Tuesday, May 12, 2015

ሰመጉ በሃመር ወረዳ የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ያጣራውን ሪፖርት ይፋ አደረገ

ሚያዝያ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) የአሁኑ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ)፣ በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመር ወረዳ ዲመካ ከተማና አካባቢው ከጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በተከሰተ ግጭት
በ7 ሰዎች የሞትና በ9 ሰዎች የመቁሰል አደጋ መድረሱን በጥናቱ አረጋግጧል። ሰመጉ ባለሙያዎቹን በደቡብ ኦሞ ዞን ጅንካ ከተማ እንዲገኙ በማድረግ የግጭቱን መንስኤና የደረሰውን ጉዳት ዓይነትና መጠን ለማጣራትና ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጿል።
አቶ ዑልዴ ሃይሳ በሐመር ወረዳ ሸንቆ ወልፎ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የነበረ አርብቶ አደር ሲሆን፣ ህዳር 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በድንገት በተነሣ አለመግባባት ምክንያት ባሌ ኢልዴ በተባለ የፖሊስ አባል ኩላሊቱ ላይ በከባድ እርግጫ በመመታቱ የአቶ ዑልዴ ህይወት በእለቱ
ህዳር 7 ሊያልፍ መቻሉን የገለጸው ሰመጉ፣ የሐመር ብሔረሰብ አባላት አቶ ዑልዴን የገደለው የፖሊስ አባል ሕግ ፊት ቀርቦ ባለመጠየቁ ከፍተኛ ቅሬታ አድሮባቸውና የመበደል ስሜት ውስጥ ገብተው እንደነበር አትቷል። ሐመር ወረዳ ውስጥ ማንጐ ተብሎ በሚጠራው
ፓርክ ጎሽ የገደሉ የሐመር ብሔረሰብ አባላት በሚል ሰዎቹን ለመያዝ ከደቡብ ኦሞ ዞን ፓሊስና ልዩ ኃይል የተውጣጡ አባላት ጥር 7/ 2007 ሥፍራው የደረሱ ሲሆን፣ የዞኑ ፖሊስና ልዩ ኃይል አባላት ሥፍራው በደረሱበት ወቅት የአካባቢው ሽማግሌዎች ሽምግልና
ተቀምጠው ማግኘታቸውን፣ ሸማግሌዎችና የማኅበረሰቡ አባላት የፖሊስን እንቅስቃሴና የተልእኮ ምክንያት ሲረዱ “በቅርቡ የተፈጸመውን የአቶ ዑልዴን ግድያ ሳታጣሩና ገዳዩን ይዛችሁ ለፍርድ ሳታቀርቡ፣ ከረዥም ጊዜ በፊት ጎሽ ገደለ የምትሉትን ሰው ለመያዝ
እንዴት መጣችሁ?” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ይዘረዝራል።
” የፖሊስና ልዩ ኃይል አባላቱ በወቅቱ የተሰጣቸው ግዳጅ ጎሽ የገደለን ሰው መያዝ ብቻ መሆኑን መግለጻቸውን፣ ፖሊስ የተላክሁበትን ግዳጅ እፈጽማለሁ ሲል፣ የሐመር ሽማግሌዎችና የማኅበረሰቡ አባላት ደግሞ የአቶ ዑልዴ ሃይሳን ገዳይ ሳትይዙ የጎሽ ገዳይ ልትይዙ
አትችሉም በሚል ተቋውሟቸውን ማሰማታቸውን ምርመራው ይጠቅሳል።
አለመግባባቱ እየተካረረ ሄዶ በዚያው ቀን ጥር 7 ቀን 2007 በሐመር ማኅበረሰብ አባላትና በፖሊሶች መካከል ተኩስ ተጀምሮ፣ ሰፋ ወዳለ ግጭት ማምራቱን፣ በግጭቱም 7 ሰዎች ሲሞቱ 9 ሰዎች መቁሰላቸውን ማረጋገጡን የሰመጉ 134ኛ ሪፖርት ያስረዳል።
ሰመጉ የሟቾችንና ስም ዝርዝር ያወጣ ሲሆን፣ በዝርዝሩ የሞቱትና ቆሰሉት አብዛኞቹ የደቡብ ኦሞ ዞን ፖሊስና የልዩ ሃይል አባላት ናቸው።
በግጭቱ ምክንያት የሟቾችን አስከሬን ለማንሳት ባለመቻሉ እስከ ጥር 10 ድረስ በስፋረው መቆየቱንም ገልጿል።
በግጭቱ ተሳታፊ ከነበሩት የሐመር ብሔረሰብ አባላት በኩል ምን ያህል ሰዎች ላይ ምን ዓይነት ጉዳት እንደደረሰ ለማጣራት የተቻለውን ያህል ጥረት ቢደረግም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አለመሳካቱን ሰመጉ ገልጿል።
ይህ ዘገባ በመጠናቀር ላይ እያለ በሐመር ወረዳ የመንግስት ሥራ ቆሞ፣ ት/ቤቶችም ተዘግተው እና በህዝቡ መሃል ውጥረቱም ጨምሮ እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን፣ ዘገባው እስከወጣበት እለት ደርስ ውጥረቱ እንዳለ ነው።
Source: Ethsat

No comments: