Friday, April 22, 2016

በጋምቤላ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ኢትዮጵያውያን ተገደሉ

ሚያዚያ ፲፬(አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ትናንት ፣ ሚያዚያ13፣ 2008 ዓም አንድ ኢትዮጵያዊ ሹፌር፣ ከጋምቤላ ከተማ በ 13 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው በጃዊ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ሁለት የደቡብ ሱዳን የኑዌር ተወላጆችን ገጭቶ መግደሉን ተከትሎ፣ ስደተኞቹ በቀን ስራ ላይ ተሰማርተው በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ እስካሁን በትንሹ 13 ሰዎች ተገድለዋል፤ ነዋሪዎች በበኩላቸው የሟቾች ቁጥር ከ20 በላይ ነው ይላሉ። 10 ሰዎች ክፉኛ መቁሰላቸው የታወቀ ሲሆን፣ በተለይ ወደ ጫካ የተሰደዱት ዜጎች ሁኔታ ሲታወቅ፣ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊደርስ ይችላል ተብሎ ተፈርቷል። ከተገደሉት መካከል በየተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችም ይገኙበታል። መንግስትም ሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን የሰጡት መግለጫ የለም።
ከሟቾቹ መካከል 4 አስከሬን ወደ ወልቂጤ እና ወሊሶ ሲጓጓዝ፣ የሌሎቹን ማንነት እስካሁን ለመለየት አለመቻሉን ነዋሪዎች አክለው ተናግረዋል።ካለው ጥበቃ አንጻር ወደ ሆስፒታል ገብቶ ለማጣራት መኩራ ቢያደርግም እንዳልተሳካለት የገለጸው ወኪላችን፣ በሆስፒታሉ አካባቢ ዘመዶቻቸውን ፍለጋ ላይ ታች የሚሉ ሰዎችን መመልከቱን ገልጿል።
በካምፑ ውስጥ የሚገኙት የደቡብ ሱዳን የኑዌር ተወላጆች፣ በኢትዮጵያ ኑዌሮች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ሲያወግዙ መሰንበታቸውን የሚገልጸው ወኪላችን፣ መንግስት የኑዌር ጎሳ አባላትን የጦር መሳሪያ ባይቀማ ኖሮ ይህ ሁሉ ጉዳት ሊደርስ አይችልም ነበር ብለው እንደሚያምኑ እና አሁን የመኪና አደጋውን ሰበብ አድርገው የወሰዱት እርምጃ ፣ በቀላቸውን በኢህአዴግ መንግስት ላይ የተወጡ ስለመሰላቸው ሊሆን ይችላል ብሎአል፡፡
በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ በክልሉ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የደህንነት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ቢጠይቁም፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት ራሳችሁን ተከላከሉ፣ የሚል መልስ እንደሰጡዋቸው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ አባላት በኑዌር ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸሙትን አሰቃቂ ግድያ እና ጠለፋ ተከትሎ፣ የህወሃት ልሳን የሆነው ሬዲዮ ፋና ፣ መንግስት ደቡብ ሱዳን ውስጥ በመግባት የጎሳውን አባላት መክበቡንና ህጻናቱና ሴቶች ያለቡት ቦታም መታወቁን መዘገቡን ተከትሎ የአለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ዜናውን ተቀባብለው ቢያሰራጩትም፣ እስካሁን ድረስ የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩ “ ለምን?” የሚል ጥያቄ አስነስቷል። በተለይ የኢህአዴግ መንግስት ተሽቀዳድሞ የደቡብ ሱዳን መንግስትም ሆነ አማጺዎች ከጥቃቱ ጀርባ እጃቸው የለበትም በማለት የሰጠው መግለጫ ፣ ዘግይቶ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ከሚሰጡት መግለጫ ጋር የመጣረስ ሆኗል።
በደቡብ ሱዳን መንግስት ጦር ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ የሆኑት የሙርሌ ጎሳ ተወላጅ የሆኑት ሌተናንት ጄኔራል ዳቪድ ያው ያው እንደተናገሩት ፣ ጥቃቱን የፈጸሙት ሃይሎች በቦማ ግዛት አስተዳዳሪ በሆኑት ባማ ሜዳን የተደራጁና የታጠቁ ናቸው። ጄኔራሉ ከጥቃቱ ጀርባ የግዛቱ አስተዳዳሪ እጅ እንዳለበት ተጨባጭ መረጃ እንደደረሳቸው ገልጸው፣ ጥቃቱን የፈጸሙት ልካንጎሌ ግዛት ውስጥ የሚገኙ የእርሳቸው የጎሳ አባላት መሆናቸውንና አካባቢው የአሁኑ የጎማ አስተዳዳሪ የትውልድ ቦታ መሆኑን አስረድተዋል።
እርሳቸው የሚመሩት ኮብራ የሚባለው ጦር እጁ እንደሌለበት የገለጹት ጄኔራሉ፣ በተቃራኒው የደቡብ ሱዳንን መንግስትን መወንጀላቸውን ሱዳን ትሪቢውን ዘግቧል። ቀደም ብሎ በተሰራጨ ዘገባ የቦማ ግዛት አስተዳዳሪ ጥቃቱን በጄ/ል ያው ያው የሚመራው ጦር ፈጽሞታል ብለው እንደሚያስቡ ገለጸው ነበር።
የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት እርስ በርስ መወነጃጀላቸው ከጥቃቱ ጀርባ ፖለቲካዊ ይዘት ሊኖረው እንደሚችል ተገምቷል።

No comments: