Monday, February 29, 2016

«አዲሱ የትራፊክ መቀጫ ህግ ትግበራ የሚጀመርበት ጊዜ ተራዘመ»

በተደጋጋሚ የትራፊክ ደንብ የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችን መረጃ በመያዝ እስከ መንጃ ፈቃድ እገዳ የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለው መመሪያ ተግባራዊ የሚደረግበትጊዜ ለሶስት ወራት መራዘሙን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።
መመሪያውን ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረ ቢሆንም፥ የአዲስ አበባ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት በጠየቁት ጥያቄ መሰረት ነው የህጉን ተፈፃሚነት ለማራዘም ያስፈለገው።
ማህበራቱ ስለ መቀጣጫ ህጉ አፈፃፀም በታክሲ አሽከርካሪዎች ዘንድ የጠለቀ ግንዛቤ ስላልተፈጠረበት ይራዘምልን የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለማርያም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
ጥያቄያቸውም በባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ተቀባይነት በማግኘቱ ህጉ ተፈፃሚ እንዳይሆን ለሶስት ወራት ያህል መራዘሙን ነው አቶ ካሳሁን የተናገሩት።
በቀጣዮቹ ሶሰት ወራትም በተለያዩ መንገዶች የመቀጣጫ ህጉን በተመለከተ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ይሰራል ብለዋል።
ቀድሞውንም ቢሆን ህጉ ተግባር ላይ መዋል የጀመረው የትራፊክ አደጋ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ግምት ወስጥ ገብቶ ነው ያሉት አቶ ካሳሁን፥ አሁንም ከሶስት ወራት በኋላ ህጉ ዳግም ተፈፃሚ መሆን እንደሚጀምር ተናግረዋል።
በደንብ 208/2003 መሰረት መመሪያው በተደጋጋሚ የትራፊክ ደንብ የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችን መረጃ (ሪከርድ) በመያዝ እስከ መንጃ ፈቃድ እገዳ የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ነው።
የትራፊክ የደንብ ጥሰቶቹ 1 እስከ 6 የጥፋት እርከን በማካተት ተግባራዊ የሚደረጉ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት በአንደኛ የጥፋት ደረጃ 80 ብር የሚያስቀጡ የትራፊክ ደንብ ጥሰት የሚፈፀም አሽከርካሪ 2 ነጥብ ሪከርድ ይያዝበታል። 100 ብር የሚያስቀጡ የደንብ መተላለፎች ደግሞ 3 ነጥብ ሪከርድ እንዲኖር ያደርጋሉ።
3 የጥፋት እርከን 120 ብር የሚያሰቀጡ የደንብ ጥሰት ሲሆኑ 4 ነጥብ ሪከርድ ይኖራቸዋል። ባለፈው 2007 ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ በላይ ሲሆኑ፥ እስከ 20 ሺህ በሚደርሱት ደግሞ ቀላልና ከባድ የመቁሰል አደጋ አጋጥሟቸዋል።
ምንጭ፦ FBC

No comments: