Wednesday, September 30, 2015

የሽብር ተግባር ለመፈጸም ፌደራል ፖሊስነት ተቀጥረዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የግንቦት 7 ድርጅትን ተልዕኮ በመቀበል የሽብር ተግባር ለመፈጸም የፌዴራል ፖሊስ አባል በመሆን መረጃ ሲያስተላልፉ ተደርሶባቸዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
በፌደራል ፖሊስ ተቋም ውስጥ ተመድበው ሕገ መንግሥቱን ለመጠበቅ የተጣለባቸውን አደራ በመተው፣ የግንቦት 7 ጥምረት ነው የተባለውን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የሰጣቸውን ተልዕኮ በመቀበል ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉት፣ ኮንስታብል ነገደ ሸዋ ቀናና ረዳት ሳጅን እንዳለ ዘየደ የሚባሉ መሆናቸውን፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት መስከረም 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ያቀረበው ክስ ይገልጻል፡፡
ኮንስታብል ነገደ የተባለው ተጠርጣሪ ኤርትራ ከሚኖርና የግንቦት 7 ድርጅት አባል ጋር በስልክ በመገናኘት፣ ለመንግሥት ጥሩ አመለካከት የሌላቸውን እየመለመለ አድራሻቸውን እንዲሰጠው መስማማታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በፌዴራል ፖሊስ ተመሳሳይ የሥራ ድርሻ የነበረው ተከሳሽ ረዳት ሳጅን እንዳለ ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙን የሚገልጸው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ ሁለቱም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ክሱን ተቀብሎ ያየው ተረኛ ችሎትም ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ በማዘዝ፣ ክሱን ለመስማት ለጥቅምት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ሌላው የመከላከያ ሠራዊት አባል መሆኑ የተጠቀሰውና የኦነግ አባል በመሆን አባላትን በመመልመልና መረጃ በማስተላለፍ ተጠርጥሮ ክስ የተመሠረተበት ወታደር አማኑኤል ደስታ ጅማ ይባላል፡፡
ተከሳሹ ኅብረተሰቡን አደጋ ላይ ለመጣል፣ ሕይወት ለማጥፋትና ንብረት ለማውደምና በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር፣ ከመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሻኪሶ አካባቢ ከድርጅቱ አባላት ጋር ይገናኝ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ተከሳሹ የኦነግን ተልዕኮ ለማሳካት በጥር ወር 2007 ዓ.ም. በአገር መከላከያ ሠራዊት በመቀጠርና ለአራት ወራት ሁርሶ ወታደራዊ ሥልጠና በመውሰድ፣ ሠራዊቱን ተቀላቅሎ መመደቡን ክሱ ያብራራል፡፡
በሠራዊቱ ውስጥ ከተመደበ በኋላ አባላትን በመመልመልና በማደራጀት በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን፣ ሻኪሶ ወረዳ፣ ሻኪሶ ከተማ ከሚገኘውና የኦነግ አባል ከሆነው ደበበ ሚደቅሳ ከተባለው የድርጅቱ አባል ጋር ግንኙነት ሲያደርግ መቆየቱ በክሱ ተጠቅሷል፡፡
የመለመላቸውን ሻምበል ባሻ ስንታየሁና ሃምሳ አለቃ ሸለመ ሞቱማ የተባሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላትንና ሌሎች ወታደሮችን አስከድቶ፣ ወደ ኤርትራ ሄደው ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ እያሉ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ክሱ ይገልጻል፡፡ ክሱን ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments: