Friday, June 26, 2015

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እየታደኑ እየታሰሩ ነው

• ከታሳሪዎቹ መካከል ሶስቱ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች ናቸው
በአማራ ክልል የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በአዲስ መልክ እየታደኑ እየታሰሩ መሆኑን የአይን እማኞች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ ከትናንት ሰኔ 18/2007 ዓ.ም ጀምሮ የሰማያዊ፣ የቀድሞው አንድነትና የመኢአድ አመራሮች እየታደኑ እየታሰሩ መሆኑ ታውቋል፡፡ ትናንት ሰኔ 18/2007 ዓ.ም የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የነበረው አዳነ አለሙ እና የመኢአድ አመራር የነበረው አቶ አበባው የተባለ ግለሰብ በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ዛሬ ሰኔ 19/2007 ዓ.ም በወንበርማ ወረዳ ሸንዲ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ የተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ የነበረው አቶ ፈንታሁን ብዙአየሁና አንድ የቀድሞው አንድነት አመራር ከወንበርማ እንዲሁም በአዴት የሰማያዊ ፓርቲ የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የነበረው አቶ ሞላ የኑስ መታሰራቸው ታውቋል፡፡
ሁለቱም የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች ያለ አግባብ በዕጩነት ተሰርዘናል በሚል ክስ መስርተው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረዛቸው አግባብ አለመሆኑን ወስኖ ወደ ዕጩነት ሲመልሳቸው የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ከዕጩነት እንዲሰረዙ አድርጓል፡፡ አቶ ፈንታሁን ብዙአየሁ እና አዳነ አለሙ እነሱን ጨምሮ ሌሎች የተሰረዙ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች ወደ ዕጩነት እንዲመለሱ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ተገልጾአል፡፡
በተጨማሪም በምስራቅ ጎጃም ዞን የቀድሞ አንድነት አስተባባሪ የነበሩት አቶ ልዑልሰገድ እምባቆም በደብረማርቆስ ከተማ ፖሊስ መያዛቸው ታውቋል፡፡ አቶ ልዑልሰገድን ዛሬ ሰኔ 19/2007 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ የያዛቸው የደብረማርቆስ ፖሊስ እስከ ቀኑ 5 ሰዓት ደብረማርቆስ ከተማ ውስጥ ካሰራቸው በኋላ ‹‹የያዝነህ እኛ አይደለንም፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ይፈልግሃል!›› በሚል ወደ ባህርዳር ከተማ ወስዷቸዋል ተብሏል፡፡
በየ አካባቢው በፖሊስ የተያዙት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ለጥቂት ጊዜ በየአካባቢያቸው እስር ቤቶች ከቆዩ በኋላ ወደ ባህርዳር ከተማ መዛወራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም መጀመሪያ የሰማያዊ፣ የአንድነትና የመኢአድ አመራሮችና አባላት ከየ ክፍለ ሀገሩ ተይዘው መታሰራቸው ይታወቃል፡፡

No comments: