*ጋዜጠኛ ጌታቸው ጨለማ ቤት ታስሯል
በሽብር ተጠርጥረው በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል በእስር ላይ የሚገኙት የኦፌኮ አመራሮች እነ በቀለ ገርባ እና ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው የ28 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ዛሬ የካቲት 11/2008 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት የቀረቡት የኦፌኮ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በቀለ ገርባ እና በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሌሎች የፓርቲው አባላት፣ እንዲሁም ታህሳስ 15/2008 ዓ.ም ለእስር የተዳረገው የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው እና የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው አቶ ዳንኤል ተስፋየ ፖሊስ ምርመራየን አልጨረስኩም በሚል የጠየቀባቸው የ28 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተፈቅዶለታል፡፡
የጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን ከችሎቱ በኋላ እንደገለጹት ፖሊስ ‹‹ግብረ አበር መያዝ ይቀረኛል፣ ምስክር አላደራጀሁም…›› የሚል ካለፈው ጋር ተመሳሳይ ምክንያት በመስጠት ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡ ደንበኛቸው ከታሰረ ጀምሮ አንድም ቀን አግኝተው ለማነጋገር እንዳልተፈቀደላቸው ለችሎት የገለጹት ጠበቃ አምሃ፣ ጌታቸው ጠበቃውን ሳያነጋግር ቃሉን ለፖሊስ ለመስጠት ፍቃደኛ እንዳልሆነ ፍርድ ቤቱ እንዲገነዘብላቸው በድጋሜ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው በበኩሉ ያለፉትን 28 የምርመራ ቀናት የተጠየቀው ነገር እንደሌለ፣ ነገር ግን በጨለማ ቤት እንዳሰሩት ለችሎት ገልጹዋል፡፡
በተመሳሳይ የምርመራ መዝገብ የሚገኙት አቶ ዳንኤል ተስፋየ እና አቶ ሸዋታጠቅ ኃ/መስቀል በበኩላቸው ቤተሰቦቻቸው እንዲጠይቋቸው እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ችሎት የቀረቡት እነ በቀለ ገርባም እንዲሁ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸው 28 ቀናት ተፈቅዶለታል፡፡ የዛሬውን የችሎት ውሎ ለመከታተል የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦችና ወዳጆቻቸው ፍርድ ቤት ግቢ ቢገኙም ችሎቱ ዝግ በመደረጉ አንድም ሰው መከታተል እንዳልቻለ ታውቋል፡፡
Source: ነገረ ኢትዮጵያ
No comments:
Post a Comment