Saturday, June 6, 2015

ኢህአዴግ ካባረራቸው አባላቱ ጋር ለእርቅ እየተነጋገረ ነው


EPRDF ኢህአዴግ


(እሁድ ግንቦት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. June 7, 2015)፡- የትግል ታሪኩ ጥንካሬ በገዛ አባላቱ ተጋኖ የሚነገርለት ኢህአዴግ ሥልጣን ይዞ በቆየበት 24 ዓመታት ለህልውናው አስጊ የሆኑ ፈታኝ ጊዚያቶች በተደጋጋሚ አሳልፏል። ከእነዚህ ውስጥ በ1993 ዓ.ም. አመራሩ ለሁለት ተሰንጥቆ በነበረበት ጊዜ የደረሰው ውጣውረድ፣ በቀድሞው ጠ/ሚንስትር ሞት የደረሰው ክፍተት እንዲሁም የ1997ቱ ምርጫ ባስከተለው ህዝባዊ ዓመጽ መሬት ነክቶ የመመለሱ አደጋ የሚጠቀሱ ናቸው።
ኢህአዴግ እነዚህ ስብራቶቹን ጠግኖ እስካሁን ድረስ ለመጓዝ ቢችልም እራሱን በራሱ እየበላ የሚሄድ በመሆኑ ከምንግዜውም በላይ በአሁኑ ጊዜ እጅና እግሩ እንደሰለለበትና የአመራር ጎኑ እንደደቀቀ የሚያመላክት ሁኔታ እየታየበት ለመሄዱ የሰሞኑ የእርቅ ንግግር አመላካች ነው።
አቶ በረከት ስምዖን፣ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ አቶ እርካበ እቁባይ እና አቶ አዲሱ ለገሰ አስታራቂ እንዲሆኑት መርጦ፤ በ1993 ዓ.ም. የድርጅቱን ዓላማ የሚጻረሩ ናቸው ህዝብ በድለዋል ብሎ ካባረራቸው አባላቶቹ መካከል ከሌተናል ጀነራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤ፣ ከሜጀር ጀነራል አበበ ተ/ኃይማኖት (ጆቤ)፣ ከወ/ሮ አረጋሽ አዳነ፣ ከአውአሎም ወልዱ እና ከተወልደ ወልደማርያም ጋር ለመታረቅ በድርርድር ላይ ይገኛል።
በዚህ ስምምነት ከቀድሞ አባላቱ ጋር በብዙ ሁኔታ መስማማቱና እንዲሁም የተባረርነው አላግባብ ስለነበረ የካሳ ክፍያ ይገባናል ያሉትንም ለማሟላት ተስማምቷል። ሆኖም አቶ ገብሩ አስራት ድርጅቱን የሚጎዳ ንግግር ስለአደረጉ ለመመለስ ፍቃደኛ እንዳልሆነ አስታውቋል።
ኢህአዴግ የ2007 ዓ.ም. ምርጫን ጨምሮ በተካሄዱት አምስት ምርጫዎች ዓይን ባወጣ ሁኔታ አሸንፌአለሁ በማለት እስካሁን ድረስ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ቢችልም፤ ይህ ያሁኑ የእርቅ ስምምነት ችግር ውስጥ እንደተደፈቀ ያመላክታል ሲሉ አስተያየት የሰጡት የፖለቲካ ታዛቢዎች፤ ጨምረው እንደሚያብራሩት የእርቅ ሂደቱ ሰምሮ የቀድሞው አባላት በአመራሩ ተካተው ለመሥራት ቢችሉ እንኳን በተፈጠረው የቆይታ ክፍተት ምክንያት ልብ ለልብ ተግባብተው ለመሥራት እንደማይችሉና የታሰበውን ያህል ተመላሾቹ የብረት መዝጊያ ሆነው እንደማያገለግሉ ይናገራሉ።
Source: ethiopiazare

No comments: