Wednesday, September 9, 2015

ፍርድ ቤቱ በእነ ጌታቸው መኮንን ላይ ተጨማሪ ምስክሮችን ለመስማት ለህዳር 13 ቀጠረባቸው

• ‹‹እኛ ብቻ አይደለም የተሰቃየነው፡፡ የሀሰት ምስክርነት ስጡ ተብለው ሁለት ሰዎች አካላቸውን አጥተዋል›› አቶ ተስፋዬ ታሪኩ
• ‹‹በማዕከላዊ 6 ወር ጨለማ ቤት ስለቆየሁ አይኔን ታምሜ ህክምና ተከልክያለሁ›› አቶ አንጋው ተገኝ
• ‹‹ማይካድራ ላይ ያዙን፡፡ ሁመራ ወሰዱንና ተገረፍን፡፡›› ምስክር
የልደታ ፍርድ ቤት 19ኛው ወንጀል ችሎት በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ ስር የሚገኙ ተከሳሾች ላይ ተጨማሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለህዳር 13/2008 ዓ.ም ቀጥሮባቸዋል፡፡ ትናንት ጳግሜ 3/2007 ዓ.ም 13 ምስክሮችን እንዲሁም በዛሬው ዕለት 7 ምስክሮችን በማሰማት አጠናቅቃለሁ ብሎ የነበረው የፌደራል አቃቤ ህግ በትናንትናው ዕለት 6 እንዲሁም በዛሬው ዕለት 8 ምስክሮችን ብቻ ያሰማ ሲሆን ተጨማሪ 6 ምስክሮችን ለማሰማት ረዥም ቀጠሮ ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡
በትናንትናው ዕለት በ6ኛ፣ በ7ኛ፣ በ9ኛ እና በ12ኛ ተከሳሾች ላይ ምስክሮቹን ያሰማው አቃቤ ህግ በ1ኛ ተከሳሽ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን፣ በ8ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ታሪኩ፣ በ13ኛ ተከሳሽ እንግዳው ቃኘው፣ በ15ኛ ተከሳሽ አግባው ሰጠኝ ላይ የሰነድ ማስረጃ እንጅ የሰው ምስክር እንደሌለው አስረድቷል፡፡ በዛሬው ዕለት በ2ኛ ተከሳሽ በላይነህ ሲሳይ፣ 3ኛ ተከሳሽ አለባቸው ማሞ፣ 4ኛ ተከሳሽ አወቀ ሞኝ ሆዴ፣ 5ኛ ተከሳሽ ዘሪሁን በሬ እና በትናንትናው ዕለት ምስክሮች የተሰሙበት 7ኛ ተከሳሽ አማረ መስፍን ላይ ምስክሮቹን አሰምቷል፡፡
የአቶ አማረ መስፍን ቤት በፖሊስ ተከቦ ሲበረበር የጦር መሳሪያና ሰነዶች ይኖራሉ ተብሎ ለእማኝነት እንደተጠራ የተናገረው 7ኛ ምስክር ሆኖም ‹‹በአቶ አማረ መስፍን ቤት ይኖራል ተብሎ የተጠበቀው መሳሪያና ሰነድ አልተገኘም፡፡›› ሲል መስክቷል፡፡ የተከሳሽ የግል ድርጅት በሆነው ሱቅ ውስጥ ሽጉጥ እንደተገኘ የተናገረው ምስክር መሳሪያው ህጋዊ መሆን አለመሆኑን ሲጠየቅ ‹‹መተማ ውስጥ ሁሉም ሰው ድርጅት መጠበቂያ መሳሪያ አለው፡፡ እኔ በዚሁ ከተማ ስለሆነ የምኖረው አውቀዋለሁ፡፡ መንግስት አስመዝግቡ ብሎ ይመጣል እንጅ ነዋሪው ለድርጅቱ መጠበቂያ ያልተመዘገበም ቢሆን መሳሪያ ይኖረዋል፡፡›› ብሏል፡፡
በውንብድና ወንጀል ተከሶ 10 አመት ተፈርዶበት ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2005 ዓ.ም ታስሮ እንደተፈታ የገለፀው 8ኛ ምስክር በበኩሉ በአቶ በላይነህ ሲሳይ በኩል ስልካቸውን አገኘሁ ያላቸው ኤርትራ ውስጥ የሚኖሩ የአርበኛው ግንባር አመራሮች በኢትዮጵያ የስልክ ቁጥር ሲደውሉለት እንደነበር፣ የአርበኛው ግንባር አመራሮች መሳሪያና ገንዘብ እንዲወስድ ሲጠይቁት ለገንዳውሃ አስተዳደር አመልክቶ መሳሪያውንና ገንዘቡን እንዲቀበል እንዳበረታቱት፣ መልምለውኛል ያላቸውንና ተመልምለዋል ያላቸውን ሰዎች እንቅስቃሴ ለመንግስት ሲያሳውቅ እንደቆየ መስክሯል፡፡
በአቶ አለባቸው ማሞ ላይ የመሰከረው 9ኛ ምስክር በዋና ጥያቄ የኢህአዴግ አባል መሆኑን እንዲሁም በመስቀለኛ ጥያቄ ደህንነት መሆኑን አምኗል፡፡ ምስክሩ ‹‹ብአዴን አይቀጥልም፡፡ በመሆኑም ከህዝብ ጋር አትቀያየም፡፡ ክፉ ስራ አትስራ›› በሚል ኤርትራ ከሚገኙ አመራሮች ሲደወሉለት እንደነበር ስልኩንም ተከሳሹ ለአመራሮቹ እንደሰጠበት መስክሯል፡፡ 9ኛ ምስክርን ጨምሮ ሌሎችም የአቃቤ ህግ ምስክሮች ፍርድ ቤት በተገኙ የተከሳሾች ቤተሰቦች ማስፈራሪያና ዛቻ እየተፈፀመባቸው ነው ሲል አቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርቧል፡፡
አቶ አወቀ ሞኝሆዴ ላይ የመሰከረው 10ኛ ምስክር በአሁኑ ወቅት ኤርትራ ውስጥ ይገኛሉ ያላቸው አቶ አንለይ ተስፋው የተባሉ ግለሰብ ወደ ኤርትራ የሄዱበት እሱም እንዲሄድ የተጠየቀበትን ምክንያት ሲያስረዳ ‹‹ኤርትራ ውስጥ ቅንጅት ስላለ ነው፡፡›› ብሏል፡፡ ለምስክርነት የመጣበት ተከሳሽ ለምን እንደተከሰሰ ሲጠየቅም ‹‹የቅንጅት አባል በመሆኑ ነው የተከሰሰው›› ብሏል፡፡ ወደ ኤርትራ ለመሄድ ማይካድራ ላይ እንደተያዘ የገለፀው ምስክሩ ‹‹ማይካድራ ላይ ያዙን፡፡ ሁመራ ወሰዱንና ተገረፍን፡፡›› ብሏል፡፡ በእስር ላይ እንደቆየም ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በተመሳሳይ አቶ ዘሪሁን በሬ ላይ የመሰከሩት 12ኛ ምስክርም ‹‹ማይካድራ ላይ ከተያዝኩ በኋላ ሁመራ ላይ ተቀጥቻለሁ፡፡›› ብለዋል፡፡
አቃቤ ህግ በዛሬው ዕለት ሁሉንም ምስክሮች አሰምቼ እጨርሳለሁ ብሎ የነበር ቢሆንም ሁለቱ ምስክሮች መጥሪያው ደርሷቸው ስላልመጡ፣ እንዲሁም አራት ምስክሮች መጥሪያ ስላልደረሰላቸው ረዥም ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ የተከሳሾቹ ጠበቆች በበኩላቸው አቃቤ ህግ ምስክሮቹን ያላቀረበበት ምክንያት ግልፅ እንዳልሆነ ደጋግመው ለፍርድ ቤቱ መናገራቸውን፣ በተለይ ደንበኞቻቸው ዋስትና ተነፍጓቸው በእስር ላይ የሚገኙ በመሆኑ አቃቤ ህግ ምስክሮቹን ማሰማት እንዳልፈለገ ተቆጥሮ በቀጣዩ ቀጠሮ ብይን እንዲሰጥ፣ ይህ ባይሆን አጭር ቀጠሮ ተሰጥቶ የቀሩት ምስክሮች እንዲሰሙ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ከተከሳሾቹ መካከል 8ኛ ተከሳሽ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ ‹‹ባለፉት 11 ወራት ያለጠያቂ፣ ቤተሰብም እኛም ብዙ ተሰቃይተናል፡፡ በግፍ እየተሰቃየንም እንገኛለን፡፡ አቃቤ ህግ ምስክሮቹን በታቀደው ጊዜ ማቅረብ አለመቻሉ ደግሞ ከበደላችን በላይ በደል እየተፈፀመብን ነው፡፡ ስቃዩ በእኛ ብቻ ሳይሆን በምስክሮች ላይም ጭምር ነው፡፡ የሀሰት ምስክርነት ስጡ ተብለው ሁለት ሰዎች አካላቸውን አጥተዋል›› ብሏል፡፡ በሀሰት ምስክርነት ስጡ እየተባሉ በደል እየደረሰባቸው ስለሚገኙ ግለሰቦች በሚናገርበት ወቅትም ፍርድ ቤቱ አስቁሞታል፡፡ 14ኛ ተከሳሽ አቶ አንጋው ተገኝ በበኩሉ ‹‹በማዕከላዊ 6 ወር ጨለማ ቤት ስለቆየሁ አይኔን ታምሜያለሁ፡፡ ለአይኔ መነፀር እንደሚያስፈልግ ቢታወቅም ህክምና እንዳላገኝ ተከልክያለሁ፡፡›› ሲል ቅሬታውን አቅርቧል፡፡
አቃቤ ህግ የተለየ መብት እንደተሰጠው፣ ካለ አግባብ ጥያቄዎችን እንደሚያቀርብና ምስክሮችንም በጊዜው ማቅረብ እንዳልቻለ በተደጋጋሚ አቤቱታ ያቀረቡት የተከሳሽ ጠበቃ ‹‹አቃቤ ህግ ችሎቱን እየመራው ነው›› ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም የልደታ ፍርድ ቤት 19ኛው ወንጀል ችሎት የአቃቤ ህግን ቀሪ 6 ምስክሮች ለመስማት ለህዳር 13/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

No comments: