Tuesday, June 9, 2015

በኢትዮ-ሶማሊያ ድንበር ተፈጸመ ለተባለው ግድያ ምርመራ እንዲደረግ ጥያቄ ቀረበ

ኢሳት ዜና
በቅርቡ በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር የተካሄደውን ግጭት ተከትሎ፥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውንና ከ 50 በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ደግሞ ወደ ጅጅጋ እስር ቤት መወሰዳቸውን የሶማሊያ ባለስልጣናት ገለጹ።
በድንበሩ አካባቢ የዘር ማጥፋት ድርጊት ተፈጽሟል የሚሉት የሃገሪቱ ባለስልጣናት፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእውነት አፈላላጊ ቡድንን ወደጋልጋዱድ ክልል በመላክ ማጣራት እንዲያደርግ ጥያቄ መቅረቡ ታውቋል።
የሶማሊያ ሕዝቦች ፓርቲ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ ኢሳ ሞሐመድ በኢትዮጵያ ልዩ ሃይሎች በ 18 መንደሮች በተፈጸመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መገደላቸዉንና ንብረታቸው መዘረፉን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በልዩ ሃይሎችና በሶማሊያ ጎሳ ታጣቂዎች መካከል ለቀናት በቆየው የድንበር ግጭት በርካታ መኖሪያ ቤቶች በእሳት መቃጠላቸውን ሃላፊው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት አብዲ ሞሐመድ ኦማር በክልሉ የሚገኙ ልዩ ሃይሎችን በማስተባበር የጅምላ ግድያው እንዲፈጸም ማድረጋቸውን የሶማሊ ህዝቦች ፓርቲ መግለጹን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ለተፈጸመው ድርጊት የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ ነው ያለው ፓርቲ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የእውነት አፈላላጊ ቡድን ወደ ስፍራው በመላክ ምርመራ እንዲያካሂዱ ጥያቄ ማቅረቡን አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ልዩ ሃይሎችና በሶማሊያ የጎሳ ታጣቂዎች መካከል ተካሄዷል የተባለው ግጭት የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል በተለያዩ የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን ይፋ የተደረገ ሲሆን በዚሁ የቪዲዮ ምስል ማንነታቸው የማይለይ በርካታ ሰዎች ሞተው ታይተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ድረስ የሰጡት ምላሽ ባይኖርም፥ የሶማሊያ ባለስልጣናት ምክክር እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

No comments: