Sunday, August 18, 2013

አገር በተቀነባበር የሐሰት ድራማ አይመራም!


አገር በተቀነባበር የሐሰት ድራማ አይመራም! 













[ከሰሞኑ የመንግስት የፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎችና አካሄዶቹን አስመልክቶ የተዘጋጀ የአቋም ማብራሪያ ጽሁፍ ከዚህ በታች በዝርዝር ቀርቧል፡፡ ጽሁፉ በድምጽ (ኦዲዮ) ተዘጋጅቶም ይለቀቃል፡፡ ሁላችንም በማንበብና ለሌሎች በማስነበብ እንዲሁም በማድመጥና ለሌሎች በማስደመጥ ሀላፊነታችንን እንወጣ፡፡] 

ፍረጃውና ውንጀላው መፍትሄ አይወልድም!
እሁድ ነሐሴ 12/2005

አገር በተቀነባበር የሐሰት ድራማ አይመራም!

የመንግስት ፍረጃና እምነትን ከእምነት የማጋጨት እንቅስቃሴ በቀጠለበት በዚህ ወቅት ሌላ አዲስ ድራማ ተቀናብሮ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቧል፡፡ ይህ ድራማ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ በርካታ የመንግስት ድራማዎች ተመሳሳይ ሐሳብ ያንጸባረቀ ቢሆንም አዳዲስ ጭብጦችንም አሳይቶናል፡፡ በዚህ ‹‹ሼህ ኑሩን ማን ገደላቸው?›› የሚል ርእስ በተሰጠው ድራማ የተንጸባረቁትን ጉዳዮች በተወሰነ መልኩ መዳሰስና ለመንግስት አካል እርምት መስጠት ተገቢ በመሆኑ የተወሰኑ ነጥቦችን እናነሳለን፡፡

የሙስሊሙ ማህበረሰብ ያነሳቸው ጥያቄያዎች እና እንቅስቃሴው የፈጠረው ስሜት መንግስት ሊቋቋመው ከሚችለው በላይ እየሆነ መምጣቱ እሙን ነው፡፡ መንግስት የተነሱለትን ሕጋዊና ሕገ መንግስታዊ ጥያቄዎች በበጎ ለማየት ከመፈለግ ይልቅ ከመጀመሪያው ወቅት ጀምሮ ሲያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች በጣም ተገቢ ያልነበሩ መሆናቸው ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ሆኖም የህብረተሰቡን ግፊትና ጫና በመመልከት መሪዎቻችንን በሚኒስቴር ደረጃ ቀርቦ ለማነጋገርና ለመደራደር የመንግስት ፈቃደኝነት መታየቱና የጥያቄዎቹን ህጋዊነትም አምኖ መቀበሉ አንድ መልካም ጅምር ተደርጎ ታይቶ ነበር፡፡

ሆኖም የመንግስት ፍላጎት የነበረው የተነሱትን ጥያቄዎች በአጉል ሽንገላ አለባብሶ ሙስሊሙን በሐይል ወደ ቤት ማስገባት ሆኖ መገኘቱ መንግስት ቀድሞውንም ችግሩን ለመፍታት ፈቃደኛ አለመሆኑን፣ እንዲሁም የችግሩ ዋነኛ ፈጣሪ መሆኑን አመላክቷል፡፡ መሪዎቻንን እንደ ሕዝብ ተወካይነታቸው ተቀብሎ በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ ሲያወያይና ሲደራደር የቆየው መንግስት እነዚያኑ ሰዎች ስም ቀይሮ ‹‹አሻባሪ›› ብሎ ለመሰየም አንድ ወር እንኳ አልፈጀበትም፡፡ የመንግስት ፍላጎት በአጉል ሽንገላ እና የፖለቲካ ብልጣብልጥነት ህዝበ ሙስሊሙን ወደ ቤቱ ማስገባት፣ ልሳኑንም መዝጋት ነበር፡፡ ይህ ግን ሊሳካ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም የመንግስት ረዣዥም እጆች ሁሉም ሙስሊም ቤትና መስጂድ መድረስ ጀምረው ነበርና፡፡ በመሆኑም ህዝቡ በአቋሙ ጸና፡፡ ‹‹እጅህን አንሳልን! አዲስ ሃይማኖት እንድንቀበልህ አታስገድደን!›› እያለ ደጋግሞ ህዝቡ ድምጹን በሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ መንግድ አሰማ፡፡ ያኔ ነው መንግስት የጭቃ ጅራፉን ደጋግሞ ማጮህ የጀመረው፡፡

መንግስት ራሱ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች የተነሱትን ጥያቄዎች ተገቢነት እንዳልገለጸ፣ የመሪዎቻችንን ሰላማዊነት እንዳላብራራ በአንዴ 180 ዲግሪ ተሽከርክሮ መሪዎቻችንን በአሻባሪነት በመፈረጅ ‹‹ጸረ ሰላም ኃይሎች፣ ጸረ ልማት፣ የመቻቻል ጸር›› ወዘተ የሚሉ አሉታዊና የፖለቲካ ትርፍ ማስገኛ ቃላትን በመጠቀም የተጠናከረ ዘመቻ ጀመረ፡፡ በባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የጀመረው ይህ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ከአንድ ዓመት በላይ ቢዘልቅም የመንግስት ትርፍ አሁንም በዜሮ እየተባዛ ነው፡፡ በቁጥር ይህ ነው የማይባሉ የሰልፍ ኢንቨስትመንቶች፣ የዜና ዘገባዎች፣ የዶኩመንተሪ ድራማዎች ቅንብር፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎችና ተዘርዝረው የማያልቁ ተግባሮች ሁሉ ማጣፊያው ያጠረው መንግስት ከዓመት ለዘለለ ጊዜ ሲያከናውናቸው የቆያቸው ተግባራት ናቸው፡፡ ሆኖም የመንግስት ትርፍ አሁንም ምንም ነው! የዚህም ዋነኛው ምክንያት የኢትዮጵያውያን ግንዛቤ መንግስት ከሚያስበው በላይ የላቀና መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ የሚያስተውልና የሚገነዘብ በመሆኑ ነው፡፡ የዚህ የተቀናጀ ዘመቻ ቀጣይ ተደርጎ የቀረበው የሰሞኑ የሼኽ ኑሩ ግድያ ላይ ያተኮረ ድራማ ያስተላለፈው መልእክትም ከቀዳሚዎቹ ብዙም የተለየ ባይሆንም በዚሁ ድራማ ላይ የተንጸባረቁ ሐሳቦች ላይ ተገቢውን ማብራሪያ መስጠቱ ግን ጠቃሚ ይመስለናል፡፡

በቀዳሚነት መንግስት አሁንም ያሉና የሚታዩ ችግሮችን መፍትሄ ከመሻትና ከመቅረፍ ችግሮቹን በመካድ ቪዲዮዎችን አቀነባብሮ ብቻ ወደ ሕዝብ በመልቀቅ ህብረተሰቡን ለማታለል ጥረት ማድረግ ምርጫው ማድረጉ እንደ አንድ የኅብረተሰብ ክፍል በጣም ያሳስበናል፡፡ ከዚህ ቀድም እንደነበሩት ሁሉ ታሳሪዎች ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት ነጻ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በመንጠቅ፣ በሕግ ጥላ ስር ያሉ ታሳሪዎችን መንግስት በሚፈልገው መልኩ በማናዘዝ የሚሻውን በሚዲያ እንዲሉለት ማድረግ መቀጠሉ የችግሩን ቁልፍ አንደማይፈታው እሙን ነው፡፡ የሕዝብ ሐብት ሊሆን የሚገባው ብሔራዊ ቴሊቪዥንና ሌሎች በመንግስት ይዞታ ስር ያሉ ሚዲያዎች በድብደባ የደከሙ ታሳሪዎች ኑዛዜዎች ቆርጦ በመቀጠልና በማቀናበር ያላቸውን ‹‹ልምድ›› በመጠቀም የሚያቀርቧቸው ፕሮግራሞች የኅብረተሰቡን ችግር ከመፍታት ይልቅ በሕዝቡ ውስጥ ቂምና እልህ እንዲበረታ እያደረገው ነው፡፡ ለካሜራ እንደሚፈለገው ‹‹ፈገግና ፈታ ብለህ አላወራህም›› እየተባለ በድብደባ የሚሰራው የምርመራ ክፍል ድራማ ሕዝብን ፈጽሞ ሊያታልል አይችልም፡፡

መንግስት ለመንፈቅ ያህል በለፋበት ‹‹ጂሐዳዊ ሐረካት›› ድራማ መታየት ማግስት የታየውን የህዝብ እልህና ቁርጠኝነት ማስታወስ ብቻ ፊልም ማቀናበር መፍትሄ አንደማይሆን ለማገናዘብ በቂ ነበር፡፡ መንግስት የሙስሊሙን እንቅስቃሴ በማስመልከት ያፈሰሰው የፕሮፖጋንዳ ኢንቨስትመንት ውጤቱ ዜሮ ብቻ መሆኑን አሁን ያለውን ሁኔታ ብቻ መመልከት በቂ ነው፡፡ ‹‹የሸሪአ መንግስት ለመመስረት የሚፈልጉ ኃይሎች›› የሚለው ተረት ከተጣለበት ቦታ ተነስቶ እንደ አዲስ የሚራገበው ቀድሞውንም አሳመኝ ሳይሆን ቀርቶ መጣሉን ማስተዋል ተስኗቸዋል፡፡ የተሰሩ የፕሮፖጋንዳ ናዳዎች ሁሉ የመንግስት ተአማኒነት ሸርሽረው ወሰዱት እንጂ ይህ ነው የሚባል ጥቅም ሊሰጡት አልቻሉም፡፡ በጣም በሚያሳዝን መልኩ መሪዎቻችን ከዚህ ቀደም ያለ ፈቃዳቸው እንዲሁም ሕገ መንግስቱን በመጣረስ፣ የፍርድ ቤቱንም ትእዛዝ በመተላለፍ ራሳቸውን ወንጀለኛ አድርገው እንዲቀርቡ ተገደው የነበረበትን ትእይንት መንግስት እንደ አዲስ አሁንም አሳይቶናል፤ መንግስት ከሕግ በላይ መሆኑንም በተገቢው መልኩ መልእክት እያስተላለፈልን ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ማረጋጋጫ የሆነው የተጠርጣሪዎች ከፍርድ በፌት ነጻ ሆኖ የመታየት መብት ተደጋግሞ እየተሸረሸረ አይተነዋል፡፡

በመሰረቱ የሼህ ኑሩ ግድያ የትኛውም ሰው ሊያወግዘው የሚገባ ተግባር መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ሼኽ ኑሩ ስራቸውም ሆነ አስተሳሰባቸው የፈለገውን ያህል የተለየ ቢሆን እንኳ በዚያ አቋም ላይ የመቆየት ህገ-መንግስታዊ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯዊም መብት አላቸው፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብም ለፖለቲካ ገበያ ማሟሟቂያነት በመንግስት ሰልፍ እንዲወጣ ከመገደዱ በፊት ድርጊቱን አውግዟል፡፡ የዚህም ምክንያቱ ሁለት ነው፡፡ የመጀመሪያው በእምነታችን አንዲትን ነፍስ ማጥፋት ወንጀልነቱ በራሱ ግዙፍ መሆኑ ነው፡፡ ይህም በቁርአን በዚህ መልኩ ተገልጿል፡፡

‹‹እነሆ ያለ ነፍስ (መግደል) ወይም በምድር ላይ ያለማጥፋት (ካልሆነ በስተቀር) ነፍስን የገደለ ሰው ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው፤ ሕያው ያደረጋትም ሰው ሰዎቹን ሁሉ ሕያው እንዳደረገ ነው›› (ሱረቱል ማኢዳህ ቁጥር 32)

በሁለተኛ ደረጃ ይህ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሰላማዊነትን ብቻ የሚሰብክና ለመንግስት አካል በሰላማዊ መንገድ ብቻ ጥያቄውን ሲያቀርብ የቆየና ከማንኛውም የሀይል እርምጃ የተቆጠበ መሆኑ ነው፡፡

መንግስት በሼህ ኑሩ ግድያ ደጋግሞ በሰራው ፖሮፖጋንዳ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ግለሰቡን እንደገደሉ አድርጎ አቅርቧል፡፡ ሆኖም ይህን አጸያፊ ተግባር ሙስሊሙ ህብረተሰብ ፈጽሞ ሊፈጽመው እንደማይችልና በዚህ አይነቱ መሰል ተግባር እንደማይሳተፍም እሙን ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባካሄድነው ሰላማዊ ተቃውሞ ምክንያት ይህ ቀረሽ የማይባል ዱላ ከመንግስት ወገን ተሰንዝሮብናል፡፡ በርካታ ሙስሊሞች ታስረዋል፣ ተደብድበዋል፣ በወህኒ አሰቃቂ ቶርች ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ከ30 የሚበልጡ ዜጎችም ተገድለውብናል፡፡ ለዚህ ሁሉ የመንግስት የጭካኔ ተግባር ምላሻችን ሰላም ብቻ ነበር፡፡ ከሰሞኑ የዒድ በዓል እለት የመንግስት ታጣቂዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያንን ያክል አጸያፊ የጭካኔ እርምጃ ሲወስዱም ምላሻችን ሰላም ነበር፡፡ እንኳን አንድ የ80 ዓመት አረጋዊ ለመግደል ይቅርና ወንድሞቻችንን በቀን ብርሃን የገደሉ የፖሊስ ሀይሎች ላይ እንኳ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ድንጋይ አላነሳም፡፡

የተቃውሞ መርሐ ግብሮች ሲወጡ የሚገለጹት ዋነኛ የጥንቃቄ መርሆች ሰላማዊ መሆንና የጸጥታ አካላትን ትእዛዝ ማክበር የሚሉት ሁሌም እንዲከበሩ ሙስሊሙ ያላሳለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ፖሊስ ትንኮሳ ቢፈጽም እንኳ ከስሜታዊነት መራቅና ምንም አይነት አጸፋ አለመስጠት ወሳኝ እንደሆነ በመርህ ደረጃ የታመነበትና ተተግብሮም ውጤታማ የሆነ ነው፡፡ በመሀከል ሊያውኩ የሚገቡ አካላት እንኳ ካሉ ለጸጥታ አካላት ተላልፈው መሰጠት እንዳለባቸው፣ የሀይል አማራጭ መቼም አመራጫችን እንዳልሆነ መሪዎቻችን ከመታሰራቸው በፊት ደጋግመው ለህዝቡ ያስተላለፉትና ከእስራቸው በኋላም ህብረተሰቡ መርሁን በምልአት ሲተገብር የቆየ መሆኑን በተግባር አስመስክረናል፡፡ ከዚያ ይልቅ መንግስት እጅግ ዘግናኝ እርምጃዎችን ሙስሊሙ ላይ በአደባባይ በመውሰድ ህዝቡ በአፀፋ ወደ አመፅ እንዲገባ ሲገፋፋ ቆይቷል፤ መንግስት ይህን የሚያደርገው አመጽን ለፖለቲካው ትርፍ ሊጠቀምበት ስለሚሻ ነው፡፡ ሆኖም የህዝቡ ንቃት መንግስት ከሚያስበው የላቀ በመሆኑ ፈጽሞ በዚህ አይነቱ ተግባር ውስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተጠምዶ አልታየም፡፡ የተቃውሞ መርሐግብሮች በሚካሄድባቸው ቦታዎች የመንግስት አውቶብሶችን በብዛት በመደርደር የ‹‹ንብረት አውድሙ›› ጥሪ ደጋግሞ ከመንግስት ተላልፏል፣ የህዝቡ ምላሽ ግን በአንድነት ‹‹አንሰብርም›› የሚል ነበር፡፡ ምክንያቱም መንገዳችን ሰላም፣ ጥያቄዎቻችን ምላሽ እንዲያገኙ የምንሻው በሰላማዊ መንገድ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ የዚህ ሰላማዊ ትግል መርህ የሆነው ‹‹የምንገድልበት አላማ ባይኖረንም የምንሞትለት ዓላማ ግን አለን›› የሚለው ሐይለ ቃል የሚያስተላልፈው ግልጽ መልእክትም የሰላማዊነታችንን ዳርቻ ጭምር ነው፡፡

የጥያቄያችንንም ሆነ የሂደታችንን ሰላማዊነት እስካሁን በተጓዝነው መንገድ ልክ ማየትና መመርመር በቂ ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ከአወሊያ መስጂድ አሀዱ ብሎ ሲጀምር ከነበረበት ወቅት አንስቶ አሁን የ30 ሰዎች ሕይወት ነፍስ እስከጠፋበት ድረስ ያለውን ሂደት የተመለከቱ ታዛቢዎች ሁሉ ይህን ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን እንቅስቃሴው ያነገበው ጥያቄ ፍጹም የመብት ጥያቄ ብቻ መሆኑን በሙሉ አፋቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግስታት መስክረዋል፡፡ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተሟጋች የሆኑት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂውማን ራይትስ ወች፣ እንዲሁም ሲፒጄ በራሳቸው መርማሪዎችና ባለሙያዎች ታዛቢነት ያረጋገጡት ይህንኑ እውነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ያነሱት ጥያቄም ሆነ እየሄዱበት ያለው መንገድ ፍጹም ሰላማዊና ከሕጋዊ ማእቀፍ ያላፈነገጠ መሆኑን ከመመስከራቸውም በላይ መንግስት የሙስሊሙን ህብረተሰብ የሃይማኖት መብት እንዲያከብር፣ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚወስደውን የሀይል እርምጃ እንዲገታና ለሙሊሙ ህዝብ ተገቢውን የመብት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡

‹‹ሽብርተኝት››ን በዓለም አቀፍ ደረጃ እዋጋለሁ የምትለውና ለዚህም ከፍተኛ ፋይናንስ የምትበጅተው አሜሪካም በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ የጠራ አቋም ይዛለች፡፡ ‹‹በምስራቅ አፍሪካ የአሸባሪነት ስጋት አለብኝ›› በሚል ሰበብ እርዳታ ለማግኘት ሲል፣ እንዲሁም የተነሳበትን የመብት ጥያቄ ወደ ሌላ ለመቀልበስ የሚጥረው መንግስት ለተደጋጋሚ ያህል ጊዜያት ‹‹ሙስሊሞች አሻባሪ ናቸው›› የሚል ሪፖርቶችን ለአሜሪካ መንግስት ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ ሎቢስቶችን (ጎትጓቾችን) በመቅጠር ይህንኑ ሀሳብ ምእራባውያን ዘንድ ከፍ ለማድረግ ብዙ ጥሯል፡፡ ሆኖም የአሜሪካ መንግስት የሃይማኖት ነጸነት ኮሚሽን ለሁለት ጊዜያት ያህል ባወጣው ሪፖርት የሙስሊም ኢትዮጵያውያንን ሰላማዊነት ከመመስከሩም በላይ መንግስት ያሰራቸውን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እና ዳኢዎችን እንዲፈታ ጠይቋል፡፡ መንግስት አዲስ እምነት በማምጣት ሙስሊሙ ላይ በግድ እየጫነ መሆኑን፣ ይህንን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ በርካታ ሙስሊሞች ለእስር መዳረጋቸውንና ከስራ መሰናበታቸውን የአሜሪካ የሃይማኖት ነጻነት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ ይህንን ያስታወቀው ወደ ኢትዮጵያ ልኡካንን ይዞ በመምጣት ከመንግስት ባለስልጣናት፣ ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ከመሪዎቻችን ጠበቆች ጋር ጥልቅ ውይይት እና የራሱን ፍተሻና ምርመራ ካደረገ በኋላ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ‹‹መንግስት የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ከመጨቆን ይታቀብ›› በሚልም ማጠቃለያውን ሰጥቷል፡፡ የመንግስት ሙግት ግን ከዚህ በተቃራኒው ሆኖ ሰላማዊ ዜጎችን በአሸባሪነትና በአክራሪነት በመፈረጅ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘትና የእምነት ነጻነትን ለመደፍጠጥ በመጣጣር ላይ ይገኛል፡፡

መንግስት የሼህ ኑሩን ግድያ ከልክ በላይ በማጎንና ሰፊ የሚዲያና የሰልፍ ዘመቻዎችን ሲያዘጋጅ በመቆየቱ ‹‹ፖለቲካዊ ትርፍ መሸመቻ ከተደረገው የሼኽ ኑሩ ግድያ ጀርባ ያለው ማን ነው?›› የሚል ጥያቄ ተደጋግሞ በህብረተሰቡ እንዲነሳ አድርጓል፡፡ የሼኽ ኑሩ ግድያን አስመልክቶ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶችን ጨምሮ በቁጥር በርካታ የመንግስት ቢሮዎች፣ ተቋማትና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መግለጫ አውጥተዋል፡፡ በቁጥር በርካታ ሰልፎች ተደርገዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ውጤታቸው ባያምርም መንግስት ጉዳዩን ከፍ አድርጎ በማራገብ ለሚሻው የፖለቲካ ፍጆታ ሊጠቀምበት ሞክሯል፡፡ ‹‹ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ያልተናነሰ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጠው የተደረገው የሼህ ኑሩ ግድያ ከጀርባው ያዘለው ምንድነው?›› ተብሎ ተደጋግሞ ተጠይቋል፡፡ ለዚህም ነው ህብረተሰቡ ‹‹ከሼኽ ኑሩ ግድያ ጀርባ የመንግስት ረጃጅም እጆች አሉ›› ብሎ በጽኑ የሚያምነው፡፡ ሟች በመሞቻቸው የመጨረሻ ሰአታት ከመንግስት ሀላፊዎች ጋር ችግር ውስጥ ገብተው የነበረ መሆኑ፣ መንግስት የሟች አስክሬን እንዲመረመር አለመፍቀዱና ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ሁሉ ተድበስብሰው እንዲቀሩ ለማድረግ የሚደረገው ከፍተኛ ጥረት የግድያው ጥርጣሬ ከመንግስት እጅ እንደማያልፍ እንዲታሰብ አድርጓል፡፡

መንግስት ከሼህ ኑሩ ግድያና ራሱ ከሚያከናውናቸው የተለያዩ ተግባራት በመነሳት ‹‹የድምጻችን ይሰማ አሻባሪ ቡድን›› እያለ በአደባባይ መጥራት መጀመሩ ሌላው አሳፋሪ ጉዳይ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› በማለት አደባባይ የወጣውን የኢትዮጵያ ሙስሊም ህዝብ በሙሉ በሽብር መወንጀል ለአንድ መንግስታዊ አካል ምን ያህል ሊቀል እንደሚችል እና ምንስ የሞራል መነሻ ሊኖረው እንደሚችል ማሰቡ በራሱ ድካም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ለሁለት ዓመታት ያህል በሰላማዊ መድረክ ብቻ፣ ብዙዎች በፖሊስ ጥይት ከቤት እንደወጡ እየቀሩ እንኳ፣ የተቀደሱ የሆኑት መስጊዶች በፖሊሶች ሲዋረዱ፣ መስጂዶች በሙስሊም ደም ሲርሱ፣ እህቶቻችን በአጸያፊ መልኩ ጥቃት ሲሰነዘርባቸው፣ መሪዎቻችን በሽብር ሲወነጀሉ፣ በአስር ቤት ዘግናኝ ቶርች ሲፈጸምባቸው …. ህዝቡ አንድ እንኳ ድንጋይ አንስቶ ወርውሯልን? ‹‹ሐይል ነው አማራጬ›› ብሏልን? በፍጹም! የሰላምን ዋጋ አሸናፊነት የሚረዳው ሕዝብ ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› ብቻ ነበር ያለው፡፡ በ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› ውስጥ ተማጽኖ እና መጠይቅ ነው ያለው፡፡ ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› የፍትህ እና የእምት ነጻነት ጥሪ ነው! ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› የህገ መንግስት ይከበር፣ የህግ የበላይነት ይረጋገጥ መጠይቅ ነው፡፡ ይህን ጥሪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ደጋግመው ብለውታል፣ አሁንም ሕጉ እስኪከበር ድረስ ማለታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ታደያ ከሰላሳ ሚሊዮን የሚልቀውን ሕዝብ አሸባሪ ብሎ ለመፈረጅ መንደርደር ጤነኝነት ይሆን?

እንደተለመደው በዚህ ፊልም ውስጥም ሙስሊም ያልሆነውንና የክርስትና እምነት ተከታይ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ሕዝብ መንግስት ፍጹም ተስፋ መቁረጡን በሚያመላክት መልኩ ‹‹ሙስሊሞች መጡብህ››፣ ‹‹ሙስሊሞች እስላማዊ መንግስት ሊመሰርቱ ነው›› እና መሰል መያዣ መጨበጫ የሌላቸውን ውንጀላዎችን በማካተት ‹‹ሙስሊሞችን እንታገል›› በሚል በግልጽ የእምነት ግጭት እንዲከሰት በመስራት ላይ መሆኑን አመላከቶናል፡፡ መንግስት ከሰሞኑ ይህንኑ የእርስ በእርስ ጥላቻ የሚነዙ ኮንፈረንሶች ሲያዘጋጅ እንደከረመና ህብረተሰቡም ሳይቀበለው እንደቀረ፣ ሆኖም ሌሎች ትላልቅ ኮንፈረንሶችን በዚህ አጀንዳ ላይ ለማዘጋጀትና ህብረተሰቡን አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳሳ ለማረግ እየሰራ መሆኑ ታውቋል፡፡ የዚያው እቅድ አካል መሆኑን በሚያሳብቅ መልኩ መንግስት ባሳየው ድራማ ላይ መሪዎቻችንን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች የተናገሯቸውን ንግግሮች በመቀጣጠል ሙስሊም ያልሆነው ሰፊ ህብረተሰብ ላይ ሽብር ለመንዛት ሞክሯል፡፡ ይህን እኩይ መንገድ የተከተለው መንግስት ለሁለት አመታት ያህል ሲነዛው የከረመው የሀሰት ፖሮፖጋንዳ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ ሊገዛ ባለመቻሉና በተቃራኒው ሕዝቡ የተለመደ ኑሮውን መቀጠሉ፣ ከዚያም አልፎ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ላነሳው ጥያቄ ሌላው ኢትዮጵያዊ ወገን ዋነኛ ደጋፊና ተባባሪ እየሆነ መምጣቱ ድንጋጤ ውስጥ ስለከተተው ጭምር ነው፡፡ ሆኖም በመንግስት ወንበር የተቀመጠና መንግስታዊ ሀላፊነትን የተሸከመ አካል በዚህ መልኩ እምነቶችን የማጋጨት ድርጊት ላይ ሲሰማራ ማየቱ በራሱ ዘግናኝና ለህሊናም የሚከብድ ነው፡፡

በጣም ግልጽ በሆነ መልኩ ከሰሞኑ የመንግስት ፕሮፖጋንዳዎች መረዳት የቻልነው እውነታ መንግስት ሙስሊሞችን ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ብቻ ሳይሆን እርስ በእርሳችንም የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጣጥተን እንድንጫረስ ያለመ መሆኑን ነው፡፡ እንደሚታወቀው በሙስሊም ምሁራን መካከል የነበሩ አንዳንድ የሃሳብ ልዩነቶችን ለመፍታት ከፍተኛና ተከታታይ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ በእነዚህ ውይይቶች ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር እድሪስና ዶ/ር ጄይላንን ባካተተ መልኩ ለወራት ሲደረግ ቆይቶ በመሰረታዊ ሐሳቦች ላይ ስምምነት በመደረሱ አጠቃላይ የውህደት ፕሮግራም ለመፈጸምና የመግባቢያ ሰነድ ለመፈረም ዝግጅት በተደረገበት ወቅት ነው የመንግስት አካላት ውይይቱም ሆነ የአንድነት ፕሮግራሙ እንዲገታ በማድረግ የተጀመረውን አስደናቂ ሂደት እንዲደናቀፍ ያደረጉት፡፡ በዚህ ሂደት ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት የአህመዲን አብዲላሂ ጨሎ መጅሊስ አባላት ሲሆኑ ከፍተኛ የደህንነት ሐላፊዎች የውይይቱን አስተባባሪዎች እነ ሐጂ ኡመር እድሪስን በማስፈራራት እና ዛቻ በመሰንዘር ከተቀደሰ ተግባራቸው እንዲታቀቡ አድርገዋቸዋል፡፡ ሐጂ ኡመር እድሪስ በአንድነት ፕሮግራሙ በመሳተፋቸው ብቻም በመጅሊሱ ውስጥ በወቅቱ የነበራቸውን ስልጣን እስከመቀማት ደርሰዋል፡፡ የአንድነት ፕሮግራሙ ፍጻሜ አግኝቶ ቢሆን ኑሮ የመንግስታዊ ሃይማኖት አመራሮቹ ሊፈነጩበትም ሆነ ጸረ አንድነት አጀንዳቸውን ሊረጩ የሚችሉበት ቦታ ማግኘት ይሳናቸው እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ መንግስትም በሙስሊሙ አንድነት የሚመጣውን ለውጥ ቀድሞ በመገንዘብ ይህንኑ በር ለመዝጋት ይህ ነው የማይባል ጥረት አደረገ፡፡

ይህን ሁኔታ ማስታወስ ብቻ የመንግስትን ፍላጎትና ግብ ለመረዳት በቂ ነው፡፡ መንግስት አሁን ሊያስተላልፍ እየፈለገ ያለው መልእክት ‹‹የነካሁት የተወሰኑ ሙስሊሞችን እንጂ ሌሎች ሙስሊሞችን አይደለም፤ እገሌ የተባለውን ቡድን እያጠቃሁ በመሆኑ ሌሎቻችሁ አግዙኝ›› መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ መንግስት መሰረታዊ ስህተት የሰራው እዚህ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መንግስት እንደሚለው እርስ በእርስ ስያሜ ተሰጣጥተን በልዩነት የምንዳክርበት ጊዜ ፈጽሞ እንደሌለ እሙን ነው፡፡ በመሰረቱ መንግስት ‹‹አክራሪነትን እዋጋለሁ›› በሚል ሰበብ ጦሩን መዞ የሚገኘው ሙስሊሙ ላይ መሆኑ ለአፍታ እንኳ ጥርጣሬ ተሰምቶን አያውቅም፡፡ ይህን ለመረዳት መንግስት ለፖለቲካ አመራሮቹ በ2003 እና በ2004 አዘጋጅቷቸው የነበሩ ሰነዶችን መመልከቱ በቂ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በስፋት ሲገለጽ እንደነበረውም በእነዚህ ሰነዶች መንግስት ሃይማኖታዊ ተግባራትን መፈጸም ሁሉ አክራሪነትና አሸባሪነት እንደሆነ አስፍሯል፡፡ መንግስት በለበጣ ስያሜ እየሰጠ አንዱን ሙስሊም በሌላው ላይ ለማስነሳት በቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ዘፈን እስከማዘፈን ደርሷል፡፡ ይህ ጅምር ነገ ምን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ጥያቄ የለውም፡፡ ‹‹እገሌ የሚባለው ቡድን ተነስቶብሃልና ታገለው!›› የሚል መልእክት በማስተላለፍ አንዱን ጨርሶ ወደ አንዱ መሄድ የመንግስት የተለመደና ያረጀ ያፈጀ ስልት ነው፡፡

በሙስሊሙ መሀከል የልዩነት እሳት ማንደድ የድሮው መጅሊስ ሲሞክረው የቆየ ቢሆንም የተሳካለት ግን በጣም ጥቂት ነው፡፡ አሁን አልሀምዱሊላህ ሙስሊሙ ኡምማ አንድ ነው፡፡ ራሱን በተለያዩ ስያሜዎች ከፋፍሎ እርስ በእርሱ የሚናቆርበት መንገድ አይኖርም፡፡ መንግስት ሙስሊሙ ላይ የሰነዘረው ጥቃት ለሙስሊሙ አንድ መሆን ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከመንግስት የተሰነዘረበትን ቡጢ እየመከተም እየተሸከመም ያለው በጋራ ያለ ምንም ልዩነት ነው፡፡ ‹‹አዲሱ›› እና ‹‹አሮጌው›› የሚባል እስልምና የለም፡፡ ‹‹ነባሩ›› እና ‹‹መጤው›› የሚባል የስያሜ ልዩነት በመካከላችን የለም፡፡ ይህን በአፍ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር ሙስሊሙ አረጋግጧል፡፡ ተቃውሞ እያካሄደ ያለው መላው ሙስሊም ህብረተሰብ እንጂ የተወሰነ አስተሳሰብ ያለው አካል እንዳልሆነ በተለያዩ ክፍለ ሃገራት የተደረጉት የአንድነትና የሰደቃ ፕሮግራሞች አሳይተዋል፡፡ በተግባር የታየው አንድነትና አብሮ መፋቀር መንግስትን አስደንግጦታል፡፡ መሪዎቻችን የሰሩት ጀብዱ ሙስሊሙን ሁሉ በአንድ ጥላ ስር መሰብሰባቸው፣ በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ አይነት ስሜት እና ውህደት መፍጠራቸው ነው፡፡ ይህ አንድነት በመንግስት ሴራ ፈጽሞ ሊገረሰስ አይችልም!

በኢትዮጵያ በሙስሊሞች ላይ እየተፈጸመብን የሚገኘውን ተግባር ሁሉም አካላት በአንድነት እያወገዙት ይገኛሉ፡፡ ይህን ተግባር እንኳን የአገር ልጅ ኢትዮጵያውያን ይቅርና የውጪ ተቋማትና ዜጎች፣ መንግስታት፣ እንዲሁም የሰው ልጅ ሁሉ ሊያወግዘው የሚገባ ተግባር እየተፈጸመብን ይገኛል፡፡ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ሚና ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሙስሊሙ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ኢ-ፍትሃዊ ተግባር በመገንዘባቸው መንግስትን በተደጋጋሚ ያህል ጊዜያት ሲኮንኑት ነበር፡፡ ለህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄም ተገቢው ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ይህ የሚጠበቅና ተገቢ እርምጃ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የሙስሊሙን ሰላማዊ ትግል እና ጥያቄ ኢህአዴግም እንደ ፓርቲ ህጋዊነቱን የሚያውቀውና ሰላማዊ አካሄዱን ደግፎ በሚዲያው ያወጀለት የህዝብ እንቅስቃሴ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ መላው የሃገራችን ህዝብ ለሰላማዊ ትግላችን ድጋፍ መስጠቱና አና ለሰው ልጆች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መከበር የሚሰሩ አካላት ህጋዊ መንገድን በተከተለ አግባብ መደገፋቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ በወጣ መልኩ ግን መንግስት የሚሰራውን ደባ የተቃወሙ ሐይሎች ‹‹ከአክራሪዎችጋር ጋብቻ ፈጽመዋል›› በማለት በመሬት ላይ የሌለውን እውነታ ለማንጸባረቅ ሌት ተቀን እየሰራ ነው፡፡ ‹‹ሙስሊሙ በሃገሩ ጉዳይ አያገባውም፤ ሌሎችም ስለ ሙስሊሙ አያገባቸውም›› በሚል መነሻ በተከታታይ ስም ማጥፋት ሊሳካ ያልቻለውን የመከፋፈል ስልት በሌላ መንገድ ለማሳካት መሞከር የሚሳካ አለመሆኑን መገንዘብ ያሻል!

አላሁ አክበር!

No comments: