Tuesday, June 30, 2015

በነጻ እንዲፈቱ በፍርድ ቤት የተወሰነላቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በድጋሚ ታሰሩ

ኢሳት ዜና (ሰኔ 23 2007)
ሰሞኑን ፍርድ ቤት ከእስር እንዲፈቱ ወስኖላቸው ፖሊስ በድጋሚ ለእስር በዳረጋቸው አራት የፓርቲ አባላት ላይ አቃቢ ህግ ይግባኝ ጠየቀ።
ተከሳሾች የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ጉዳያቸው ከውጭ ሆነው ለመከታተል ጥያቄ ቢያቀርቡም ከሳሽ አቃቢ ህግ ተቃውሞን እንዳቀረበ ከሀገር ቤት የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ጉዳዩን ለማየት የተሰየሙት ዳኛ ተከሳሾች እስካሁን ድረስ በእስር ቤት ስለመቆየታቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸው አንደኛ ተከሳሽ ባለመቅረቡ ምክንያት ክርክሩ ሰኔ 24 2007 እንዲካሄድ ውሳኔ ሰጥተዋል።
ከወራት በፊት መንግስት በሊቢያ የተገደሉ ኢትዮጵያዊያንን ድርጊት ለማውገዝ ጠርቶ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት አራቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ብጥብጥን ላማነሳሳት ተንቀሳቅሳችኋል ተብለው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ተከሳሾች በሁለት ወር እስራት እንዲቀጡ ቢወስንም አራቱ ተከሳሾች ከተላለፈባቸው የእስር ጊዜ በላይ በእስር ቤት በመቆየታቸው ፍርድ ቤት እንዲለቀቁ ሲል ወስኗል ።
ይሁንና ተከሳሾችን ከፍርድ ቤት በር ላይ ጠብቆ ለእስር የዳረጋቸው ፖሊስ ሁሉንም ተከሳሾች በአዲስ አበባ ከተማ 6ተኛ ፖሊስ ጣቢያ ይዞ እንደሚገኝ ታውቋል።
ከሳሽ አቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሾችን ሊለቅ ያልቻለው በተከሰሱበትና በተለቀቁበት ርዕስ ላይ ይግባኝ ስለጠየቀ መሆኑን አስረድቷል።
አቶ ኤርሚያስ ጸጋዬ፣ አቶ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ወይዘሪት ወይንሸት ሞላና፣ ቤተልሄም አካለ ወርቅ ከእስር እንዲፈቱ ውሳኔ ቢተላለፍባቸውም አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆባቸው ይገኛል።
ባቀረበባቸው አዲስ ይግባኝ ላይ ክርክር ላማካሄድም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለረቡዕ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ከወራት በፊት መንግስት ጠርቶት በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ከአንድ ሺ የሚበልጡ ለእስር ተዳርገው ከ 100 በሚበልጡት ላይ ክስ መመስረቱ የታወቃል።

No comments: