Tuesday, March 4, 2014

የገዢዎቻችን መጨረሻና የተከተላቸው ሀቅ

የገዢዎቻችን መጨረሻና የተከተላቸው ሀቅ
አንዱ ዓለም ተፈራ
የእስከመቼ አዘጋጅ
የካቲት ፳፫ ቀን ፳፻፮ ዓመተ ምህረት
የመጨረሻውን በማያውቁት ያዘቀዘቀ ጨለማ መንገድ እየተውዘረዘጉ መሪዉን በማስተካከል ከመጨረሻው ለመድረስ የሚጣድፉ መሪዎች፤ የድንቁርና ኒሻን ይገባቸዋል። በፈጠሩት የራሳቸው የመኖሪያ የገዢነት መኮፈሻ “ሀቅ” ተጀንነው በመቀመጥ፤ ፈንጠር ብሎ ርቆ ሌላውን ማየት ባለመቻላቸው፤ የተከተላቸውውን ሳይውቁት እጃቸውን ሠጥተዋል። የተለዬ የመሰለ የራስ “ሀቅ” የብዥታ ጭጋግ፤ ሩቅ ማየትን ነፈጋቸው። ማስተዋልን ከአእምሮ መዝገባቸ ሰወረው። መደናበርን አነገሠባቸው። ካይናቸው ፈት በተገተረው የእብሪታቸው መነፅር ዓለምን ግቢ ውጪ እያሉ በማስገደድ፤ ያለው የሌለ ሆኖ፣ ከተጨባጩ ይልቅ በምኞታቸው ዓለም ሲዳክሩ፤ የቆሙበት መሬት ከዳቸው። ከሕዝቡ መሆናቸው ቀርቶ ሕዝቡ የነሱ አገልጋይ ሎሌ ሆነና፤ የነሱ መኖሪያና የሕዝቡ መኖሪያ በአጥር ተለያዬ። መኖሪያቸው ዓለማቸው ሆነና ከሕዝቡ ዓለም ወጡ። ረጋ ብለው ያሉበትን ለመመርመር ጊዜ አጠራቸው። ያጠራቸው ጊዜ ጥሏቸው ሄደ። እናም ባሉበት ቆመው ቀሩ።
መንግሥትን ለመምራት፤ ከፍተኛ ብስለትና ጥንቃቄ ታላቅ መሣሪያ ናቸው። “ጠላት” እና “ወዳጅ” ብሎ በመፈረጅ፤ ወዳጅን መጥቀምና ጠላትን መጉዳት በሚሉት ጋቢ ከተሸፈኑና በዛሬ ወንበር ከረጉ፤ ነገ የራሷን ወዳጅና ጠላት አበጅታ ከጎን ብቅ ስትል፤ የሚይዙትን ታሳጣለች። ለሁሉ ጥሩ ነገሮች ባለቤት ወዳጅ ብሎ የፈረጀውን ወገን ያቀሰሰና ለሁሉ ነገር መጥፎ ባለንብረት፤ ጠላት ብለው የፈረጀውን ሠፈር የወነጀለ ገዢ፤ መጨረሻው አያምርም። የኛ ገዢዎች እንዲያ ነበሩ፤ አሁንም እንዲያ ባይ በጀርባችን ተሸክመናል። ፍርሃትን በሕዝብ በመዝራት ለመግዛት የተነሱት ገዥዎቻችን፤ ራሳቸው በፍርሃት ተውጠው ከሕዝቡ ራቁ። ሕዝቡን ጠላት አድርገው ፈረጁት። መውደቃቸው የጊዜ ጉዳይ ሆነ።
ገዢዎች ከአመጣጣቸው ማንነታቸውን መገንዘብ ይቻላል። አንድ የተለዬ ወገን ቦድነው የመጡ ክፍሎች፤ ያንኑ ምርኩዝ ይዘው እስከመጨረሻው ሲሄዱ አየናቸው። ያ አመጣጣቸው ለተከተሉት ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያቸው መነፅራችን ነው። እናም እምነታቸውና ተግባራቸው ይኼንኑ አንፀባረቀልን። እብሪት የጉልበተኞች መመኪያ ሆነች። እብሪተኞች ዘለዓለማዊ ነን አሉ። በሥልጣን ላይ ሲሆኑ የረጋ አእምሮን መንገድ መጥረግ አቆሙ። በስሜትና በፍላጎት መብራት ጨለማውን ለማለፍ ተደናበሩ። የተፈጥሮ ሕግን ጠምዝዘው ሊዘውሩ ሞከሩ፤ ራቁታቸውን ተጋልጠው ቆማ። ንጉሡ ባሉበት ደነዘዙ፣ ደርጋማው መንግሥቱ ጭራውን ቆልፎ ሐራሬ ምሽግ ውስጥ ተደበቀ። ያሁኖቹ ደግሞ በተራቸው የት ይገቡ ይሆን?
እኔ ራሴ ባየኋቸው ሶስት የተከታተሉ ገዢዎቻችን፤ ይህ ሀቅ በጣም ጎልቶ ታይቷል።
በመጀመሪያ ንጉሠ ነገሥቱ፣ ራሳቸው በፈጠሩትና ባመኑበት “ከአምላክ የተቀባሁ ነኝ!” ባይ እብሪት፤ ሕዝቡን ለሳቸው የተሠጠ አገልጋይ በማድረግ፤ ጊዜ ሲለውጥና የዓለም ፖለቲካ መልኩን ሲቀያይር፣ ከኋላችን የነበሩትና አዲስ ነፃ የወጡ የአፍሪቃ ሀገሮች ቀድመውን ሲሄዱ፣ በሀገራችን በሚሠጠው ትምህርት የዓለምን ግስጋሴ የተገነዘበው የተማረው ክፍል የስልጣኔ ናፍቆቱ ሲያድግ፣ የዓለም ህዝብ የኑሮ ደረጃ ከፍ እያለ ሲወጣና የኛ ኑሮ ባለበት ከመዘፍዘፉ የተነሳ የኋሊት ጉዞ ሲጀምር፤ ያመኑበት መለኮታዊ ገዢነታቸው ዓይናቸውን አውሮ ማየት ተሳናቸው። እናም የግል ጠባቂ ብለው ያደራጁት የጦር ኃይል ያለበት የኑሮ ሁኔታ አላስጨነቃቸውም። ሁሉም በተዓምርና በሳቸው ምኞት ብቻ የሚመራ አድርገው ሲያዩት፤ ታሪክ ያልተገናኙ አድርጎ ከሥራቸው መሬት ካዳቸው። እናም ሲነቁ በጨለማ ተውጠው የሚጨብጡትን አጡ። ተነድተው የታሪካቸው የመጨረሻ ምሽት፤ ባልታወቀበት ቦታ ሆነ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በየካቲት ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓመተ ምህረት ባንድነት ተነስቶ የራሱን መንግሥት ለመመሥረት ሲዘጋጅ፤ ባቋራጭ የገባው የወታደሮች ቡድን አብዮቱን አኮላሸው። በሂደቱም አንድ አምበገነን ወጥቶ፤ የፈራቸውን፣ የጠላቸውን፣ በሕልሙ የሚያስበረግጉትን፣ ለሱ ሠጥ ለጥ ብለው፣ አሜን ጌታዬ ብለው ያልተገዙለትን በማሰር፣ በመግደልና በተለያዬ መንገድ በማጥፋት ሊገዛ ተነሣ። ሰዎችን እንደ ጠጠር በፈለገበት ማስቀመጥና ማዞር፣ ማሽከርከርና መጣል የዕለት ተዕለት ተግባሩ ሆነ። ራሱን ኢትዮጵያ፣ የሱን ተቃዋሚ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ፣ እሱን ያልተቀበለ ኢትዮጵያን ያልተቀበለ በማድረግ ሊገዛን ፈለገ። በመሐል ቤት ራሱ በሚያልመው መነፅር ሀገሪቱንና የሀገሪቱን የፖለቲካ ሀቅ እየተመለከተ ከህዝቡ ተለዬ። ሕዝቡ ለማያባራ ጦርነት ልጆቹን መገበር እምቢ አለ። ሕዝቡም መጥፎ ነገር እንደነካ እንጨት ራቀው። እናም ብቻውን ቀረ። ዙሪያውን ሲከበበ፤ ጅራቱን ቆልፎ እንደሚሮጥ ፈሪ ውሻ፤ እግሬ አውጪኝ ብሎ ወደ ሐራሬ ፈረጠጠ።
በቦታው የተተካው ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ደግሞ፤ ራሱን ልዩና ብቸኛ ሆኖ የተፈጠረ አዳኝ በማድረግ፤ ለሁሉም ነገር እሱ ብቻ መፍትሔ አዋቂና ራሱ ብቻ ትክክለኛ ሆኖ በመቅረብ፤ እሱም እንደቀደሙት ሁሉ፤ ሕዝቡ ገዢው የሚለውን የሚሰማ፤ ገዢው የሚያዘውን የሚፈፅም አድርጎ እየገዛ ነው። በዚህ ተግባሩ ከሕዝቡ ተነጥሎ ተንሣፏል። ቀደም ያሉ ገዢዎቻችንን ያስቆጧቸው ወገኖች በሥራቸው እንዳቆጠቆጡት ሁሉ፤ በአዲሱ ገዥዎቻችን ላይም የሕዝብ ወገን የሆኑ ተቃዋሚዎች በየቦታው ተኮልኩለዋል። አሁንም ያለበትን ሀቅ ሳይሆን፤ የሚያልመውን እየተቀበለ እውነቱን ማየት አቃተው።
ጊዜያዊ የመሰለያ አምስት ለአንድ ጥፋሮውንና ወታደራዊ ጥንካሬውን የማይበገር ምሽግ አድርጎ ወስዶታል። የሚታየውን በሀገሪቱ የሠፈነ የኅብረተሰብ ችግርና የኑሮ ሁኔታ እንዳያይ የራሱ ቅንጦትና ምቾት አውሮታል። እንደቀድሞዎቹ ራሱን ዘለዓለማዊ አድርጎ ወስዷል። እንደቀደሙትም ተራውን እየጠበቀ ነው።
ለኔ፤ የወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ ቡድን ነገ፤ ጉዳዬ አይደለም። ጉዳዬ፤ የኛ የኢትዮጵያዊያንና የሀገራችን የኢትዮጵያ ነገ ነው። እንደትናንቶቹና ዛሬ በዙፋኑ ላይ ቁጢጥ እንዳለው፤ ሌላ አምባገነን ገዢ እንዲተካ አልፈልግም። የእስከዛሬው አንገፍግፎኛል። ይህ ምን ጊዜም መረሳት የለበትም። ግፉ እንዲቀጥል በምንም ሁኔታ መንገድ አሠልጢዎች መሆን የለብንም። ታዲያ እኛ ምን ማድረግ አለብን? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። መልሱን ደግሞ ነገ ሳይሆን ዛሬ መሥጠት አለብን። እጆቻችን አጣጥፈን መጪውን መጠበቁ፤ በተዓምር ኢትዮጵያዊያን የምንፈልገውን ሀቅ እንዲከተል አያደርግልንም። እናም እኔ ኃላፊነቴን መወጣት አለብኝ። ብቻዬን የምጥረው የትም እንደማያደርስኝ አውቃለሁ። ችግሩ የሁላችን የኢትዮጵያዊያን በሙሉ ነው። መፍትሔውም በሁላችን በኢትዮጵያዊያን ጥረት የሚገኝ ነው። እናም ለርስዎና ለመሰሎችዎ ጥያቄ አለኝ።
ያሁኑ ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ሲወገድ ምን እንዲተካ ነው የሚፈልጉት?
ይህ እንዴት ሊመጣ ይችላል?
የኔና የርስዎ፤ የያንዳንዳችን አስተዋፅዖ ምንድን ነው ይላሉ?
የኔን ላጋራዎ፤
አሁን በሀገራችን ያለው ወራሪ ዓይነት ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ነው። ሀገራችንን ወደ ከፍተኛ አደጋ እየመራት ነው። የነገው የሀገራችን ዕጣ አደገኛ ሁኔታ ላይ ወድቋል። እኛ የዚህን ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መከታተላችን፤ ኢትዮጵያዊያን የምንፈልገውን ሕዝባዊ አስተዳደር አያመጣልንም። የራሳችንን ተግባር ነው መወሰን ያለብን። ሀገር አቀፍ የሆነ ሁሉን ኢትዮጵያዊያንን ያጠቃለለ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞ፤ የዴሞክራሲያዊ አሠራር መሠረቱ ሲጣል ብቻ ነው አስተማማኝ የሆነ የወደፊት የሚኖረን። ለዚህ ደግሞ ሁላችንን የሚካትት ራዕይና ተልዕኮ ሊኖረን ይገባል። ይህ መንግሥት በሕዝቡ ግፊም ሆነ ራሱ በውስጡ በመንቀዙ መውደቁ አሌ አይባልም። ጥያቄው መቼ? ብቻ ነው።
በኔ እምነት፤ ኢትዮያዊነታችንን የተቀበልንና የሕዝቡን ትግል የምንደግፍ ሁሉ፤ በመጀመሪያ ማመን ያለብን፤ የምንፈልገው ተከታይ ሥርዓት፤ ለምናደርገው ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ነው። ምን እንፈልጋለን? በአንድነት ሆነን ተሰባስበን በምናደርገው የአደረጃጀት ተሳትፎ፤ በግል ወንም በቡድን ሥልጣን መያዝ ወይንም አንድን ርዕዩተ ዓለም የማራመድ ጉዳይ ቦታ የለውም። ቦታ ያለው፤ በአንድነት ሁላችን፤ ሀገራችን ከዚህ ወራሪ ከመሰለ አስተዳደር ነፃ ወጥታ፤ ሕዝቡ የወደደውን መንግሥት ለማቋቋም መሸጋገሪያ መንገድ ማዘጋጀቱ ነው። ሕዝቡ የወደደውን ከመምረጡ በፊት የመሸጋገሪያ ወቅት አለ። እናም የኛ የትግሉ ተሳታፊነት በትግል ዕሲውቶቻችን ይመራል። እናም የትግል ዕሴቶቻችን የሚከተሉት ናቸው፤
ሀ) ሕዝቡ ሉዓላዊነቱ ተከብሮለት፣
ለ) የሀገራችን አንድነት ተጠብቆ፣
ሐ) የሕግ የበላይነት ሠፍኖና፤
መ) የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው፤
የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን የሚያመቻች የሽግግር መንግሥት መቋቋሙ ነው። እኒህ አራት የትግል ዕሴቶች ሁላችንም በታጋይ ክፍል የተሠማራነው የምንጋራው ስለሆነ፤ በነዚህ ዙርያ መሰባሰቡ ወደ አንድ ያመጣናል። እናም እነኚህን አራት የትግል ዕሴቶች የተቀበልን ኢትዮጵያዊያን፤ በኢትዮጵያዊነታችን መሰባሰባችን ግዴታ ነው።።
ታሪክ ጥሏቸው ሲጓዝ ባሉበት ቆመው የተያዙትን ገዢዎቻችንን እናጢን። ኃላፊነቱ የኛ ነው ብለን እስካልጨበጥንና ግዴታችንን እስካልተወጣን ድረስ፤ ሌሎች በሚያመጡት ለውጥ የኛን ፍላጎት እንዲሟላ እጃችንን አጣጥፈን መቀመጡ፤ በቀላሉ ጅልነት ነው። ከአፄው የከፋና የከረፋ ደርግ ተከተለ። ከደርግ የገማና የተግማማ ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ ተከተለ። የከፋ አይመጣም እያልን የተሻለ ባጠገባችን አላልፍም አለ። የሚቀጥለውስ የመዓት ነው። እኛ ካላወቅንበት! ምን ይላሉ?

No comments: