ኢሳት (ጥር 25 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር መነሻነት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተከትሎ ለእስር የተዳረጉ በርካታ ሰዎች በቃሊቲና ሌሎች እስር ቤቶች ስቃይ እየተፈጸመባቸው መሆኑን የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ አስታወቀ።
እነዚሁ በጨለማ ክፍል ታስረው የሚገኙ እስረኞች በጸጥታ ሃይሎች ለሰዓታት የቆየ ድብደባና እንግልት እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ ሊጉ የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ይፋ አድርጓል።
በዚሁ የቃሊቲ እስር ቤት ከድር ዝናቡ፣ አብዲሳ ኢፋ፣ አብዲ ብሩ፣ በንቲ ደገፉ፣ ደጃዝማች በየነ እና ሁሴን አብዱራህማን የተሰኙ ታሳሪዎች ከተፈጸመባቸው ድብደባ የተነሳ አካላቸው ደም በደም ተለውሶ መታየቱን ሊጉ መረጃዎችን አስደግፎ አቅርቧል።
በስም ከተገለጹት መካከልም ሁሴን አብዱራህማን የተሰኘ ታሳሪ ከሌሎች እንዲለይ ተደርጎ አሁን ያለበት ሁኔታ እንደማይታወቅ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ ገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ ወደ አምስት ሺ የሚጠጉ ተማሪዎችና ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸውን የፓርቲ አመራሮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ሲገልጹ መቆየታቸውን ይታወሳል።
እልባትን ባላገኘው በዚሁ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ከ150 በላይ የሚሆኑ ሰዎችም በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች መገደላቸውን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በቅርቡ በዚሁ የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ላይ ልዩ መድረክን ያዘጋጀው የአውሮፓ ፓርላማ የፀጥታ ሃይሎች የወሰዱትን እርምጃ በማውገዝ የተፈጸሙ ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበት መጠየቁ ይታወሳል።
በቅርቡ በዚሁ የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ላይ ልዩ መድረክን ያዘጋጀው የአውሮፓ ፓርላማ የፀጥታ ሃይሎች የወሰዱትን እርምጃ በማውገዝ የተፈጸሙ ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበት መጠየቁ ይታወሳል።
የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ውሏል ቢሉም በርካታ ተማሪዎች ለእስር የተደረጉ ተማሪዎች እንዲፈቱና የፀጥታ ሃይሎች ከዩንቨርስቲዎች አካባቢ እንዲርቁ ጠይቀዋል።
ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ህብረት ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመታደም ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ የአሜሪካ ባለስልጣናት ሃገራቸው ተቃውሞን በልዩ ሁኔታ እየተከታተለች መሆኑን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሃላፊ የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በሰላማዊ ሰልፈኞች የተነሳው ጥያቄ አግባብ መሆኑንና የተወሰደው የሃይል እርምጃ ስህተት እንደነበር አስታውቅዋል።
በአዲስ አበባ ቆይታ የነበራቸው የሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ተወካይ የሆኑት ቶም ማሊንዎስኪ በበኩላቸው ጉዳዩን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝና ሌሎች አካላት ጋር መምከራቸውን ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment