Tuesday, March 15, 2016

ሰመጉ በኦሮሚያ የተወሰኑ ወረዳዎች ተፈጸሙ ያላቸውን ግድያዎች፣አስገድዶ መድፈሮችና መፈናቀሎች ይፋ አደረገ

sem7
sem7(ሳተናው) የኦሮሚያ ክልል በ18 ዞኖችና በ342 ወረዳዎች መዋቀሩን ያስታወሰው የሰብዓዊ መብት ጉባኤው በአቅም ውስንነት የተነሳ በሁሉም የኦሮሚያ ዞኖችና ወረዳዎች ባለሞያዎቹን በመላክ ህዝባዊውን ተቃውሞ ተከትሎ ስለተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መከታተል ባይችልም በ33 ወረዳዎች መንቀሳቀስ በቻሉ ባለሞያዎች አማካኝነት መረጃ መሰብሰቡን በመንተራስ 140ኛውን ልዩ መግለጫ ማውጣቱን ይፋ አድርጓል፡፡
የሰመጉ ባለሞያዎች በአካል በመገኘት መረጃዎች የሰበሰቡባቸው ዞኖች ምዕራብ ሸዋ ፣ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ምዕራብ ወለጋ ዞንና በፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞኖች መሆናቸው በመግለጫው ተወስቷል፡፡መረጃዎቹ የተሰባሰቡባቸው ጊዜዎችም ከህዳር 2 እስከ የካቲት 12/2008 ያሉት ናቸው፡፡በቀድሞ አጠራሩ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ይባል የነበረው የአሁኑ ሰመጉ ማጣራት ባደረገባቸውና ተጨባጭ መረጃ አገኘሁባቸው ባላቸው ወረዳዎች 103 ሰዎች ግድያ ተፈጽሞባቸዋል ብሏል፡፡ግድያ የፈጸሙ አካላትንም ሲገልጽ አጋዚ፣የታጠቁ የመንግስት ኃይሎች፣የመከላከያ ኃይል፣የፌደራል ፖሊስና የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ብሏል፡፡ከሟቾቹ ውስጥ ሶስት የፖሊስ አባላት መኖራቸውን ያስታወሰው ሰመጉ በምክትል ኢንስፔክተር፣ዋና ሳጅንና ሳጅን የኃላፊነት ደረጃ ላይ ነበሩ ህይወታቸው ማለፉን ጠቅሷል፡፡ሰመጉ በመግለጫው የፖሊስ አባላቱ በማንና በምን እንደተገደሉ ባይገልጽም በደፈናው ህይወታቸው አልፏል ብሏል፡፡
ወንዶች፣ሴቶች፣ተማሪዎች፣የቀን ሰራተኞችና በተለያየ የስራ መስክ የተሰማሩ ዜጎች በአደባባይ መገደላቸውን በጽኑ ያወገዘው ሰመጉ ከ12 ዓመት እስከ 78 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ሟቾቹ ይገኙ እንደነበርም አስታውቋል፡፡
ሰመጉ ምርመራ ባደረገባቸው ወረዳዎች 79 ሰዎች የቆሰሉና የተደበደቡ ፣84 የታሰሩ፣18 የደረሱበት የማይታወቁ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
በአምቦ፣በጀልዱና ግንደበረት በመንግስት ኃይሎች አስገድዶ የመድፈር ወንጀል መፈጸሙን የገለጸው ሰመጉ አማራ በመሆናቸው ምክንያት 800 መፈናቀላቸውንና ከ600 የሚልቁ ቤቶች መቃጠላቸውን አስታውቋል፡፡በምዕራብ አርሲ የኦርቶዶክስ፣የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል ያለው ሰመጉ ድርጊቱ በማንም ይፈጸም በማን መወገዝ ይገባዋል ብሏል፡፡
ምክትል ኢንስፔክተር፣ዋና ሳጅንና ሳጅን ህይወታቸው አልፏል ይላል እንጂ በምን ምክንያት ህይወታቸው እንዳለፈ አይጠቅስም፡፡
ምንጭ ሰመጉ

Source: Satenaw

No comments: