Friday, February 19, 2016

በምዕራብ አርሲ ከተሞች በተቀሰቀሰው ግጭት የሟቾች ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 10 2008)
በሳምንቱ መገባደጃ በምዕራብ አርሲ አካባቢ በሚገኙ ከተሞች የተቀሰቀሰው ግጭት ለአምስተኛ ቀን ቀጥሎ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ነዋሪዎች ገለጹ። 
በአካባቢው ተሰማርተው የሚገኙ የፌዴራል እና የክልል የጸጥታ ሃይሎች የጅምላ እስር በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ሻሸመኔ ከተማን ጨምሮ በአጄና በአቅራቢያ ባሉ የገጠር ከተሞች የፀጥታ ሃይሎች በፈጸሙት የተኩስ እርምጃ እስካሁን በትንሹ 17 ሰዎች ህይወት ማለፉንም ነዋሪዎችና እማኞች አስታውቀዋል።
በነዋሪዎች ላይ እየተወሰደ ካለው የሃይል እርምጃ በተጨማሪም በርካታ ሰዎች የገቡበት እንደማይታወቅና የጀምላ እስር እየተካሄደ መሆኑንም እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል። 
የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በአካባቢው የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠር የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ጥረትን እያደረጉ እንደሆነ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
በአካባቢው ለግጭቱ መንስዔ የሆነውን ጉዳየ ለማወቅም ጥረት እየተደረገ ይገኛል ሲሉ ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
የሞዕራብ አርሲ አካባቢ ነዋሪዎች በበኩላቸው በባለስልጣናት እገዳ የተጣለበት የኦሮምኛ ዘፈን በአንድ የሰርግ ስነ-ስርዓት ላይ በመዘፈኑ ምክንያት የፀጥታ ሃይሎች የወሰዱ የሃይል እርምጃ ለግጭቱ መንስዔ መሆኑን ይገልጻሉ።
ይኸው ድርጊት የነዋሪዎችን ቁጣ ቀስቅሷል የሚሉት እማኞች ግጭቱ ከአራት በላይ በሚሆኑ ከተሞችና የገጠር መንደሮች መዛመቱን አስታውቀዋል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞን ባሰሙ ሰዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ በትንሹ 17 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ የመንግስት ባለስልጣናት ሰባት የጸጥታ አባላት ተገድለዋል በማለት በነዋሪዎች ላይ የደረሰን አደጋ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል በአካባቢው በመስፈር 24 ሰዓት ቁጥጥር እያደረገ እንደሆነም ከሃገር ቤት ከተገኙ መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።


No comments: