Tuesday, December 16, 2014

ጦማርያኑና ጋዜጠኞች ተጨማሪ 20 ቀናት ተሰጠባቸው



∙ተሻሻለ በተባለው ክስ ላይ አስተያየት ተሰጥቶበታል
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የዞን 9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ተጨማሪ 20 ቀናት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ዛሬ ታህሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም ለ13ኛ ጊዜ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ጦማርያኑና ጋዜጠኞች በጠበቆቻቸው አማካኝነት ቀደም ብሎ ተሻሽሎ በቀረበባቸው ክስ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆችም ተሻሻለ በተባለው ክስ ላይ አስተያየታቸውን በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ጠበቆቹ አስተያየታቸውን በጽሑፍ ከማቅረባቸው በተጨማሪ በቃል ለችሎቱ ለማስረዳት ጠይቀው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹በጽሑፍ ካቀረባችሁ በቃል መድገም አያስፈልግም›› በሚል ሳይፈቅድላቸው ቀርቷል፡፡
ጠበቆቹ ‹‹ተሻሻለ የተባለው ክስ ምንም መሻሻል የለውም›› በማለት ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት ቢሞክሩም፣ ችሎቱ ንግግራቸውን አቋርጦ ‹‹ክሱ በታዘዘው መሰረት መሻሻል አለመሻሻሉን መርምሮ የሚወስነው ፍርድ ቤቱ ነው›› ሲል አስረድቷል፡፡
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ጠቦቆች የቀረበውን አስተያየትና ቀደም ብሎ ለአቃቤ ህግ ክሱን እንዲያሻሽል የሰጠውን ትዕዛዝ በማገናዘብ ጉዳዩን መርምሮ ክሱ በምን አግባብ እንደተሻሻለ አይቶ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments: