Tuesday, June 23, 2015

ኢህአዴግ የምክር ቤትና የክልል ወንበሮችን ሙሉ ለሙሉ አሸነፍኩ አለ

ገዢው የኢህአዴግ መንግስት በግንቦት ወር በተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ በተቃዋሚ ስር የነበረን አንድ ወንበር መልሶ በመውስድ ሁሉንም የፓርላማ ወንበሮች በብቸኝነት ማሸነፍ መቻሉን ትናንት ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ከዚህ በፊት በፓርላማ አንድ የተቃዋሚ እንዲሁም አንድ የግል ተወዳዳሪ ወንበሮችን ማግኘት ችለው የነበረ ሲሆን በዘንድሮው ምርጫ ኢህአዴግ ለመጀመሪያ ጊዜ መቶ በመቶ ማሸነፉን ይፋ አድርጓል።
የምርጫ ቦርድ ሰኞ ምሽት ይፋ ባደረገው ውጤት መሰረትም ኢህአዴግ 500 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮችን ሲያሸንፍ የፓርቲው አጋር ድርጅቶች ደግሞ 46 ወንበሮችን እንዳሸነፉ የቦርዱ ሀላፊዎች አስታውቋል።
በደቡብ ክልል በቦንጋ ጋዋት የተካሄደው ምርጫ ውጤት በቦርዱ ባለመጽደቁ ውጤቱ አለመካተቱን የቦርዱ ዋና ጸሀፊ ፐሮፌሰር መርጋ በቃና ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
በግንቦቱ መርጫ ከተመዘገበው 36 ሚሊዮን ህዝብ ከ 33 ሚሊዮን የሚበልጥ ድምጽ መሰጠቱን የቦርዱ ሀላፊ ፐሮፌሰር መርጋ በቃና ተናግረዋል።
ለክልል ምክር ቤቶች በተካሄደው በዚሁ ምርጫ ገዢው ኢህአዴግ 1 ሺ 984 ማሸነፍ እንደቻለና በቦንጋ የሶስት ብቻ ወንበሮች ውጤት አለመታወቁን ብሉምበርግ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የምክር ቤትና የክልል ወንበሮችን በብቸኝነት ሙሉ ለሙሉ በማሸነፍ የተለመደ ድሉን ይፋ ሲያደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን በርካታ መገናኛ ብዙሀን በመዘገብ ላይ ናቸው ።
ምርጫውን በብቸኝነት የታዘበው የ አፍሪካ ህብረት ከታዘባቸው ከ300 በላይ ጣቢያዎች 21 በመቶ ኮሮጆዎች ባዶ ስለመሆናቸው ሊያረጋግጥ የነበረው እንቅስቃሴ በሀላፊዎች ክልከላ እንደተደረገበት መግለጹ ይታወሳል።
አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በበኩላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች የድምጽ አሰጣጡን ሂደት እንዳይታዘቡ መደረጉና በጋዜጠኞች ላይ የተከፈተው ወከባ በምርጫው ሒደት ላይ ተጽእኖን አሳድሯል ሲሉ ስጋታቸወን መግለጻቸውን የታወሳል።

No comments: