Thursday, August 27, 2015

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እየታደኑ እየታሰሩ ነው

‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል ስለሆንኩ መታወቂያየን በግድ ነጥቀውኛል››
በምዕራብ ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እየታደኑ እየታሰሩ ነው፡፡ ዛሬ ነሃሴ 21/2007 ዓ.ም በምዕራብ ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ አብዮት ፋና ቀበሌ ሶስት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ታድነው መታሰራቸውን የዞኑ የፓርቲው አስተባባሪዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ሶስቱም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ቤታቸው በታጣቂ ተከቦ እንዳደረ የተገለፀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በቀበሌው ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ታድነው የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ተመስገን የኔሀብቴ፣ ማስተዋል አዱኛና ሙሉ አለየነው ሲሆኑ ሌሎች አባላትም እየታደኑ ነው ተብሏል፡፡
በዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የቀበሌ መታወቂያ ሲጠይቁ ‹‹የእኛ አባል ካልሆንክ አንሰጥህም›› እንደሚባል የጠቀሱት አስተባባሪዎቹ አቶ ተመስገን የኔሀብቴ መታወቂያ በጠየቀበት ወቅት የቀበሌው ሊቀመንበር ቄስ እሱባለው ‹‹የእኛ አባል ካልሆንክ መታወቂያ አልሰጥህም›› በማለታቸው፣ እሱም ‹‹መብቴ ነው!›› ብሎ በመከራከሩ ነሃሴ 11/2007 ዓ.ም ‹‹እያንገራገረኝ ነው›› ብለው እንዳሳሰሩትና ነሃሴ 18/2007 ዓ.ም 1500 ብር ዋስ ከእስር ተለቅቆ እንደነበርም ተገልጾአል፡፡
በተመሳሳይ በአርሲ በቆጅ የሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ለክልል ምክር ቤት የተወዳደሩትና የሰርቦ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጃዋሩ ገልገሉ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የመንግስት አግልግሎት እንደማያገኙና በፖሊስ ተይዘው መታወቂያቸውን እንደተነጠቁም ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል ስለሆንኩ መታወቂያየን በግድ መጥቀውኛል፡፡ ይህ የእኛ መታወቂያ ነው፡፡ ምንም አታመጣም፡፡ ሂድና ሰማያዊ ይስጥህ›› ብለውኛል ሲሉም ገልጸውልናል፡፡

No comments: