Saturday, August 31, 2013

ለመጋራት ወይስ ለመደጋገፍ?! ......!

 ለመጋራት ወይስ ለመደጋገፍ?! ......!

"ደጋፊዎች ለማግኘት ትጥራለህ" የሚል ኣስተያየት ደርሶኛል።

እንደኔ ግን ማንም ለመደገፍ ይሁን የማንም ድጋፍ ለማግኘት ኣልተነሳሁም። ጓደኞቼ ከኔጋ ተመሳሳይ የሆነ የፖለቲካ ኣመለካከት ቢያራምዱ ደስታውን ኣልችለውም፤ የራሳቸው የሆነ የተለየ ኣቋም ቢኖራቸውም ኣደንቃቸዋለሁ። 

የማልፈልገው ኣካሄድ ቢኖር (መብታቸው እንደተጠበቀ ሁኖ) በጥቅም ተደልለው (ለሆዳችው ሲሉ) ለሌሎች የፖለቲካ ተዋንያን ህሊናቸው የማይፈቅደውን የፖለቲካ ድጋፍ በመስጠት ከነፃነት (በፍቃዳችው) ባርነትን የመረጡ ሰዎች መንገድ ነው።

እኔ ኣልደግፋቹሁም፤ ሃሳባችሁ ሲመቸኝ እጋራለሁ። ከናንተ የምጠብቀውም ይህ ነው። እኔ ከሰዎች ወይ ከፓርቲዎች መርህ የሚያጣብቅ ኣቋም የለኝም። የኔ ቃል ኪዳን ከእውነት ጋር የታሰረ ነው። ስለዚ ስለደጋፊዎች ኣልጨቅም። እንደውም የኔ ምክር ማንም ሰው ማንንም መደገፍ እንደሌለበት ነው።

እኔን ማመን (ወይ ኣለማመን) የለባችሁም። ኣያስፈልግም። የሚያስፈልገው እውነተኛውን ሓሳብ መለየት ላይ ነው። ኣንድ ሃሳብ መቀበል ያለብን ከራሳችን ኣስተሳሰብ ጋር ኣብሮ እንደሚሄድና ምክንያታዊ መሆኑ ስናረጋግጥ ነው።

በሌላ ኣባባል በዚ መንገድ ከሌሎች የምንወስደው ሃስብ የለም። ምክንያቱም የተቀበልነው ሃሳብ በውስጣችን (በራሳችን ኣስተሳሰብ ውስጥ) ኣግኝተነውልና።

ስለዚ ለምንነጋገረው ይሁን ለምንተገብረው ነገር በራሳችን (በግላችን) ሃላፊነት መውሰድ መቻል ኣለብን። እያንዳንዱ ሰው የራሱን የግል ውሳኔ ሲኖረውና የብዙዎቹ ተመሳሳይ ሲሆን ውጤታማ ለውጥ ይመጣል።

ብዙ የኢትዮዽያ ዜጎች በመሪዎቻቸው መከፋፈል ተስፋ ይቆርጣሉ። "ተስፋ ቆረጡ" ማለት የያንዳንዱ ግለሰብ ሃላፊነት ለመሪዎቹ ኣሳልፎ ሰጥቶ ነበር ማለት ነው። ይህ ስሕተት ነው። የግላችን ሃላፊነት በራሳችን ትከሻ መቀመጥ ይኖርበታል።

የምንፈልገው ነፃነት ከሆነ ሃላፊነታችን ለመሪዎቻችን ኣሳልፈን መስጠት ኣይገባም። ከሰጠናቸውማ ነፃ እየወጣን ሳይሆን ኣለቆችን (ጌቶችን) እየቀየርን ነው። ስለዚ ከመሪዎች ሃሳብን (ኣቋምን) መጋራት እንጂ ደጋፊ መሆን ኣያዋጣም። መሪዎቹ ኣንድ ነገር ሲሆኑ ኣላማው በናንተ መቀጠል ይኖርበታል።

ስለዚ የምንፃፃፈው ለመደጋገፍ ሳይሆን ሃሳብን ለመጋራት ነው። ሃሳባችን ዘላቂነት እንዲኖረው በእውነት የተመሰረተ መሆን ኣለበት።

ለህሊና ነፃነት ቅድሚያ እንስጥ።

No comments: