Tuesday, December 2, 2014

ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ውስጥ የገባባቸው ምክንያቶች


 

አለሳ መንገሻ (የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር)

በ1983 ዓ.ም ነሃሴ ወር በሽግግሩ ወቅት አባል ሆኜ ከእነ አቶ መለስ ጋር ነበርኩ፡፡ በ1985 ዓ.ም በፓሪስ በተካሄደው የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የፓሪስ ጉባዔ ውሳኔ ምክንያት በርካታ ደቡብ ህብረት ውስጥ የነበሩ ድርጅቶች ከተወካዮች ምክር ቤት ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ የሽግግሩ ወቅት ቻርተር በተለይም ደግሞ በቻርተሩ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች አዋጅ መካተቱ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ይፈታል የሚል እምነት የነበረን ሰዎች የዛ አካል ነበርን፡፡ ነገር ግን በዛ አካሄድ ብዙም ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል ስላመንን ከሽግግር መንግስቱ ውጭ ሆነን የተቃውሞውን እንቅስቃሴ ተቀላቅለናል፡፡ 

ከምርጫ ህጉና ከምርጫ ቦርድ ላይ የሚነሱ ጉዳዮች

ከምርጫ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች ህጋዊ ነጻነታቸው ምንድን ነው? አንደኛው ህጋዊ መሰረት ህገ መንግስቱ ነው፡፡ የህገ መንግስቱ አንቀጽ 38 የመምረጥና የመመረጥ መብትን ያውቃል፡፡ በአንቀጹ ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ‹‹ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሄር፣ በብሄረሰብ፣ በ ጾታ፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖት፣ በፖለቲካ ወይንም በሌላ አመለካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት የሚከተሉት መብቶች አሉት›› ይላል፡፡

‹‹በቀጥታና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በህዝብ ጉዳይ አስተዳደር ላይ የመሳተፍ መብት›› ይላል፡፡ ይህን ሳልዘረዝረው ህገ መንግስቱ የመምረጥና የመመረጥ መብትን በዚህ መልኩ ያውቀዋል፡፡ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ይህንን መብት ተጨባጭ ለማድረግ ይህንን መብት እውን ለማድረግ የሚያስችል ተቋም ስለሚያስፈልግ የምርጫ ቦርድ እንዲቋቋም ደንግጓል፡፡ አንቀጽ 102 (1) ላይ ‹‹በፌደራልና የክልል ምርጫ ክልሎች ነጻና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲያካሄድ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ የሆነ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል›› ይላል፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ ምርጫን በሚመለከት ይህ መሰረት አለ፡፡ 

ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ የተሻሻለው የምርጫ ህግ ቁጥር 532/1999 አለ፡፡ ከዚህ ህግ አላማዎች መካከል አንዱ ‹‹ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ ነጻ፣ ገለልተኛና ፍትሃዊ ምርጫ በማካሄድ በህዝብ ድምጽ የተመረጠ መንግስት እንዲቋቋም ማድረግ›› ይላል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እኛ ለምናነሳው የመምረጥና የመመረጥ ጥያቄ የህዝብን ሉዓላዊነት በምርጫ አማካኝነት፣ በተወካዮቹ በኩል ለሚያነሳው ጥያቄ ህጋዊ መሰረቱ ህገ መንግስቱና የተሻሻለው የምርጫ አዋጅ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ብቻ ግን አያበቃም፡፡ ሌላም ህጋዊ መሰረት አለው፡፡ ሶስተኛው የምርጫ ህጋዊ መሰረት ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ቃል ኪዳኖች፣ አዋጆች፣ ድንጋጌዎች ናቸው ይላል፡፡ ከእነዚህ መካከል መጠቀስ ያለበት ከሀይማኖት ድንጋጌዎች ቀጥሎ በፖለቲካው ዓለም የተዋጣለት ሊባል የሚችለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች አዋጅ የኢትዮጵያ ህግ አካል ሆኗል፡፡ የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች አዋጅ የሚባለውም ተካትቷል፡፡ የአፍሪካ የዴሞክራሲ፣ ምርጫና የመልካም አስተዳደር ቻርተር የሚባለው የኢትዮጵያ ህግ አካል ነው፡፡ 

አሁን ከኢህአዴግ ጋር መነጋገር የምንፈልገው እነዚህ በህገ መንግስቱ ውስጥ ያሉ፣ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አዋጅ፣ በዓለም አቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብት እንዲሁም በአፍሪካው ቻርተር ያሉት መሰረታዊ መብቶች ከኢትዮጵያ ህግ ይውጡልን አይደለም፡፡ ጥያቄው ተግባራዊ መሆን አለባቸው የሚል ነው፡፡ እነዚህ በህግ ማዕቀፍነት ደረጃ በየትኛውም ዓለም ተቀባይነት ያላቸው ስለሆኑ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ 

ምርጫ ቦርድ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ያወጣቸው ደንቦችና መመሪያዎችም አሉ፡፡ እነዚህ ደንቦችና መመሪያዎች የሚያስቀምጡዋቸው መርሆች ከህገ መንግስቱ፣ ከምርጫ አዋጅና ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ህጎች የመነጩ ናቸው፡፡ እነዚህ መርሆች ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ በቂ የህግ መሳሪያዎች ናቸው፡፡

ይህ ሁሉ የህግ ማዕቀፍ እያለ እስከዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄዱት ምርጫዎች ለምን ችግር ውስጥ ወደቁ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ በቀላሉ የምርጫ አስፈጻሚው አካል ገለልተኛ ቢሆን ኖሮ ህጎቹ የዚህን ያህል የተፈጻሚነት ባህሪያዊ ችግር ያለባቸው አይደሉም፡፡ ነገር ግን የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡

ምርጫ ቦድር ጥያቄ ውስጥ የገባባቸው ምክንያቶች 

1. የምርጫ ቦርዱ አሰያየም፡- የምርጫ ቦርድ ጥያቄ ውስጥ የሚገባው ቦርዱ የተሰየመበት አካሄድ ከወገንተኝነት ያልጸዳ በመሆኑ ነው፡፡ በምርጫ ቦርድ አዋጅ እንደሚለው ዘጠኙ የቦርድ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ ይላል፡፡ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ዛሬ አራት ኪሎ ባለው ፓርላማ ሁኔታ፣ 99.6 በመቶውን የፓርላማ መቀመጫ በአንድ ፓርቲ በወደቀበት አገር፣ ይህንን ስልጣን ለአንድ ፓርቲ መስጠት ወገንተኝነትን ለመከላከል የሚያስችል በቂ መሳሪያ በእጃችን የለም፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርዱ የተሰየመበት መንገድ ለወገንተኝነት ክፍት ነው፡፡ 

2. ግልጽነት፡- የምርጫ ቦርድ ሁኔታ ግልጽነት የጎደለው ነው፡፡ የምርጫ ቦርድ ሰዎች ተሰየሙ ሲባል እንሰማለን እንጂ ይህንን ያህል አገራዊ ኃላፊነት የሚጣልበት ተቋም የሚሰየሙበት ሂደት ለህዝብ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህም የገለልተኝነት ጥያቄ እንድናነሳ የሚያደርግ ነው፡፡ 

3. የምርጫ አስፈጻሚ አካላት መዋቅር ለገዥው ፓርቲ ጣልቃ ገብነት ክፍት የተደረገ መሆኑ፡- ከራሱ ከአዋጁ አንቀጽ 7 (14) የቦርዱ ስልጣንና ተግባር በሚለው ስር ‹‹ቦርዱ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ይመለምላል፣ ይመድባል፣ ያንቀሳቅሳል›› ይላል፡፡ ይህ ለምርጫ ቦርድ የተሰጠ ስልጣን ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ከመንግስታዊ አካላት ምርጫ አስፈጻሚዎችን ሲመለምል፣ ዛሬ መንግስታዊ መዋቅሩን የተቆጣጠረውና ከመንግስትነት ጀርባ ያለው ገዥው ፓርቲ እንደሆነ፣ የመንግስት ሰራተኞች በገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ስር እንደወደቁ ስለምናውቅ መንግስትም ሆነ ገዥው ፓርቲ ከሚቆጣጠራቸው ተቋማት ምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎችን መልምየ መደብኩ በሚልበት ጊዜ ስለ ገለልተኝነታቸው አሳማኝ ነገር ልናገኝ አንችልም፡፡ 

ምርጫ ቦርድ ‹‹መንግስታዊ ካልሆኑ አካላትም የምርጫ አስፈጻሚዎችን ይመድባል›› ይላል፡፡ አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በየ ቀበሌው ‹‹መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት›› የሚባሉት እነማን ናቸው? መንግስታዊ አካላት ማለት በተለይም ከምርጫ 1997 በኋላ የበጎ አድራጎትና የማህበራት ኤጀንሲ ከተቋቋመ በኋላ ‹‹መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች›› ማለት የኢህአዴግ አደረጃጀቶች ናቸው፡፡ የወጣቶች ማህበር፣ የሴቶች ማህበር፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማህበር፣ የኮሌጅ ተማሪዎች ማህበር፣ የሰራተኛ ማህበር፣ የሰራተኛ ማህበር፣ የሰራተኛ ኮንፌደሬሽን፣ የልማት ምክር ቤት፣ የዛ ብሄር የልማት ማህበር፣ ሸማቾች ማህበር፣ አነስተኛና ጥቃቅን፣ ኑ ቡና ጠጡ ማህበር....፡፡ ምርጫ ቦርድ በአዋጁ አንቀጽ 7/14 መሰረት የምርጫ አስፈጻሚዎችን የሚመድበው ከእነዚህ አካላት ነው፡፡ ስለዚህ አራት ኪሎ ፓርላማ ያለው ኢህአዴግ፣ መንግስታዊ ካልኑ ድርጅቶች በስተጀርባ ያለው ኢህአዴግ፣ ያንን መዋቅር ተከትሎ የምርጫ አስፈጻሚ የሚሆነው ኢህአዴግ ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት ለመጠየቅ በቂ ምክንያት አለን ብየ አምናለሁ፡፡ 

4. የምርጫ አስፈጻሚዎች አመዳደብ፡- የምርጫ አስፈጻሚዎች የስነ ምግባር መመሪያ ቁጥር 4/2001 የሚለውን እንመልከት፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ከየትኛው አካል እንደሚመርጡ በምርጫ ቦርድ አዋጅ ላይ ተቀምጦአል፡፡ ማን ነው የሚመለምላቸው? ሲባል የቦርዱ ጽ/ቤት የክልል ጽ/ቤት አስፈጻሚዎችን ይመለምላል፡፡ በክልል ደረጃ ያሉትን 9 የምርጫ አስፈጻሚዎችን የመመልመል ስልጣን የምርጫ ቦርድ ነው፡፡ አንድ ኃላፊና ቁጥራቸውን ሳያስቀምጥ ሌሎች ይላል፡፡ ስለዚህ 1+9X ብለን ነው የምናስቀምጠው፡፡ ይህንን በ9ኙም ክልሎች የሚሾመው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ እነዚህም ‹‹መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት›› ነው የሚመለመሉት፡፡ 

ምርጫ ቦርድ የክልል ምርጫ ጽ/ቤቶች ኃላፊን ይሾማል፡፡ ከእሱ በታች ደግሞ የምርጫ ክልል የሚባለው አለ፡፡ የምርጫ ክልሉን አስፈጻሚ የሚሾመው የክልል ምርጫ ጽ/ቤት ኃላፊው ነው፡፡ ቦርዱ ዘጠኝ (9+) በላይ ይሰይማል፡፡ 9ኙ የምርጫ ክልሎች በአገሪቱ ያሉትን 547 የምርጫ ክልሎች አስፈጻሚዎችን ይሰይማሉ፡፡ የየክልሉ አስፈጻሚዎች የ547 ምርጫ አስፈጻሚዎችን ይመርጣሉ፡፡ የምርጫ ክልል ስራ አስፈጻሚዎች 3 ናቸው፡፡ እነዚህን ሶስት ሰዎች የሚሰይመው የክልሉ ምርጫ ጽ/ቤት ነው፡፡ አሁን የሚቀረው የምርጫ ጣቢያ የሚባለው ነው፡፡ እነዚህን የሚመድበው የምርጫ ክልሉ ነው፡፡ የምርጫ ክልልና የክልል ምርጫ አስፈጻሚ ልዩነት እንዳላቸው ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ 547 የምርጫ ክልሎች አሉ፡፡ 43 500 የምርጫ ጣቢያዎች አሉ፡፡ በአንድ የምርጫ ጣቢያ 5 አስፈጻሚዎች ይኖራሉ፡፡ 43 500 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ አምስት አምስት አስፈጻሚዎች ሲመደቡ በአጠቃላይ በአገሪቱ 217 500 የምርጫ አስፈጻሚዎች ይኖራሉ፡፡ 
እነዚህን የምርጫ አስፈጻሚዎች የሚመድባቸው የምርጫ ክልል ነው፡፡ ይህ መዋቅር ከምርጫ ቦርድ ርቆ በየገጠሩ ያለ መዋቅር ነው፡፡ በኢትዮጵያ በአማካይ በአንድ ምርጫ ክልል 80 ጣቢያ ነው ያለው፡፡ በአንድ ምርጫ ክልል 400 የምርጫ አስፈጻሚዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን 400 የምርጫ አስፈጻሚዎች በምርጫ ክልሉ ያሉ ሶስት ሰዎች ናቸው የሚመድቧቸው፡፡ አንድ ምርጫ ክልል ከተማና ገጠርን አጠቃልሎ ሊይዝ ይችላል፡፡ ሶስት ሰዎች በምን ያህል ተቋማዊ ብቃት ነው? ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ይህን ሁሉ እየሰራ ያለው ታች እሱ በማይቆጣጠረው ለኢህአዴግ ባስረከበው መዋቅር ነው፡፡ የሶማሊ ክልል የምርጫ ክልል ማለት በሁለት ቀን የእግር ጉዞ መድረስ የሚቻልበት አይደለም፡፡ ደቡብ ኦሞ ውስጥ ያለ የምርጫ ክልል በሁለት ቀን የሚሸፈን አይደለም፡፡ 3 ሰዎች 400 የምርጫ አስፈጻሚዎችን እንዲቆጣጠሩ መደረጉ በምርጫ ቦርድ ላይ ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ 

5. የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ጉዳይ፡- የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ከየት ነው የሚመጡት? በመመሪያው 3/2002 አንቀጽ 7(2) የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ከብዙሃን ማህበራት እና ከሙያ ማህበራት ይውጣጣሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የብዙሃን ማህበራት የሚባሉት የሴቶች ፌደሬሽኖች፣ የሴቶች ማህበራት፣ የወጣቶች ማህበራት.... የመሳሰሉት ናቸው ታዛቢ ይሆናሉ የሚባሉት፡፡ በአሁኑ ወቅት ‹‹የሙያ ማህበራት›› የሚባሉት ናቸው እንግዲህ የምርጫ ታዛቢዎች ይሆናሉ የሚባሉት፡፡ በ2002 ዓ.ም ምርጫ በንግድ ምክር ቤቱ ግንባር ቀደምነት የተመራው ‹‹የምርጫ ታዛቢዎች ጥምረት›› 40 ሺህ ታዛቢዎችን አሰማርቶ ‹‹ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ ነው›› ብሏል፡፡ ለዚህኛው ምርጫም የምንጠብቀው እነዚህን ታዛቢዎች ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ እነዚህ ታዛቢዎች እንደሚመደቡ እያወቀ ገለልተኝነቱን ማስጠበቅ ባለመቻሉ ከዚህ ጨዋታ በኋላ የሚመጣውን ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ እንድንልለት ይፈልጋል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው፡፡ እኛ መፍትሄ ይሆናል ብለን ያሰብነው በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ከምርጫ ቦርድና ከገዥው ፓርቲ ጋር መነጋገር ነው፡፡ 

(ይህ ጽሁፍ አቶ አለሳ መንገሻ ቅዳሜ ህዳር 20 በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ‹‹የኢትዮጵያ ምርጫ ተሞክሮዎች እና ቀጣይ አቅጣጫ›› በሚል ካቀረቡት ውይይት የተወሰደ ነው)

Source: Negere ethiopia

No comments: