Thursday, February 4, 2016

የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ይዘው አዲስ አበባ የገቡ 14 የኮሜቴ አባላት ታሰሩ

ኢሳት (ጥር 24 2008)
የወልቃይት ህዝብን የመብት ጥያቄ በመያዝ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት አቤቱታ ለማቅረብ አዲስ አበባ የገቡት 14 የኮሚቴ አባላት ረቡዕ ዕለት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታወቋል። የወልቃይት ህዝብ አማራ በመሆኑ በአማራ ክልል እንካለል በማለት ጥያቄውን ያቀረቡት የኮሚቴ አባላት ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤት ብለው ሲወጡ መያዛቸው ታውቋል።
በሰሜን አሜሪካ የወልቃይት ህዝብ ተማጋች የሆኑት አቶ ቻላቸው አባይ ለኢሳት እንደተናገሩት 14 የኮሚቴ አባላት በመንግስት የጸጥታ ሃይላት ከተያዙ በኋላ የደረሱበት አልታወቀም።
ኢህአዴግ ወደስልጣን መምጣቱን ተከትሎ ከጎንደር ክፍለ ሃገር ተወስዶ ወደ ትግራይ ክልል የተጠቃለለው የወልቃይት አካባቢ ላለፉት 25 አመታት ሲያወዛግብ የቀጠለ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጥያቄው እየጠነከረና በሃገር ቤት ያሉ ተወላጆችንም በከፍተኛ ደረጃ እያንቀሳቀሰ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
የወልቃይት ተወላጆችን እንቅስቃሴ ለመግታት የትግራይ ክልላዊ መንግስት ሲያሳስብ የቆየ ሲሆን፣ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት እርምጃ እንወስዳለን ባሉ ማግስት እርሳቸው በማይቆጣጠሩት አዲስ አበባ የኮሚቴ አባላቱ መታሰር አነጋጋሪ ሆኗል። ሰዎቹ የታሰሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ አልታወቀም።


No comments: