Thursday, February 6, 2014

ፕሬስ ከሌለ መንግስት የለም!

ፕሬስ ከሌለ መንግስት የለም!
ነጻ ፕሬስ የመንግስትን አሰራር ለህዝብ፣ የህዝብን አስተያየትና ጥያቄዎች ደግሞ ህዝብን ለሚመራው መንግስትና ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ማስተላለፊያ አብይ ድልድይ ነው፡፡ መንግስትና ህዝብን አገናኝ፣ አስተያየትና ብሶትን መተንፈሻ፣ መፍትሄን መቀየሻ መሳሪያ ነው ፕሬስ፡፡
ነጻ ፕሬስ መልካም ሀሳቦች እንዲጎለብቱ፣ መታረም ያለባቸው ደግሞ እንዲታረሙ መጠቆሚያ ብርቱ ክንድ ነው፡፡ በተለይም ፕሬስ በመንግስት አሰራር ሂደት ውሰጥ የተፈጠሩ፣ የሚፈጠሩና ሊፈጠሩ የሚችሉ ስህተቶችና ክፍተቶችን ለይቶ በማሳየትና በማጋለጥ የመንግስት አካላትን ተጠያቂነት ለማስፈን ዋነኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ሆኖም ግን የኢህአዴግ መንግስት ይህን መሰረታዊ የፕሬስ ሚና ዘንግቶታል፤ አሊያም በአግባቡ አላወቀውም ማለት ነው፡ ፡ መንግስታችን በተለያየ ጊዜ በፕሬሱ እና በጋዜጠኞቹ ላይ እያደረሰ ያለው በደልም ከዚህ የተዛባ የፕሬስን ሚና አረዳድ የመነጨ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በዚህም በህገ- መንግስቱ ዋስትና ያገኘውን የዜጎች በአመቻቸው መንገድ ሁሉ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በአደባባይ እየጣሰ ይገኛል፡፡
መንግስት በራሱ ላይ የሚቀርቡበትን ማናቸውም አይነት ትችት በመፍራት ጋዜጦችን እና መጽሔቶችን ይዘጋል፤ ያግዳል፤ ድህረ-ገጾችን ‹ብሎክ› ያደርጋል፤ እንዲሁም ጋዜጠኞችን በተደጋጋሚ ለእስርና ለእንግልት፣ አንዳንዴም ለሞት እንዲዳረጉ በማድረግ የህዝብን መረጃ በነጻነት የማግኘትን መብት በከፋ ሁኔታ እያፈነ ይገኛል፡፡
በቅርቡ በነጻው ፕሬስ (መጽሔቶች) ላይ ‹የአዝማሚያ ጥናት› አሰርቻለሁ ብሎ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እንዳሰፈረው ደግሞ መጽሔቶችን የጽንፈኛ ፖለቲካ ማራመጃ ናቸው ሲል ክስ አዘል ወቀሳ ሰንዝሮባቸዋል፡፡ በበኩላችን ይህ ጉዳይ ያሳስበናል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ አይነቱ የመንግስት አካሄድ ‹ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ…› ማለት እንደሆነ ካለፉት ተግባሮቹ በመነሳት ምን ሊያደርግ እንደፈለገ ማወቅ ይቻላልና ነው፡ ፡ የሚዲያ ውጤቶችን መዘጋት ከእንግዲህ ማስተናገድ አንችልም፤ እስካሁን የተዘጉ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሳያንሱን ቀሪዎቹን ሲዘጉ ማየት ህዝብ ከሚታገሰው በላይ ነው፡፡
ከመንግስት ወገን መረጃ ለማግኘት እጅጉን ከባድ በሆነበት የሀገራችን መንግስት አሰራር ውስጥ ሙያቸውን ተጠቅመው አማራጭ የመረጃ ምንጭ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙትን የህትመት ውጤቶች በእንዲህ አይነት ‹የአዝማሚያ› ውንጀላ ማካተት መንግስትን ‹የራሷ ሲያርባት…› ያስብለዋል፤ ነጻው ፕሬስ በበኩሉ ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› ይሆንበታል፡፡ በእርግጥም መንግስት ለፕሬሱ እድገት መጫዎት የሚገባው የራሱ ሚና ጎልቶ መውጣት በተገባው ነበር፤ ምክንያቱም የፕሬሱ እድገት የመንግስትን አሰራር ዘመናዊ፣ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት የማድረግ ሚናው የላቀ ስለሆነ ማለት ነው፡፡
ሀቁ ግን መንግስት በአሰራሩ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ስለሌለው ይህን ማድረግ ያስፈራዋል፡፡ ስለሆነም በሰበብ አስባቡ የፕሬሱን መቀጨጭ ሲያፋጥነው ይታያል፡፡ ይህ ሀላፊነት የጎደለውና ከአንድ ሀገርን ከሚመራ መንግስት የማይጠበቅ አፋኝ ተግባር በሀገር ውስጥ ያለውን የፕሬስ እንቅስቃሴ ከማወክ በዘለለ የዲያስፖራ ሚዲያዎችንና ዓለም አቀፍ ስርጭት ያላቸውንም ጭምር ወደ ህዝብ እንዳይደርሱ ሲያደርግና፣ ለማድረግ ሲታትር ይታያል፡፡
ይህንን የሚዲያ አፈና በተመለከተም ሀፍረተ-ቢሱ መንግስታችን በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በኩል ዘመን መፅሔት ላይ የተለያዩ ሚዲያዎችን እንደሚያቅቡ (jaming) በቅርብ ጊዜ መናገራቸው የህዝብን አማራጭ የመረጃ ምንጭ ማሳጣትን ለማመልከት ከበቂ በላይ አስረጂ ነው፡፡ ይህ የመንግስት ተግባር ይቆም ዘንድ ‹ነገረ-ኢትዮጵያ› ማሳሰብ ትወዳለች!
ጋዜጣችን የፕሬሱን ሚና ዘንግቶ የህዝብን የመረጃ ምንጭ ለሚያፍነው መንግስታችን ፕሬስ ከሌለ መንግስት አለሁ ሊል እንደማይችል በድጋሜ ለማስታወስ ትፈልጋለች፡፡ ፕሬስ ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ነው! ስለሆነም ህዝብ ፕሬሱን ይፈልገዋል፤ ሀሳቡን በነጻነት ይገልጽበት ዘንድም የመንግስት እጅ እንዲነሳለት ይፈልጋል፡፡ ከምዕተ-ዓመታት በፊት 3ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ቶማስ ጀፈርሰን ስለፕሬስ አስፈላጊነት ሲናገሩ፣ ‹‹መንግስት ያለ ፕሬስ ወይም ፕሬስ ያለ መንግስት የሚሉ ምርጫዎች ቢቀርቡልኝ ያለምንም ማመንታት ፕሬስ ያለመንግስት የሚለውን እመርጣለሁ›› ብለዋል፡፡

በተቃራኒው ግን በዚህ ሚዲያ ዋነኛ የዓለም ህዝቦች መሳሪያ በሆነበት ዘመን የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት ከድሮዎቹ መንግስታት ሳይማር ቀርቶ ዛሬ ላይ ይህን መሰረታዊ የህዝብ መሳሪያ ይከለክላል፡፡ እናም ይህን መሰሉ የአምባገነንነት ተግባሩን አቁሞ ፕሬሱ በነጻነት ስራውን ይሰራ ዘንድ መንግስት ቢችል ድጋፍ እንዲያደርግ፣ አሊያ ግን በጋዜጠኞችና በፕሬሱ ላይ እያደረሰ ያለውን መጠነ-ሰፊ የማሳደድ እርምጃ እንዲያቆም እናሳስባለን! 

No comments: