Friday, July 11, 2014

አንድነትና መኢአድ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የትግል ጥሪ በማቅረብ የመንግስትን እርምጃ አወገዙ

በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /ቤት ዛሬ አንድነትና መኢአድ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአንድነት የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ የሆነው የአቶ ሐብታሙ አያሌው፣የድርጅት ጉዳይ ምክትል አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣የአረና የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ አቶ አብርሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት ምክትል ሃላፊ የሆነው አቶ የሺዋስ አሰፋ መታሰርንና እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን፣በጠበቃቸውና በወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲጎበኙ አለመደረጋቸውን በጽኑ ተቃውመዋል፡፡ 
ሰሞነኛውን የእስር እርምጃ የተቀነባበረ የስርዓቱ ድራማ መሆኑን በመግለጫቸው ያጋለጡት ፓርቲዎቹ ‹‹እስሩ ቀጣዩን መት አገር ዓቀፍ ምርጫ በተለመደው ማሸማቀቅና ማወናበድ ለመውሰድ የተጀመረ የመጀመሪያ እርምጃ ነው ››ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡
በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ ፓርቲዎችም ይህን ህገ ወጥ እስር በማውገዝና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚደረገውን ሩጫ በመቃወም እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲቆሙና በጋራ እንዲሰሩ ሀገራዊና ወቅታዊ ጥሪ ማቅረባቸውን ሁለቱ ፓርቲዎች አስታውቀዋል፡፡
የሲቪክ ተቋማት፣ነጻው ሚዲያና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶችም መንግስት በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን መንግስታዊ ግፍና በደል በዓለም አቀፍ ደረጃ በማጋለጥ ግዴታቸውን እንዲወጡ መግለጫውን የሰጡት ፓርቲዎች ጠይቀዋል፡፡

No comments: