Monday, February 22, 2016

መንግስት ከብሄራዊ ባንክ ተበድሮ ያልመለሰው ገንዘብ 92 ቢሊዮን ብር ድርሷል ተባለ

ኢሳት (የካቲት 22 2008)
አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለመንግስት የሚሰጠውን ቀጥተኛ ብድር እንዲያቆም ቢያሳስቡም ባንኩ ለመንግስት እያበደረ ያለው ገንዘብ በመጨመር ላይ መሆኑ ተገለጠ። 
ባንኩ ለፌዴራል በጀት መሸፈኛ ካበደረው ገንዘብ ውስጥ ያልተመለሰለት ገንዘብ 92 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። 
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው የመንግስት ብድር እየጨመረ መሄድ ለሃገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ማደግ አስተዋጽዖ ማድረጉን በመገለጽ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን አስረድተዋል። 
የብሄራዊ ባንክ ለመንግስት አበድሮ ካለተመለሰለት 92.1 ቢሊዮን ብር ውስጥም 9.7 በመቶ የሚሆነው በቦንድ ተበድሮ ያልተመለሰ መሆኑም ታውቋል። 
የአለም አቀፍ ሞኒተሪ ፈንድ (አይ ኤም ኤፍ) እና የተለያዩ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት ከብሄራዊ ባንክ በሚበደረው ገንዘብ ላይ ማስተካከያን እንዲያደር ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል። 
ይሁንና መንግስት ከብሄራዊ ባንክ የሚወስደው ብድር እየጨመረ በመምጣቱና ያልተከፈለ ብድርም በመኖሩ ምክንያት የዋጋ ግሽበቱ እያደገ መምጣቱን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገልጸዋል። 
የተያዘው ወር የአሃገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 10.2 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ቁጥሩ እድገትን እያሳየ ሊሄድ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል። 
በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያበደረው ገንዘብ 23.3 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ቁጥሩም ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር 15.3 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተገልጿል።

No comments: