Tuesday, April 19, 2016

እኔ አንድ ሃሳብ አለኝ

ሁላችን በያለንበት አንድ እንሁን፣ አንድ እንሁን፣ አንድ እንሁን ማለታችን አልቀረም። ታዲያ የዚህ አንድነት መሠረቱ ምንድን ነው? ለምን? እንዴት የሚለውን እንየውና፤ አንድም ድርጅቶች አምነውበት ቢሰባሰቡ፤ አለያም በግለሰብ ደረጃ ተሰባሰበን ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ነው።
ለኔ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ወገንተኛ አምባገነን መንግሥት ሀገራችንን ወደ ባሰ አዘቅት ከመጣሉ በፊት፤ ራሱ ወደ አዘቅት መጣል ያለበት መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። እንግዲያውስ በምን መንገድ? የሚለው ነው ቀጣዩ ጥያቄ። በዚህ ልውውጥ የምትሳተፉት ግለሰቦች፤ በአንድ መንገድ ወይንም በሌላ፤ በየድርጅቶች ውስጥ አባል ሆናችሁ ለሀገራችሁ የወደፊት ጥሩነት እየጣራችሁ ነው። ግለሰቦችም እንዲሁ! እስኪ መደበኛ መሥመር ተከትዬ፤ ጥሪዬን ለሁላችሁ ላቅርብ። ምን አልባት በየድርጅቶቻችሁ ትመካከሩበት ይሆናል። ባሁኑ ሰዓት አማራጮቹን ሁሉ ማየቱ አይጎዳም። እናም፤
ይድረስ፤  ለተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊያን በያላችሁበት፤
በዚህና በሌሎች የኢሜል ልውውጦች የሀገራችሁን ጉዳይ በመከታተል ያላችሁት ተቆርቋሪዎች በመሆናችሁ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሀቅ፤ ማንኛችንም ለማናችንም የምናስረዳበት ወቅት ላይ አይደለም ያለነው። ነገር ግን ሁላችንም የምንፈልገውን በግልፅ አውጥተን በመወያየት መፍትሔ አለማግኘታችን ሀቅ ነው። ዝቅተኛ የመሰባሰቢያ የትግል ዕሴቶችን በማቅረብ፤ ትግሉን ወደፊት ማራመድ ግዴታችን ነው። ያልተሞከረና ያልተጣረበት መንገድ አለ የሚል እምነት ባይኖረኝም፤ ግዴታ መሰባሰቢያ መንገድ ፈልጎ የታጋዩን ወገን ወደ አንድ ማምጣት እንዳለብን ሁላችን አናምናለን። ታዲያ ለዚህ ይረዳ ዘንድ ይኼን አቅርቤያለሁ።
ትግሉ እየተካሄደ ያለው በሀገራችን ውስጥ ነው። ይህ ማለት በውጭ ያለ ድርጅት የትግሉን ወሳኝነት መያዝ የለበትም ማለቴ አይደለም። የትግሉ የበላይነት የሕዝቡ ሲሆን፤ እንደየአደረጃጀቱ ደግሞ፤ ከሕዝቡ ጎን በመቆም፤ መሪውን አብሮ የሚጨብጥ ድርጅት የትም ሊገኝ ይችላል። ይህ ደግሞ በሕዝቡ ምርጫ ሲሆን ነው። የሀገራችን ተጨባጭ ሀቅ ግን አሁን የሕዝቡ ሉዓላዊነት ያልተከሰተበት በመሆኑ፣ ትግሉ ያንን ለማስገኘት ነውና፤ በድርጅቶች መካከል ያለው እሽቅድድም፤ ትግሉን ከመጎተቱ በስተቀር፤ ዋጋ የለውም። ይልቁንስ ይኼን በደንብ ደቁሰን ተረድተን፤ ወደፊት የሚያስኬደንን መንገድ መምረጥ አዋቂነት ነው። ከድርጅቶች ውጪ ሆነን በውጪ ሀገር የምንገኝና ትግሉን ልንረዳ የምንፈልግ ኢትዮጵያዊ ግለሰቦች፤ አንድ ምርጫ አለን። ይኼውም በአንድነት ከታጋዩ ወገን መሠለፍ ነው። ይኼን ለማድረግ ደግሞ በአንድነት እንድንሠለፍበት የምንመርጥበን ምክንያት ለይተን ማወቅ አለብን።
ኢትዮያዊነታችንን የተቀበልንና የሕዝቡን ትግል የምንደግፍ ሁሉ፤ ተከታዩ የምንፈልገው ሥርዓት ለምናደርገው ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ምን እንፈልጋለን። በያዝነው የአደረጃጀት ተሳትፎ፤ ሥልጣን መያዝ ወይንም አንድን ርዕዩተ ዓለም የማራመድ ጉዳይ ቦታ የለውም። ቦታ ያለው፤ ሀገራችን ከዚህ ወራሪ ከመሰለ አስተዳደር ነፃ ወጥታ፣
ሀ) ሕዝቡ ሉዓላዊነቱ ተከብሮለት፣
ለ) የሀገራችን አንድነት ተጠብቆ፣
ሐ) የሕግ የበላይነት ሠፍኖና፤
መ) የእያንዳንዱ/ዷ ኢትዮጵያዊ/ት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው፤ የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ነው።
እኒህ አራት የትግል እሴቶች ሁሉም የታጋይ ክፍል የሚጋሩት ስለሆነ፤ በነዚህ ዙርያ መሰባሰቡ ወደ አንድ ያመጣናል። እናም እነኚህን የተቀበለ/ች ማንም ኢትዮጵያዊ/ት፤ በኢትዮጵያዊነቱ/ቷ መሰባሰቡ ትግሉን ወደፊት እንዲሄድ ያደርጋል። እዚህ ላይ መሠመር ያለበት፤ ይሄ ስብስብ የግለሰብ ኢትዮጵያዊያን ስብስብ መሆኑ ነው። እናም የድርጅቶች ስብስብ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች ስብስብ ነው። ይህ ጠቃሚነቱ ብዙ ነው።
፩ኛ.      የሕዝቡን የበላይነት ይቀበላል።
፪ኛ.      መላ ኢትዮጵያዊያንን ያሰባስባል።
፫ኛ.      አንድ የትግል ማዕከል በመፍጠሩ፤ የሰው ኃይልን ወደ አንድ ጎራ ያመጣል።
፬ኛ.      የቁሳቁስ ክምችትን ያዳብራል።
፭ኛ.      ለሕዝቡ አማራጭ ሆኖ ይቀርባልና የሕዝቡን ተስፋ ያሳድጋል።
መቀጠል እችላለሁ ነገር ግን ይኼን ስለማታጡት አቆማለሁ። የኢትዮጵያዊያ ሕዝብ ለትግሉ ከድርጅቶች ቀድሞ የተሠለፈ ለመሆኑ ጥያቄ የሚያቀርብ የለም። ነገር ግን፤ አስተማማኝ ምርጫ ሳይኖረው የተበታተነን ታጋይ ክፍል ምረጥ ቢሉት በጄ አይልም። አንድ ሆነን ከተገኘን ግን፤ ሕዝቡ እኛን ያስተምረናል። እስኪ የተሰማችሁን ወርውሩ።
ከታላቅ አክብሮት ጋር
አንዱ ዓለም ተፈራ


No comments: