Thursday, April 17, 2014

መንግሥት የሕዝቡን ጩኸት መስማት ግድ ይለዋ፡፡!

መንግሥት የሕዝቡን ጩኸት መስማት ግድ ይለዋ፡፡!

የአክሲዮን ማኅበራትን በማደራጀት ሰበብ የተሰበሰበውን የሕዝብ ሀብት አስመልክቶ ለበርካታ ጊዜያት ለንባብ በቅተው የነበሩት የሕዝብ አቤቱታዎች ዛሬም ምላሽ ሲያገኙ አይታዩም፡፡ ለእነዚያ ብሶቶችና አቤቱታዎች የመንግሥት ምላሽ የዘገየ መሆን ሕዝቡ የሕግ ጥበቃና ከለላ ማግኘት አልቻልኩም በሚል ቅሬታ እንዳያድርበት መንግሥትን ሊያሳስበው ይገባል፡፡
በዚህ አኳኋን ስለተፈጸሙ ድርጊቶች ከኢኮኖሚያዊ አሉታዎችና ተፅዕኖዎች ባሻገር በባህላዊና ቁሳዊ ማንነት ላይ ስለጣሉት ጠባሳ መገምገም ተገቢ ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ችግሮቹን ለመፍታት አለመቻል አንዱ ችግር ሲሆን፣ በሌላ በኩል ግን በሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ እየተመላለሰ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱ ባሻገር ድርጊቱ ለአገራዊ ልማታዊ አስተሳሰብ ነቀርሳ መሆኑ ታውቆ አግባብ የሕግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አያጠያይቅም፡፡
የአክሲዮን ማኅበራትን በማደራጀት ስም የተሰበሰበው በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ሀብት ጥቂት ጮሌዎች በአቋራጭ ብልፅግና ላልተገባ ጥምቅ እያዋሉት ስለመገኘታቸው ሲታሰብና ዝርፊያውም መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር ላይ የተፈጸመ መሆኑ ሲታወስ፣ የተጎጂዎች ቁጣ በዘራፊዎች ላይ ከመሆን ባለፈ በመንግሥት ላይ ኩርፊያ ሊያስከትል እንደሚችል ነባራዊ እውነታዎቹ እያሳዩን ነው፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው ደግሞ የሕዝብን ቅሬታ የሚሰማ አካል የመታጣቱ ጉዳይ ነው፡፡ በዘረፋው ሒደት ውስጥ የነበሩ እውነታዎችም ይህንኑ ያመለክታሉ፡፡ በልማታዊ አስተሳሰብ ስም የተፈጸሙ የኪራይ ሰብሳቢዎች የአቋራጭ ብልፅግና ንድፎች እንደነበሩ ለማሳየት ጥናታዊ ጽሑፎችን ማጣቀስ ግድ አይልም፡፡
በአገራችን የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት የፈጠረውና ሕዝቡ በኢኮኖሚው ላይ የተቀዳጀውን የሞራልና የመንፈስ ድል በመጥለፍ ለግል ርካሽ ተልዕኮ የማዋል እኩይ ተግባር እየተስፋፋ ነው፡፡ አገራችን በፈጠነ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ መገኘትዋንና ይህንን የኢኮኖሚ ዕድገት ለሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ መነሳሳት ምክንያት መሆኑን የተረዱ የአቋራጭ ብዕግፅና ጥቅመኞች፣ የተነሳሳውን የሕዝቡን መንፈስ ምናባዊ የፕሮጀክት ሐሳቦችን እያሳዩ የሕዝብ ሀብት መንጠቃቸው ሲታሰብ፣ ድርጊቱ በግለሰቦች አማካይነት ንዋይ ለመዝረፍ የተወጠነ ስትራቴጂ ከመሆን ባለፈ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ላይ የተፈጠረ ደባ እንደሆነ ለማወቅ አስረጂ አያስፈልገውም፡፡
አደራጆች በአክሲዮን ሽያጭ ወቅት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ጠንካራና ዓማላይ ቃላቶች ፋይዳቸው አክሲዮኖችን በመሸጥ ጠቀም ያለ ገንዘብ ከማግኘት ያለፈ እንዳልነበር በቆይታችን የታዘብነውና ያየነው ነገር ምስክር ነው፡፡
ለሕዝቡ ጩኸት ሕጋዊ ዋስትና ሊያሰጥ የሚችል አካል ብቅ አለማለቱ ለዘራፊዎች ትዕቢት ጥንካሬ ከመሆን ባለፈ የአክሲዮን አደራጆች ላይ ተስፋ መቁረጥን አስከትሏል፡፡
ባልተገባ የአበልና የደመወዝ ክፍያዎች ዘረፋ፣
በሽያጭ ስም ለሚወሰዱ እጅግ የተጋነኑ ኮሚሽኖች፣
በግዥ ስም ለሚወሰዱ የኮሚሽን ዘረፋዎች፣
የተሰበሰበውን ገንዘብ ለሌላ የግል ጥቅም የማዋል ሕገወጥ ተግባራት፣
ለዘመድ አዝማድ ያልተገባ የሥራ ዕድል ባልተገባ ክፍያ ማመቻቸት፣
የንግድ ልውውጡን ግላዊ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባላቸው ፋይዳ ብቻ እንዲታዩ በማድረግ ሕገወጥ ተጠቃሚነትን መከተል፣
የድርጅቱን ስምና ዝና ለግል መጠቀሚያ ማድረግ ከሚታዩ ሕገወጥ ተግባራት በምሳሌነት የሚጠቀሱና ሕዝቡ የተቸገረባቸው ድርጊቶች ናቸው፡፡
ወላጆች ለልጆቻቸው ሕክምና ዋስትናና ለሌላ መጠባበቂያ የደበቁትን ሀብት፣ የሰሙትን በማመንና ተስፋ በማድረግ አክሲዮን ቢገዙም ማለቂያ በሌላቸው ምክንያቶች ገንዘቡ እየተበላ ትርፉ ቀርቶ ያዋጡትን ገንዘብ ዋናውን ማግኘት የሚችሉበትን ጊዜ ይናፍቃሉ፡፡
ውንብድናውን የሚያካሒዱት የሕዝብ ሚዲያ በመንተራስ፣ የሕጋዊነት ሽፋን ተላብሰው የታዋቂ ሰዎችን ስምና ምሥል በመጠቀም ስለሆነ የችግሩን ጥልቀትና ስፋት
አባብሰውታል፡፡ የመንግሥት መጠቃሚያ በሆኑ ሚዲያዎች ሕዝቡ ውሸት ይስተናገዳል ብሎ ስለማያስብ በቀላሉ ለመታለል ተመቻችቷል፡፡ ሚዲያውን፣ የታዋቂ ሰዎችንና የአገር ሽማግሌዎችን ስም ለግል እኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያነት ያውላሉ ብሎ የሚገምት ባለመኖሩ ችግሩ ተባብሷል፡፡
Nati Man

No comments: