Wednesday, February 10, 2016

በሙስና የተባረሩት በሌሎች ቦታዎች እየተመደቡ ነው

የካቲት (ሁለት) ቀን ፳፻፰ / ኢሳት ዜና :- የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት መልካም አስተዳደር አጓድለው በተገኙት አመራሮች ላይ እርምጃ በመውሰድ ቁጥራቸው አራት ሽህ በላይ የሚሆኑ አመራሮችንና ሠራተኞችን ገምግሞ ከስራ ማሰናበቱን ቢገልጽም፣ ከእነዚህ ውስጥ 260 በላይ የሚሆኑት በአመራር ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ መሆናቸው ታውቋል።
በአንድ ክፍለ ከተማ ውስጥ የነበሩ ስድስት የኮር አመራሮች ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ተብለው ከነበሩበት ቦታ ተገምግመው እንዲነሱ ቢደረግም ውሳኔው ከተላለፈባቸው ኃላፊዎች ውስጥ ግን ዋና ሥራአስፈፃሚው የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተደርጎ ሲሾም ምክትል ኃላፊውና ዋና ካድሬው ትምህርት ቤት እንዲገቡ ተደርገዋል። ሁለተኛ ካድሬው የልደታ ክፍለ ከተማ የቤቶች ኃላፊ ሲደረግ የመሬት ማኔጅመንት ኃላፊው የክፍለ ከተማ የፍትህ ኃላፊ ሆኖ ተሾሟል። 
ወደ ትምህርት ቤት የተላኩት አመራሮች ከነሙሉ ደሞዛቸው ሲሆን በእነሱ ቦታ ደግሞ አዲስ አመራሮች ተሰይመዋል። ከኃላፊነታቸው ለተነሱት አመራሮችና አዲስ ለተተኩት አመራሮች መስተዳደሩ የደሞዝ ክፍያ ይፈጽማል። 
ዲፕሎማ ወይም የቴክኒክና ሙያ ዲፕሎማ ያላቸው አመራሮች ዲግሪ እንዲማሩ ውሳኔ ማሳለፉ የአቅም ግንባታ ለመፍጠር በጎ ጅማሮ ቢሆንም ከመጀመሪያው ለምን ሕግን በተከተለ አግባብ ቅጥር አልተፈፀመም? በማለት ሕብረተሰቡ በከንቲባው ጽሕፈት ቤት ላይ ቅሬታ ማቅረቡን ሰንደቅ ዘግቧል።

No comments: