ሚያዝያ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመላ ሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ መብራት እየተቆራረጠ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በህዝቡ ጥያቄ የተወጠሩት የኢትዮጽያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ሃላፊ ሠራተኞቻቸውን ተጠያቂ አድርገዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የውጭ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ገብረእግዚአብሔር ታፈረ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ለመብራት መቆራረጥ መንስኤ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ምግባረ ብልሹ ሠራተኞቻቸው መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
ሃላፊው ተቋሙ ከ13 ሺ በላይ ሠራተኞች እንዳሉት በመጥቀስ አንዳንድ ስነምግባር የጎደላቸው ሰራተኞች ችግሩን እንደሚፈጥሩና ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለመፍታት እየጣሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ህብረተሰቡ ብልሹ ሠራተኞች ችግር ሲፈጥሩበት ስማቸውን እንኳን ባያውቀው ልዩ ምልክትና የሚንቀሳቀሱበት ሰዓትና የተሸከርካሪ ሰሌዳ በመያዝ እንዲጠቁምም ተማጽነዋል፡፡
ከዚህ ቀደምም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በተመሳሳይ ሁኔታ መንግስትና ሕዝብን ለማጣላት የሚያሴሩና ሳቦታጅ የሚሰሩ ሠራተኞች መኖራቸውን በመጥቀስ በጅምላ በሰራተኞች ላይ ዛቻ አከል መግለጫ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስአበባ በየቀኑ መብራት የሚጠፋ ሲሆን ሕዝቡም የራሱን ጥናት በማድረግ በዚህ ቀን የመብራት ተረኛ ነን፣ ይጠፋል በማለት ፕሮግራሙ ን ለማስተካከል ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ኢኮኖሚውም እያዘቀዘቀ መሆኑም ኢኮኖሚ
ባለሙያዎች አስተያየት ያስረዳል፡፡ መንግስት ከዚህ ቀደም የሃይል እጥረት እንደሌለና ችግሩ የስርጭት መሆኑን ሲጠቅስ ቆይቷል።
Source: Ethsat
No comments:
Post a Comment