Monday, February 22, 2016

የብሪታኒያና የኖርዌይ መንግስታት ዜጎቻቸው በኦሮሚያ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ በድጋሚ አሳሰቡ

ኢሳት (የካቲት 22 2008)
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች ዳግም የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የብሪታኒያና የኖርዌይ መንግስታት ዜጎቻቸው በክልሉ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ በድጋሚ አሳሰቡ። 
ለተቃውሞ በደቡብ ክልል በሚገኙ አካባቢዎች መዛመቱን ያስታወቀው የብሪታኒያ መንግስት የላንጋኖ ሃይቅን ጨምሮ በዝዋይ ወረዳት በምስራቅ ሸዋ ዞኖች በሚገኙ አካባቢዎች ዜጎች ጉዞን እንዳያደርጉ ጠይቋል። 
አርሲ ነገሌ፣ ሲራሮ፣ ኮፈሌ፣ ዶዶላ እና ኮኮሳ ወረዳዎችም ዳግም ተቃውሞ የተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች በመሆናቸው የብሪታኒያ ዜጎች አስቸኳይ ካልሆነ በስተቀር መጓዝ እንደሌለባቸው የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳስቧል። 
በተመሳሳይ ሁኔታም መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የኖርዌይ ኤምባሲ ዜጉች በክልሉ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ በድጋሚ ጠይቋል። 
በኦሮሚያ ክልል ያለው ተቃውሞ ዳግም ማገርሸትን ተከትሎ በሃገሪቱ የሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካይ ተቋማትም ተመሳሳይ ማሳሰቢያን ለሰራተኞቻቸው በማሰራጨት ላይ መሆናቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

No comments: