Friday, June 5, 2015

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ክስ ተመሰረተባቸው

ግንቦት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ያለፉትን 9 ወራት በእስር ሲማቅቁ የቆዩት የሰማያዊ፣ የቀድሞው አንድነትና የመኢኢድ ፓርቲዎች የአመራር አባላት ላይ ክስ መመስረቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል። በአንደኛ ተከሳሽ ጌታቸው መኮንን መዝገብ 16 ሰዎች በሽብር ወንጀል መከሰሳቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
ተከሳሾቹ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን ፣ በላይነህ ሲሳይ፣ አለባቸው ማሞ፣ አወቀ ሞኝሆዴ፣ ዘሪሁን በሬ፣ ወርቅየ ምስጋና፣ አማረ መስፍን፣ › ተስፋዬ ታሪኩ፣ ቢሆነኝ አለነ፣ ታፈረ ፋንታሁን፣ ፈረጀ ሙሉ፣ አትርሳው አስቻለው፣ እንግዳው ዋኘው፣ አንጋው ተገኘ፣ አግባው ሰጠኝና አባይ ዘውዴ ናቸው፡፡
ተከሳሾቹ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ናቸው የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን ፣ በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ የደረሰባቸውን በደል ለፍርድ ቤት ለማሰማት ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካለቸውም። ጋዜጣው እንደዘገበው አንደኛው ተከሳሽ ጌታቸው መኮንን በማንነቴ ምክንያት ዘሬን እንዳልተካ ተደርጌአለሁ በማለት የደረሰበትን ለዳኛው አሳይቷል። ተከሳሹ ብልቱ ላይ በተፈጸመበት ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ለማወቅ ተችሎአል።
7ኛ ተከሳሽ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ በበኩሉ ‹‹አንዴ ብቻ ስሙኝ…ከዚህ በኋላ አልናገርም…እንደፈለጉ ይወስኑ…›› በማለት የደረሰበትን ለማስረዳት እድል እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱ ግን አቤቱታችሁን በጽሑፍ አቅርቡ በማለቱ እንዲናገር ሳይፈቅድለት ቀርቷል። አቶ ተስፋየ ታሪኩ ከዚህ ቀደም ከቅንጅቶች ጋር ከ2 አመታት ላላነሰ ጊዜ ታስሮ እድሜ ልክ ተፈርዶበት በድርድር በተደረገው የይቅርታ ጥያቄ ተፈትቶ ነበር።
ሌሎችም ተከሳሾች በማንነታቸው ላይ የተመሰረተ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ከመግለጻቸው በተጨማሪ የህክምና አገልግሎትም እያገኙ እንዳልሆነ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል። ፍርድ ቤቱም ለሐምሌ 1/2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በእነ ብርሃኑ ተክለያሬድ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ብርሃኑ ተ/ያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማው እና ደሴ ካህሳይ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበር ሲሆን፣ ለዛሬ እንዲያቀርቡ ይጠበቅ የነበረውን የክስ መቃወሚያ ማረሚያ ቤቶች እንድንገናኝ ስላላደረጉን መቃወሚያ ማቅረብ አልቻልንም በማለታቸው ለሰኔ 9/2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ተከሳሾች በማረሚያ ቤቶች እየደረሰብን ነው ያሉትን የመብት ጥሰት በቃል ያሰሙ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ግን አቤቱታቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ አዝዟል፡፡
ከዚሁ የፍርድ ቤት ውሎ ሳንወጣ ከግንቦት7 ጋር አብራችሁዋል በሚል የተከሰሱት ዘመነ ምህረት፣ መለሰ መንገሻ እና ጌትነት ደርሶ ልደታ 19ኛ ችሎት ቀርበው ከማንነታቸው ጋር በተያያዘ መሰደባቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። ጌትነት በማንነታቸውን ተደብድበናል፣ ተሰድበናል እያለ ቢናገርም ዳኞች አቤቱታውን ለማዳመጥ ፈቃደኞች አለሆኑም።
መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ሰበብ ተይዘው የታሰሩት ሜሮን አለማየሁ፣ ዳዊት አስራዳና አለነ ማህፀንቱም የፖሊስን ተጨማሪ ምስክሮችን ለመስማት ከአምስት ቀናት በሁዋላ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡ አራዳ ምድብ
ችሎት የቀረቡት እነ ሜሮን የዋስትና ገንዘብ ከፍለው ከተለቀቁ በኋላ በህገ ወጥ መንገድ የታሰሩ መሆናቸውን እና ቋሚ አድራሻ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ቢጠይቁም፣ ፖሊስ ‹‹በሰልፉ ወቅት ለህዝብ
ገንዘብ በመስጠትና በማደራጀት ዋና አደራጆች በመሆናቸው፣ ከኢትዮጵያ ለመውጣት እቅድ ያላቸው መሆኑና ምስክሮች ላይ ጫና ስለሚያደርጉብኝ›› በሚል 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቆ 5 ቀናት ተፈቅዶለታል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ኃላፊነት ያለባቸውና ቋሚ አድራሻ ያላቸው በመሆናቸው ከሀገር ለመውጣት እንደማይፈልጉ በመግለጽ የፖሊስን መከራከሪያ ተቃውመዋል፡፡ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ ዳዊት አስራዳ በአንድ ባንክ ውስጥ በከፍተኛ
ኃላፊነት የሚሰራና በቂ ደመወዝ የሚከፈለው እንዲሁም የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን ጠቅሶ ከአገር ለመውጣት አቅደዋል መባሉ ትክክል እንዳልሆነ ተናግሯል።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሜሮን አለማየሁ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ስትሆን ዳዊት አስራዳና አቶ አለነ ማህፀንቱ የቀድሞው አንድነት አመራሮች መሆናቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
Source: Ethsat

No comments: