Thursday, March 6, 2014

ኤፈርት ዜጎችን የማፈናቀል ተግባሩ ቀጥሎበታል

ኤፈርት ዜጎችን የማፈናቀል ተግባሩ ቀጥሎበታል – አብርሃ ደስታ

በህወሓታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ መሰረት ስልጣን ለመያዝና በስልጣን ለመቆየት ገዢውን መደብ ሁሉም ነገር መቆጣጠር አለበት። በዚሁ መሰረት ማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በኤፈርት (ትእምት) ሥር መሆን አለበት። ኤፈርትም (ትእምት) በህወሓት መሪዎች ሥር መሆን አለበት። እንደዉጤቱም በትግራይ ክልል ጥሩ ገቢ ሊያስገኙ በሚችሉ ዘርፎች ላይ የግል ባለሃብቶች እንዲሳተፉ አይፈቀድም። ጥሩ ቢዝነስ የሚሰራበት ከሆነ ለኤፈርት፣ ለህወሓቶች ነው።
በዚሁ መሰረት በትግራይ የግል ባለሃብቶች በማዕድን ቁፋሮ (በተለይ ወርቅ) መሰማራት አይችሉም። በባህላዊ መንገድ ወርቅ ከሚለቅሙ ግለሰቦች ዉጭ (እነሱም ሕጋዊ አይደሉም እየተባለ ይያዛሉ) ማንኛውም የግል ኩባንያ በወርቅ ቁፋሮ መሰማራት አይፈቀድለትም። ምክንያቱም ወርቅኮ ነው!
ስለዚህ በትግራይ ክልል ያለው የወርቅ ማዕድን ቁፋሮ የሚከናወነው በትእምት (ኤፈርት) ነው። ለዚሁ የወርቅ ማዕድን ቁፋሮ እንዲያከናውን የተፈቀደለት “ኢዛና” የማዕድን ቁፋሮ ፋብሪካ ነው። ኢዛና የማዕድን ቁፋሮ ፋብሪካ የኤፈርት ኩባንያ ነው። ይህ የትእምት ኩባንያ በሰሜናዊ ምዕራብ ትግራይ፣ አስገደ ፅምብላ ወረዳ (ደደቢት የሚገኝበት ቦታ ነው) የማዕድን ቁፋሮ ለማካሄድ በመፈለጉ ምክንያት ባከባቢው የሚገኙ አርሶአደሮች ቀያቸው ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል።
በአስገደ ፅምብላ ወረዳ ዕዳጋ ሕብረትና ልምዓት በተባሉ ጣብያዎች (ንኡስ ወረዳዎች) የሚኖሩ 320 አባወራዎች መሬታቸው ለኤፈርት በማስረከብ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ተፈርዶባቸዋል። አርሶአደሮቹ ከቀያቸው ሲፈናቀሉ ምንም ዓይነት ካሣ ወይ ተለዋጭ መሬት አይሰጣቸውም። በዚሁ ምክንያት አርሶአደሮቹ ከፍተኛ ቅሬታ እያሰሙ ቢሆንም ሰሚ አላገኙም። እንዴት ከኤፈርት ጋር ይከራከራሉ? ምስ ደጃዝማቲ መን ተሟጋቲ?!
በተያያዘ ዜና በአስገደ ፅምብላ ወረዳ ከ1000 በላይ መኖርያ ቤቶች እንዲፈርሱ ተወስኗል። እስካሁን በደብረማርያም ጣብያ፣ ኮር ተኽሊ በተባለ ቁሸት 200 መኖርያቤቶች በመንግስት ሃይሎች መፍረሳቸው ኗሪዎቹ በስልክ ገልፀውልኛል።

No comments: