Sunday, November 15, 2015

ድህነታቸውን ተረት ያደረጉ ታጋዮች! (ታሪኩ አባዳማ)

ታሪኩ አባዳማ – ህዳር 2008
ሀብታሞች ድሀ መሆን ከፈለጉ ቀላል ነው – የለበሱትን ንፁህ ልብስ አውልቆ በቱቶ መልበስ ፣ ቤት ንብረት ለቆ መመነን እና ደጀ ሰላም ተቀምጦ መለመን። ህግ ሳይጥሱ ባንድ ቅፅበት ድሀ መሆን ይቻላል። ይህ ደርሶ አላየንም። ሀብታም መሆን ግን ይቻላል ከባድ ነው እንጂ። ሂደት አለው ፣ ደረጃ አለው ፣ እርከን አለው – ከጫካ ተንደርድሮ መጥቶ ፣ ከዜሮ እና ከባዶ ተነስቶ ፤ ከሞጋ ጫማ ፣ የተቀደደ ቁምጣ ተነስቶ ባንድ ጀምበር ሀብታም ለመሆን መቻል ጥያቄ ያስነሳል። ሎተሪ እንደወጣለት ሰው ትናንት ባዶ እጅ ዛሬ ረብጣ ቆጣሪ ሆኖ መገኘት ምንጩ ምንድነው የሚል ጥያቄ ይጋብዛል። ብር እንደ ቅጠል ከጫካ ከዛፍ አይቀጠፍም – እንቅልፍ የለሽ ትጋት ይጠይቃል።
ሀብታም ድሀ መሆን ከፈለገ ቀላል ነው – ድሀው ሀብታም ለመሆን ሲፈልግ ግን መንገዱ ሩቅ ነው። ይህ እንግዲህ ሁሉም የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠበብት የሚስማሙበት አጠቃላይ ግንዛቤ ነው።
በወያኔ ዘመን የናጠጡትን ታጋይ ዲታዎች በዚህ መነፅር ለመቃኘት ብንሞክርስ?
ሀብታምነት እንደ አገሩ የምጣኔ ደረጃ እና አማካይ ገቢ የሚለያይ ቢሆንም በጥቅሉ በድሎት እና ምቾት የተደላደለ ኑሮ ላይ መድረስ መቻል ነው በሚል ልንገልፀው እንችላለን። ጥሪት አከማችቶ ቢጠሩት የማይሰማ የናጠጠ ሀብታም ከሚባሉት ተርታ ለመሰለፍ ብዙ ውጣ ውረድ ማለፍ ያስፈልጋል።
ነግዶ በማትረፍ ፣ ተምሮ ከጥበብ ማማ ላይ ቆሞ ጠብሰቅ ያለ ደሞዝ እና ህግ በሚፈቅደው አግባብ ጥቅማ ጥቅም በማግኘት ወይንም ስኬታማ የፈጠራ ግኝት አዳብሮ በውጤቱ በማትረፍ ፣ ከቤተሰብ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ ውርስ… ወዘተ። ወይንም ዛሬ ኢንቨስተር እንደሆኑት አትሌቶቻችን የድህነትን ዳገት በሩጫ መውጣትም አንዱ መንገድ መሆኑን እያየን ነው። አቋራጭ መንገድ የለም። የነገደ ሁሉ አያተርፍም ፣ የሮጠ ሁሉ አይቀድምም እንጂ… የታገለ ሁሉ አያቸንፍም የሚለውን እናክልበት?
ይህ አንግዲህ ከመጋረጃ በስተጀርባ የተደበቀ ምትሀት ሳይቀየጥበት ከሞላ ጎደል ህጋዊ በሆነ መንገድ የሚደረጅ ሀብት ነው። ሳይቀሙ ፣ ሳያምታቱ ፣ በስልጣን ትምክህት ህገወጥ በሆነ መንገድ የአገር የህዝብ ወይንም የሌላውን ዜጋ ንብረት ሳይቀሙ የሚገኝ አዱኛ ነው።
ከተለመደው ህጋዊ መንገድ እና ከተፈጥሯዊ የኢኮኖሚ ሂደት ውጪ ሳይነግዱ ወይ ሳይማሩ ወይ ሳይሮጡ ጠመንጃ በመጨበጣቸው ብቻ ሀብት በሀብት መሆን እንደሚቻል በወያኔ የአገዛዝ ዘመን ይፋ ሆኖ ያየነው አዲሱ የድህነት ማራገፊያ ብልሀት ነው። ይህን ላንባቢ መንገር ለቀባሪ አረዱት ያህል ይሆንብኛል። ጉዳዩን በበቂ ጭብጥ ለማሳየት ግን በቶን የሚመዘን አስረጂ ማቅረብ ይቻላል። የዛሬዎቹን ቱባ ባለ ፎቅ ቤት ሹማምንት የትናንት ነፃ አውጪ ታጋዮች ኑሮ ከየት ወደ የት የሚለውን በማጣቀስ እና በመፈተሽ ።
አንዲት ቀን እንኳ የዩንቨርሲቲ ደጃፍ ሳይረግጡ ወይንም መፅሀፍ ሳያገላብጡ ባላ ማስተርስ እና ዶክተሬት እንደሆኑት ሁሉ ከድህነት ወደ ሀብታምነት ፣ ከማይምነት ወደ ወረቀት ሊቅነት ፣ ከተራ ጎጆ ወደ ተንጣለለ ቪላ ፣ ከሞጋ ጫማ ወደ መርሰዲስ ቤንዝ ፣ በመርፌ ከተጠቃቀመ ቁምጣ ወደ ሀር ሸማ መሸጋገር እንደሚቻል አሳይተውናል። ውጣ ውረድ ፣ እንቅልፍ ማጣት ፣ ፈተና መቀመጥ እና መወዳደር ለተራው ህዝብ ልጆች የተተወ መንገድ ነው – ጠመንጃ ይዘው ስልጣን ላይ የወጡት ነፃ አውጪዎች የሚሳናቸው ምንም ነገር አለመኖሩን በየዘርፉ አረጋግጠዋል።
ነፃነት እንሻለን ብለው ትናንት ጫካ የገቡት ወያኔዎች ከፊሉ ከትምህርት ገበታው ፣ ሌላው ከእርሻ ማሳው ወይንም ከመደበኛ ስራው ተንደርድረው መሄዳቸው ይታወቃል። በረሀ ለመውረድ የተገደዱት ደግሞ ፍትህ ስለጠፋ ፣ በዜጎች መካከል ተመጣጣኝ የሀብት ክፍፍል ስለሌለ ፣ መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች ስለታፈኑ ፣ ኤርትራ ቅኝ ግዛት ስለሆነች ፣ የመገንጠል መብት ስለተረገጠ… ያልተበረዘ ያልተከለሰ ኮሙኒዝም ተግባራዊ የሚሆንባት አገር ለመትከል… እያለ ይቀጥላል።
እናም ብረት አነሱ ፣ በለስ ቀንቷቸው ተሟሙተው ለስልጣን ወንበር ደረሱ – አለቀ ደቀቀ። ወደ ስልጣን መንበር እየገሰገሱ ከነበረበት ዘመን አንስቶ ግን ባህሪያቸው እና አድራጎታቸው እንዋገዋለን ብለው ከሚሰብኩት አላማ መካከል በተለይ በፍትህ እነ በሰብአዊ መብት ዙርያ ብሎም በህግ የበላይነት ጥያቄ ላይ የነበራቸው ታሪክ በሰነድም በአይን እማኞችም እንደተረጋጋጠው ጉድፍ የተሞላበት ነበር። ከቆሙለት አላማ መካከል ሳይከለስ ሳይበረዝ ያከናወኑት ቢኖር ኤርትራን አስገንጥለዋል ፣ እርግጥ ነው የመገንጠል መብት በህግ እንዲፀድቅ አድርገዋል።
ትናንት ቁምጣ ተጥቆ ባንድ እጁ ጠመንጃ በሌላ እጁ የተቋጠረ በሶ ጨብጦ አዲስ አበባ የገባው ነፃ አውጪ ዛሬ ቢጠሩት የማይሰማ ቱጃር ሆኗል – ህግ የማይገዛው ፣ በህግ የማይዳኝ የማይጠየቅ በደረጃው የላቀ ዜጋ ሆኗል። ተራውን ህዝብ እዚያው ተራ ተርታ ትቶት ሽቅብ ተመዟል።
መሬት ፣ ፎቅ ቤት ፣ ውድ አውቶሞቢል ፣ ዘጠኝ አሀዝ ብር በግል ፣ በሚስት ፣ አጎት እና አክስት ስም ማከማቸት – ቤት ሲፈተሽ ድንበር የለሽ የገንዘብ አይነት (ዶላር) በየፍራሹ ስር ረፍርፎ መተኛት ዋነኛ መታወቂያው ሆኗል። ሰሞኑን እንደምንሰማው ደግሞ የዘረፉትን ብር ዱካ ለማጥፋት መሬት ቆፍሮ መቅበር አይነተኛ የቁጠባ (saving) ስልት ሆኗል።
የወያኔ አገዛዝ እና ገዢዎች የደረሱበት የዘረፋ መጠን ለጆሮ የሚቀፍ አይነት ስግብግብነት የተጠናወተው መሆኑን ድርጊታቸው ይበልጥ እየመሰከረ ነው። ጉዳዩ ለህዝብ እንግዳ ባይሆንም እነሱ ግን ተሰብስበው ‘ሌብነታችን’ ቅጥ እያጣ ነው እስከማለት ደርሰዋል – አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል እንደሚሉት ሆኖባቸው የግፍ ፅዋ ሞልቶ ሲፈስ ራሳቸውንም ያንገሸገሻቸው ይመስላል። መትፋት ሳያስነውር ሀያ አራት ዓመታት ተቆጥሮ ዛሬ ምን ተገኘ ያሰኛል።
በያቅጣጫው የሚነገረው ጄነራሎች ስለ ገነቡት ፎቅ ሆኗል። መደበኛ ጦር ትምህርት ቤት ገብቶ የማያውቅ የወያኔ ጄኔራል ትከሻው ላይ አንበሳ ጭኖ መሬት ዝርፊያ ላይ ዘመቻ ሲያደርግ መኖሩን ማን ይስተዋል። እናም ፎቅ ቤት በማስገንባት ውድድር ለማሸነፍ ፉክክሩ ቀጥሏል።
ሰሞኑን የተገረን ዜና ለዚህ ውድድር ማድመቂያ አይነተኛ ማጣቀሻ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከ15 ሚሊየን በላይ ህዝብ ጠኔ እየቆላው ቢሆንም ቅሉ ጡረታ ለሚወጡ ታጋይ ወያኔዎች ለያንዳንዳቸው 25 ሚሊየን ብር የፈጀ ‘መጠለያ’ እየተገነባላቸው ነው። ልማታዊው መንግስታችን ታጋዮቹ በጡረታ ዘመናቸው እንዳይከፋቸው እጅጉን በመጨነቁ ፤ እስከ ዛሬ ያጋበሱት ያግበሰበሱት አልበቃ ብሎ ከረሀብተኛው ህዝብ በተሰበሰበ ታክስ ወይንም በስሙ በተለመነ ዶላር አሮጌ ታጋዮች የተንጣለለ ቪላ ሊሸለሙ ነው። በዜናው እንደተጠቀሰው ይህ የትም አገር ተደርጎ የማያውቅ በመሆኑ አገራችንን አንደኛ አድርጓታል።
ዝናም የማይፈራው ወያኔ እነሆ ከፊታችን ቆሟል።
ድህነታቸውን እስከ ወዲያኛው ተረት ለማድረግ ቆርጠው በተነሱ ነፃ አውጪዎች እርምጃ ያኔ ‘ተራሮችን ያንቀጠቀጠው’ ታጋይ ሜዳዎችን በፎቅ እያንቆጠቆጠ ነው… ።
የዕለት ጉርስ እንዳይጎድልበት ደፋ ቀና ሲል የቆየው ዜጋ ዋስትና በሌለውና እንደ ቀስት ሽቅብ ከሚወነጨፍ የገበያ ዋጋ ግሽበት ጋር መራመድ ተስኖት ዛሬ የቆሻሻ ምግብ መጣያ መኪና ላይ ከነ ቴድሮስ አድሀኖም ፣ በረከት ስምኦን ፣ ደብረፅዮን ፣ አርከበ እና ሌሎች ኦሮሞን ፣ አማራን ፣ ደቡብን …ወዘተ ወክለናል ከሚሉ ታጋዮች ጌቶቹ ቤት እና ማዕድ ተርፎ የተጣለ ፍርፋሪ ለመልቀም ተገዷል። ሲያገኝ በልቶ ሲያጣ ጦሙን ተደፍቶ ጊዜውን ይገፋል።
እነሱ ድህነታቸውን ተረት አድርገውታል – እነሱ የሚተርቱለትን ድህነት እየኖረላቸው ነው።
በተባበሩት መንግሥታት የሕዝብ የኑሮ እድገት መለኪያ መሠረት (ማለትም በትምህርት፤ በጤናና በሌሎች የኑሮ ሁኔታ መለኪያዎች) ዛሬም ኢትዮጵያ ከ187 አገሮች ውስጥ 173ኛውን ደረጃ በመያዝ በዓለም የመጨረሻ ተርታ ተሰልፋ ትገኛለች። 73 ከመቶ የሚሆነው የአገራችን ሕዝብ በቀን ከ$1 ዶላር በታች ገቢ የሚያገኝ ነው። በቀን 1.25 ዶላር የሚያገኘው ብዛት ከሕዝባችን 35 ከመቶ የሚሆነው ነው። 88.2 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ በጤና በትምህርትና በኑሮ ሁኔታ የመጨረሻ ደኻ ተብሎ የተፈረጀ ነው። 44 ከመቶ የሚሆኑት ሕጻናት በቂ ምግብ የማያገኙ ናቸው። ከ15 ሚሊየን ህዝብ በላይ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ለጠኔ ተጋልጦ የወያኔን ተረት እየሰማ ያድራል።
ባለፈው ዓመት ከአሜረካ እርዳታ ድርጅት (US Aid) ብቻ የ$237 ሚሊዮን (ዶላር) የምግብ እርዳታ ተቀብላለች። በከተሞች በአነስተኛ ደረጃ የተሟላ የመጸዳጂያ አገልግሎት የሚያገኘው ሕዝብ 27 ከመቶ ብቻ ነው። የኢንተርኔት ተጠቃሚው ሕዝብ 1.5 ከመቶ በታች ነው። ከተሞች አካባቢ በመብራትና በውሃ እጦት የሚሰቃየው ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ነው። በዋና ከተማው ዛሬ መብራት ለሳምንታት ያህል ጨርሶ የሚጠፋበት ሰማይ ጠቀስ ፎቆች በተንጣለሉበት ከተማ ወሃ በጀሪካን የሚገዛበት ብቸኛይቱ አገር ናት… ።
ስለድህነታቸው የሚተርቱ ታጋይ ሀብታሞች የፈለቁባት ብቸኛዋ አገርም ናት – በሁሉም አንደኛ!
ይቀጥላል
Source: Ecadforum

No comments: