሪጅኖች፣ ሁሉም ኃላፊዎችና እስከታች ሠራተኞች ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ስልክ አለማንሳት፣ ቅን አለመሆን፣ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣትና ሌሎችም ድርጊቶች ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ጭምር ኮሚቴው ኃላፊነት ወስዶ እየሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡ በተለይ ስልክ እያነሱ የሚዘጉ፣ በአግባቡ ደንበኞችን የማይቀበሉና ሌሎች የኮርፖሬሽኑን ስም ጥላሸት የሚቀቡ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 36 የአስቸኳይ ጥገና ቡድን ተቋቁሞ ሦስት ሙያተኞች ከአንድ ተሽከርካሪ ጋር በመመደብ እንዲሠሩ የተደረገ መሆኑንና ሌሎች የችግር መፍቻ ዘዴዎችን ለመዘርጋት እየተሠራ መሆኑን አቶ ምስክር ገልጸዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ 17 ሺሕ ሠራተኞች ሲኖሩት ከ700 በላይ የሚሆኑት አመራሮችና ኃላፊዎች በመሆናቸው፣ ያለውን ችግር ለማቃለልና ለመቀነስ ተግቶ እየሠራ መሆኑን አቶ ምስክር አስታውቀዋል፡፡
No comments:
Post a Comment