Tuesday, May 13, 2014

‎የነፃ ፕሬስ አሳታሚዎች አስቸኳይ ስብሰባ‬

(በወሰንሰገድ ገብረኪዳን)

የነፃ ፕሬስ አሳታሚዎች ለመንግስት ያቀረቡት የማህበር ምስረታ ጥያቄ ከ2 ዓመት ውጣውረድ በኋላ ዓም ምላሽ አገኘ፡፡ አሳታሚዎቹ የመሰረቱት ማህበር “ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማህበር” በሚል ስያሜ ከመንግስት የህጋዊነት ፍቃድ ሰርተፍኬት የተሰጣቸው ግንቦት 1 ቀን 2006 ዓም ነው፡፡
ማህበሩ ህጋዊ ፍቃድ (ሰርተፍኬት) ባገኘ በአራተኛው ቀን ፤ ማለትም ዛሬ ግንቦት 5 ቀን 2006 ዓም አባላቱን አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱም ታውቋል፡፡ የነፃ ፕሬስ አሳታሚዎች ማህበር አባላቱን ዛሬ “በአዲስ አድማስ” ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት “የማተሚያ ማሽን ተበላሽቶብኛል” በማለቱ ጋዜጦች ከሕትመት ውጪ መሆናቸው ክፉኛ ያሳሰበው በመሆኑ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ለአንባቢያን መቅረብ የነበረባቸው “ሪፖርተር”፣ ፎርቹን እና ካፒታል ጋዜጦች ለሕትመት ባለመብቃታቸው አንባቢያን እጅ መድረስ አልቻሉም፡፡
በመንግስት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪነት የሚተዳደደረው አንጋፋው ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት “ማሽን ተበላሽቶብኛል” ባለ ቁጥር የነፃ ፕሬስ ውጤቶች አንባቢያን እጅ እንዳይደርስ መደረጉ አግባብ አይደለም፤ የሕዝብን መረጃ የማግኘት ሕገመንግስታዊ መብት የሚጥስ ነው ብለዋል1- አሳታሚዎቹ፡፡ በመንግስት የሚተዳደር ተቋም የማተሚያ ማሸን “ብልሽቱን” መፍታት ወይም አዲስ የማተሚያ ማሽን በመግዛት ሲችል፤ የሕዝብ የማወቅ መብት በማተሚያ ማሽን ብልሽት ሰበብ ፈፅሞ ሊነፈግ አይገባም ፤ ስለዚህም መንግስት ልዩ አካል አቋቁሞ ጉዳዩን አጣርቶ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጠን ብለዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ሐዝብ መረጃ የማግኘት ሕገመንግስታዊ መብት አለው፤ ይህ መብት በሕገመንግስቱ አንቀፅ 29 በግልፅ ተደንግጎ ሳለ፤ ማሽን ተበላሽቷል በሚል ሰበብ ስለሃገሩ መረጃ እንዳያገኝ መደረግ የለበትም፤ የነፃ ፕሬስ ውጤቶች በዚህ መሰል ተልካሻ ምክንያት ከሕትመት ውጪ መሆናቸው፤ በአሳታሚዎቹ ሕልውና ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አደጋ ይጋርጣል፤ ዜጎች በሚዲያ ስራ ላይ የመሰማራት መብታቸውን የሚገፍ ነውና መንግስት አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጠን እንሻለን የሚል አቋም እንደያዙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አሳታሚዎቹ እነዚህንና ሌሎች አቋሞቻቸውን የያዘ ሕጋዊ ደብዳቤ ለጠ/ሚ/ሩ ቢሮ፣ ለፓርላማ፤ ለፌዴሬሸን ምክርቤት፣ ለብሮድካስት ኤጀንሲ እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲላክ ተስማምተው ስብሰባቸውን አጠናቀዋል፡፡
የግል አሳታሚዎች ማሕበር ሲመሰረት ፤ የግል ፕሬስ ውጤቶች የሚታተሙበት ማተሚያ ቤት ማቋቋም ከዓላማዎቹ መሃል አንደኛው ጉዳይ መሆኑን ከዚህ ቀደም መገለፁ ይታወሳል፡፡
http://ethioforum.org

No comments: