Sunday, February 9, 2014

አባልነት ለሥራ ቅጥር ቀዳሚው መስፈርት

አባልነት ለሥራ ቅጥር ቀዳሚው መስፈርት 

ሕገ መንግሥቱ የኢኮኖሚ የማህበራዊና የባህል መብቶችን በሚገልጽበት አንቀጽ 41 ንዑስ አንቀጽ 1 «ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው » ሲል ንዑስ አንቀጽ 2 ደግሞ «ሁሉም ኢትየጵያዊ መተዳደሪያ ሥራውንና ሙያውን የመምረጥ መብት» ያለው መሆኑን ይደነግጋል፡፡
ይሁን እንጂ አንድ ሰው በፈለገው መስክ ለመሰማራትም ሆነ የመረጠውን ስራ ለመስራት በህገ መንግሥት መደንገጉ ብቻውን የሚያስችለው አይሆንም፡፡ እውቀት፣ ልምድ፣ ችሎታ፣ዝንባሌ ወዘተ አስፈላጊ ነው፡፡ የሥራ ማስታወቂያ ሲወጣ የትምህርት ዝግጅት፤ የእውቀት ደረጃ፣ የስራ ልምድ ወዘተ መስፈርት ተደርጎ ተዘርዝሮ የሚገለጸው የሚፈልጉትን ሥራ መምረጥ ብቻ ለሥራ ስለማያበቃ ነው፡፡ በቀጣሪው አካል መመረጥንና መፈለግን ይጠይቃል፡፡
ነገር ግን ቀጣሪው መስሪያ ቤት በግልጽ ከሚታወቁ መስፈርቶች አልፎ በይፋ ያለተገለጸና የማይገለጽ ፖለቲካዊ መመዘኛ ካወጣና አይን አውጥቶ የኢህአዴግ አባል ለመሆናችሁ ማስረጃ አቅርቡ ካለ፣ በዚህም ምክንያት የመወዳደሪያ ፈተናውን በአጥጋቢ ውጤት ያለፉትን ወደ ጎን አድርጎ ዝቅተኛ ውጤት ያመጡትን ለአባልነታቸው ቅድሚያ ሰጥቶ ከቀጠር ከላይ የተጠቀሰውን የህገ መንግስት ድንጋጌ በግልጽና በድፍረት መጣስ ይሆናል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም ህገ መንግሥቱ በአንቀጽ 25 /1 «ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው በመካከላቸውም ማንኛውም አይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡በዚህ ረገድ በዘር በብሄር ብሔረሰብ በቀለም፣በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣በፖለቲካ፣ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው፡»ተብሎ በግልጽ የሰፈረውን መጋፋት ነው፡፡
ስለ ህገ መንግሥቱ ጠዋት ማታ የሚዘምሩና ራሳቸውን ከምንም በላይ የሕገ መንግስቱ ተጠቃሚም ጠባቂና ጠበቃም አድርገው ሌሎችን ያለ መረጃና ማስረጃ ጸረ ሕገ መንግሥት እያሉ የሚወነጅሉ በተለያየ የሥልጣን ደረጃ ላይ የሚገኙ የሥርዓቱ ሰዎች በማስታወቂያ ከሚያወጡት የሥራ መመዘኛ በስተጀርባ በአደባባይ ከሚናገሩት የሰዎች እኩልነት በተቃራኒ ሥራ ለመቅጠር አባልነትን ዋና መስፈርት እያደረጉ ሕገ መንግስቱን እየረገጡ ነው፡፡
ይህን ለአመታት ከተቃውሞው ወገን ክስ ሲቀርብበትና በመንግሥት በኩል ደግሞ ሲስተባበል የኖረ ጉዳይ አንደ አዲስ ማንሳቴ ግልጽና ወቅታዊ ማስረጃ በማግኘቴ ነው፡፡ ለምርጫ 2007 ዝግጅት ይሁን ወይንም የ2006 ዓመት በጀት የሚያወላዳ ሆኖ ባይታወቅም ቀበሌዎች ተጨፍለቀው የፈጠሩዋቸው ወረዳዎች በርካታ የስራ መደቦችን እያዘጋጁ የከፍተኛ ትምህርት ወጣት ምሩቃንን ለሥራ እየጠሩ ነው፡፡ ማስታወቂያ አይቶ አራት ኪሎ አካባቢ ከሚገኙ የወረዳ ጽ/ቤቶች ወደ አንዱ በመሄድ የተወዳዳረ የአንድ ወዳጄ ልጅ ለጽሁፍ ፈተና ከተቀመጡ ተወዳዳሪዎች ሁሉ የበለጠ ውጤት አምጥቶ አራት ከሚሆኑ ተወዳዳሪዎች ጋር ለቃለ መጠይቅ/ለቃል ፈተና ይጠራል፡፡ ይህ ወጣት በእለቱ የገጠመውንና ለዚህ አስተያየት መነሻ ምክንያት የሆነኝን ጉዳይ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡
«ጥያቄው ቀላልና አስገራሚ ነበር፣ ራስህን ግለጽ ተባልኩኝ ገለጽሁ፡፡ ከዛም ሕገ መንግሥቱን ተቀብለሀል ወይ የሚል ጥያቄ ሲቀርብልኝ በጣም ተገርሜ መገረሜንም የፊቴ ገጽታ እያሳበቀብኝ ሕገ መንግሥቱን ተቀብዬማ በሀገሪቱ እየኖርኩ ነው በማለት ስመልስ ጠያቂዬ የፊቴ ገጽታም የአነጋገሬ ሁኔታም ያልጠበቀው ሆኖበት ነው መሰል እንደመደናገጥ ብሎ አንደበቱ እየተንተባተበ ማለቴ እ.እ በካምፓስ ቆይታህ ተሳትፎ አልነበረህም ወይ አለኝ፡ ቃላቶቹን በጭንቀት ከአንደበቱ እያወጣ፡፡ የምን ተሳትፎ አልኩት፡፡ በኢህአዴግ አባልነት፣ካምባስ እያለህ አንዳንድ ተሳትፎዎችን ከአደረክ እኮ ማስረጃ ይሰጣል በማለት ሲጨነቅበት የቆየውን የመጨረሻ ነገር እንደምንም ተነፈሰው፡፡ አልነበርኩም ለመሆኑ አሁን የምትጠይቀኝ ሥራ ለመቀጠር አባልነት መስፈርት ሆኖ ነው፣ ከሆነስ ማስታወቂያ ስታወጡ የአባልነት ማስረጃ ማቅረብ የሚችል በማለት መስፈርቱ ላይ አትገልጹም ነበር አልኩት፡፡ ሊያሳምነኝ የሚያስችል እውነት፣ ሊከራከረኝ የሚያበቃው ሞራል አልነበረውምና አየተቅለሰለሰ ከቻልክ እስከ ከሰዐት በኋላ ለማቅረብ ሞክር በማለት አሰናበተኝ፣» በማለት በሀዘኔታና በመገረም ነበር ሁኔታውን የገለጸልን፡፡ አባል ባለመሆኑ ወይንም የውሸትም ቢሆን የተሳትፎ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ ለማወዳደሪያ የቀረበውን ፈተና በአጥጋቢ ውጤት ያለፈው ወጣት የተወዳደረበትን የሥራ ቦታ ሳያገኝ ቀረ፡፡
ይህ አድራጎት በቀዳሚነት ሕገ መንግሥቱን የሚጥስና የዜግነት መብትን የሚገፍ ነው፡፡ሲቀጥል ደግሞ ለህግ የበላይነት አለመከበር፣ለመልካም አስተዳደር አለመስፈን፣ለሰብአዊ መብቶች አለመረጋገጥ ወዘተ ምክንያት ነው፡፡ ሁለት አሥርት አመታት እነዚህ ጉዳዩች አጀንዳ እንደሆኑ መዝለቃቸው የአለም ህብረተስብ ውግዘት ፣የኢትዮጵያውያን ተቃውሞ፣ የመንግስት ግምገማ፣ ስብሰባ፣ መተካካት ትራንስፎርሜሽን ክስና እስራት ሊያስተካክላቸው አለመቻሉ ከመሰረቱ ቅጥር በእውቀት ሳይሆን በአባልነትና በታማኘነት መፈጸሙ አንዱ ምክንያት ነው፡፡
በእውቀቱ በልጦ በችሎታው ተወዳድሮ የተቀጠረ ሰው ይበልጥ ለማወቅ ይጥራል፣የሚያውቀውን ይፈጽማል፣ለህሊናው ታማኝ፣ ለህግ ተገዢ፣ባለጉዳይን አክባሪ ሆኖ ይሰራል፡፡ በአንጻሩ በአባልነት የተቀጠረ ለቦታው ያበቃውን አባልነት በበለጠ ታማኝነት ለማረጋገጥ ከአጎብዳጅነት አልፎ የቅርብ አለቆቹ ሎሌ እስከመሆን ይወርዳል፡፡ በመንፈስ ይደኸያል በሞራል ይዘቅጣል፡፡ ይህ ሲሆን ህሊና፣ ፈጣሪ፣ ህግ፣ሕዝብ፣ የሚባሉ በዚህ ሰው አእምሮ ውስጥ ቦታ አይኖራቸውም፡፡
ሆኖ ሳይሆን መስሎ መኖሩን ስለሚያውቅ በማይገባው ቦታ መቀመጡም ስለማይዘነጋው አንድ ቀን ቦታውን ላጣው እችላለሁ ብሎ ስለሚሰጋም የሚነገረውን እንደበቀቀን ከመድገም፣ አንደገደል ማሚቱ ከማስተጋባት፣ የሚታዘዘውን ያለምንም ጥያቄና ማንገራገር ከመፈጸም ውጪ ምርጫም መንገድም አይኖረውም፡፡ በዚህ መንገድ መንፈሱን ገሎ ህሊናውን አደድቦ ይኖራል፣ በዚህ ቦታ እስከመጨረሻው አልዘልቅም በሚለው ስጋትም የሙስና ዋና ተዋናይ ይሆናል፡፡ ለሙሰኝነት ህሊና ቢስነት ያስፈልጋል፡፡ ፈሪሀ እግዚአብሄር ያለው የህሊናው ጌታ የሆነ የሞራል የበላይነትና የመንፈስ ነጻነት የተቀዳጀ ሰው በዘረፋ አይሰማራም፣የሙስና ተዋናይ አይሆንም፡፡
ሲቪል ሰርቪስ ምኒስቴር መስሪያ ቤትን የተፈራረቁበት ባለሥልጣኖች በየሥልጣን ዘመናቸው በምኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስር ያለው ሰፊ ቁጥር ያለው ሰራተኛ ተገቢውን አገልግሎት ለተገልጋዩ ሊሰጥ እንዳልቻለ መልካም አስተዳደርን ማስፈን እንደተሰናው እየገለጹ ክፍተት የሚል የክርስትና ስም ያወጡለትን ድክመት ለመሸፈን ስልጠናን፣ የሰራተኛ ብወዛን፣ የመወቅር መለዋወጥን ወዘተ በመፍትሄነት ተግባራዊ ማድረጋቸውን ያለፉት ተናግረዋል፡፡ ያሉትም እየተናገሩ ነው፡፡ መፍትሄ የተባለው ግን በሽታው ሳይታወቅ የታዘዘ መድሀኒት በመሆኑ ለውጥ ሊያመጣ ፈውስ ሊያስገኝ አልቻለም፡፡
ዶ/ር የራስ ወርቅ በርዕይ 2020 የውይይት መድረክ ላይ «ሥርዓታት ፣የፖለቲካ ነፃነት እና ልማት በኢትዮጵያ» በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ «በመጀመሪያ ደረጃ የቱ የቱ የመንግሥት የሥራ ገበታዎች በፖለቲካ ተዋሚዎች እንደሚያዙና የቱ የቱ ደግሞ ለተቀጣሪ ባለሙያዎች ወይም ሲቪል አገልጋዮች ክፍት አንደሚሆኑ የሚወስንና ይህንኑም በተግባር ያረጋገጠ ቀልጣፋ የቢሮክራሲ ሥረዓት መገንባት አለበት፡፡ የዚህ አይነቱ የቢሮክራሲ ሥርዓት ዕውን መሆን «መልካም አሰተዳደር »የሚባለውን በተሟላ መልኩ ለማስገኘት ይረዳል፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ሥራውን የማይመጥኑ ሰዎች በሆነ የሥራ ገበታ ላይ ተገኝተው ለሥራ ሂደት እንቅፋት አንዳይፈጥሩ ያደርጋል፡፡ ሁለተኛ እንዲያ ያሉትን ሰዎች ወደሚመጥኑት ብቻ ሳይሆን ይበልጥ ውጤታማ ወደሚሆኑበት የሥራ መስክ በመስደድ ሥራና ሠራተኛን ያገናኛል፡፡ ሦስተኛ ቢሮክራሲው በተፈጥሮው ተለዋዋጭና ወገናዊ ከሆነው ፖለቲካ ውጪ ሆኖ ቀጣይነት ባለው መንገድ እንዲሰራ ያደርጋል፡፡ አራተኛ በተያያዥ ደግሞ የፖለቲካ አቋምና የፖለቲካ ወገናዊነት የግድ «የአንጀራ ጉዳይ »እንዳይሆኑ በማድረግ የዜጎች የፖለቲካ ነፃነት የተረጋገጠበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡» በማለት አጽንኦት ሰጥተው ገልጸው ነበር፡፡
ግና ምን ዋጋ አለው እኛ የምንላችሁን ብቻ ስሙ እኛ የምንለውን ብቻ ተግብሩ የሚሉ ከብቃትና ከእውቀት ይለቅ በአባልነትና በታማኝነት የሚሾሙና የሚቀጠሩ ሰዎች የበዙበት ሥርዓትና ዘመን ሆነና ዶ/ር የራስ ወርቅ መልእክታቸውን ካደረሱ ከስድስት ዓመት በኋላ ዛሬ ለሥራ ቅጥር ከእውቀትና ብቃት በላይ የድርጅት አባልነት ቀዳሚውን ስፍራ አንደያዘ ችግሮችም ባሉበት አንደቀጠሉ ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ዋናውን የዜጎችን የፖለቲካ ነጻነት ማረጋገጥን አንዳይሳካ አድርጎታል፡፡
በዛው ርዕይ 2020 የውይይት መድረክ ላይ ኢንተርፕረነርሽፕ እና ልማት በኢትዮጵያ በሚል ርእስ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶ/ር ወሮታው በዛብህ ስለ መልካም አስተዳደር ከዘረዘሩዋቸው በርካታ ነጥቦች መካከል «መልካም አስተዳደር ቀና፣ ታታሪ፣ ሀገር ወዳድ፣ ህዝብ አክባሪ፣ ሀቀኛ፣ የአመራር ችሎታና ራዕይ ላቸው የፖለቲካና የአስተዳደር መሪዎች ያሉት ሥርዓት ነው፣ መልካም አስተዳደር የሀገርን ጥቅምና ክብር ያስጠብቃል የዜጎቹን መብት ያስከብራል፣»የሚሉ ይገኛሉ፡፡ ይህን አገላለጽ ከላይ ከጠቀስነው ከዶ/ር የራስ ወርቅ አባባል ጋር አዛምደን ስናየው የምናገኘው እውነት ለመልካም አስተዳደር መስፈን በፖለቲከ ሹመትና በተቀጣሪ ባለሙያዎች ወይም ሲቪል አገልጋዮች የሚያዙ ቦታዎቸን መለየት መወሰንና በተግባር ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡
ለዚህ ጽሁፍ ምክንያትና ማስረጃ የሆነው ወጣት እነደአጋጠመው ከታችኛው የመጨረሻ እርከን ጀምሮ ለሥራ ቅጥር ከእውቀትና ከልምድ በላይ የድርጅት አባልነት ዋንኛው መስፈርት እየሆነ ከቀጠለ ሰዎች በዜግነታቸው እንዲሁም በችሎታቸውና በእውቀታቸው ሥራ የመቀጠር መብታቸውን የሚጋፋና ሕገ መንግሥቱን በግልጽና በድፍረት የሚጥስ ተጋባር ከመሆኑ በላይ የመልካም አስተዳደር እጦት የሁልግዜም አጀንዳ ሆኖ አንዲቀጥል ያደርጋል፡፡ የዜጎች የፖለቲካ ነጻነት የተረጋገጠበትን ስርዓት እውን ማድረግም ህልም እንደሆነ ይቀጥላል፡
ዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ ከላይ በተጠቀሰው ጽሁፋቸው እንዲህ ይላሉ፡፡ «ሁሉን በእኩል የሚያስተናግዱ ግልፅነትና አንጻራዊ መረጋጋት ያላቸው ሥርዓታት ዕውን መሆን የሚችሉት የፍትህ የበላይነት ሰፍኖ ሁሉም በህግ ፊት እኩል ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ይኸ ሳይሆን ቀርቶ በማንኛውም ዘመናዊ ሕብረተስብ ዘንድ የሥርዓታት ሁሉ መሰረት የሆኑት የህግ ሥርዓታት (legal institutions) የፖለቲካው ሥርዓት የበታችና ጥገኛ ሆነው ከቀጠሉና ከሕግ በላይ ሆነው የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ አካላትና ባለሥልጣናት በመኖር ከቀጠሉ ወደፊት የሚፈጠሩትም አሁን ያሉትም ሥርዓታት ከላይ የተቀመጡትን መመዘኛዎች ሊያሟሉ ስለማይችሉ በስም እንጂ በገቢር አይኖሩም ማለት ነው፡፡»
ከላይ የተገለጹት የተባሉት መመዘኛዎች ሁሉን በእኩል የሚያስተናግዱ ፣የሚፈቅዱትንና የሚነሱትንም በግልጽ የሚያሳውቁና አንፃራዊ መረጋጋት ያላቸው መሆን የሚሉት ናቸው፡፡
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ምክንያት የሆነው በአደባባይ በሚለጠፉና በሚነገሩ ማስታወቂያዎች የእውቀትና የልምድ ማስታወቂያ እያወጡ በጓዳ የድርጅት አባልነትን ዋንኛ መስፈርት እያደረጉ ቅጥር መፈጸም የብዙ ነገር ማሳያ የሚሆን ነው፡፡
መፍትሄው ግልጽም ቅርብም ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን ምሁራን ጨምሮ በርካታዎቹ ለሀገር ባላቸው ቀናኢነትና ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ባለቤት ሆና ለማየት ካላቸው ጉጉት በግልጽና በድፍረት መፍትሄዎችን ከእነአተገባበር ዘዴያቸው በተለያየ ግዜና መንገድ ጠቁመዋል፡፡ ችግሩ እውነትም መንገድም እኛ ነን ከእኛ ውጪ ያለ ሁሉ ….የሚል አመለካከትና ፍረጃ አይን እንዳያይ ጆሮም አንዳይሰማ ማድረጉ ነው፡፡ ስለሆነም ግምገማ ስብሰባ የመዋቅር ማስተካካያ ትራንስፎርሜሽን ወዘተ ለውጥ ሊያመጣ እንዳልቻለ በመገንዘብ እውነታውን የጋረደባቸውን አይነ ርግብ አውልቀው ጆሮአቸውን ከፍተው እውነቱን ማየት መስማትና በድፍረት መጋፈጥ ነው የሚበጀው፡፡ ጥያቄ ሲቀርብ ተቃውሞ ሲሰነዘር ትችትና አስተያየት ሲጻፍ ያልሆነ ስም እየሰጡ ከመፈረጅና ከማጥላላት በቀጥታ ለሚነሱ ጉዳዮች ምላሽ መስጠቱ መፍትሄም መፈለጉ ነው የሚበጀው፡፡
ኢህአዴግን ያባነነው ምርጫ 97 በግንቦት ወር ተካሂዶ በሰኔ ወር በጥድፊያ ተዘጋጅቶ በተሰራጨው ዲሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ አንድነት በኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሀፍ «የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ በህዝብ ወይም በተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጥ ሳይሆን በህዝብ የተመረጠ መንግሥት የሚቀይሰውን ፖሊሲ የሚተገብር ሙያተኛ በሙያው የሚቀጠርበት መዋቅር ነው፡፡ በመሆኑም መዋቅሩ በተዋጽኦ ሳይሆን በሙያና በሥራ ብቃት የሚመደብ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የሙያና የሥራ ብቃቱ ሳይጓደል ብሄራዊ ተዋፅኦው እንዲመጣጠን ቢደረግ እጅግ ተመራጭ ይሆናል» ይላል፡፡
በተግባር የሚስተዋለው በዚህ ጽሁፍም ማስረጃ የቀረበበት ድርጅታዊ አባልነትም ሆነ ታማኝነት በአብዮታዊ ዴሞክራሲው ጽሁፉ ውስጥ ቦታ አልተሰጣቸውም፡፡ በጽሁፍ የሚገለጸውና በተግባር የሚፈጸመው እንዲህ በተለያየበት አሰራር ከላይ ለማመልከት እንደተሞከረው መልካም አስተዳደር የሰፈነበትና የዜጎች የፖለቲካ ነጻነት የተረጋገጠበት ሥርዓት እውን ማድረግ አይቻልም፡፡ (ጥር 27/2006 ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ላይ የታተመ)

1 comment:

Anonymous said...

ሚስተር ቤንጃሚን የኢሜል ዝርዝሮችን እነሆ ፣ Lfdsloans@outlook.com ፡፡ / ወይም ደግሞ ንግዴን ለመጀመር በ 90,000.00 ዩሮ ብድር የረዳኝ WhatsApp + 1-989-394-3740 እና እኔ በጣም አመስጋኝ ነኝ ፣ እዚህ አንድ ነጠላ እናት ነገሮች እንዳላደረጉ መንገድ ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው ፡፡ ከእኔ ጋር ቀላል ይሁኑ ግን ንግዴ እየጠነከረ ሲመጣ እና እያሰፋ ሲሄድ እያየሁ በሚስተር ሚስተር እርዳታ ፊቴ ላይ ፈገግታ አሳየኝ ፡፡ የገንዘብ ድጋፍን መፈለግ ወይም በዚያ ንግድ ውስጥ መከራን ማለፍ ወይም የመነሻ የንግድ ሥራ ፕሮጀክት መጀመር መፈለግ ይህንን ማየት እና ከችግራቸው ለመውጣት ተስፋ ሊኖረው ይችላል ... እናመሰግናለን ፡፡