Wednesday, May 13, 2015

ትግላችንን እንመርምር

ትግላችንን እንመርምር
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
አርብ፤ ሚያዝያ ፴ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት ( 5/8/2015 )
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ፤ “ትግላችን ወደፊት የሚሄደውና ለድል የሚበቃው፤ ሀገራዊ ራዕይ ይዘን፤ በአንድነት ስንሰለፍና ለአንድ ግብ ስንታገል ብቻ ነው!” በማለት አስፈላጊውን ውይይት ለማበረታታት ጽሑፎችን አቅርቤ ነበር። በዚህ ጽሑፍ ደግሞ፤ አሁን ያለንበትን በመመርመር፤ ወደፊት ለመሄድ፤ አሁንም ወሳኝ የሆነው፤ በአንድነት መነሳታችን መሆኑን አሰምርበታለሁ። ይሄን የማደርገው፤ እያንዳንዱን የትግል ድርጅትና ይህ የትግል ድርጅት የያዘውን የብቸኛ የትግል መንገድ በማየት፤ የዚህን የትግል ድርጅት እምነትና ተግባር በመመርመር፤ ብቸኛ ጉዞው ጎጂ መሆኑን በማስረገጥ ነው። በግልጽ መወያየትና እርስ በርሳችን መነጋገር ካልቻልን፤ በደፈናው የምናደርገው የትግል ጉዞ፤ የእሬያ ታጥቦ ጭቃነት ነው። እውነት ያዛልቃል። መሸፋፈን ጊዜ ያራዝማል፤ አያዋጣም። ጥሩ የሠሩትን ጥሩ፤ የጎደለባቸውን ደግሞ ጎደለ ማለት ሳንችል፤ በግትልትልነት ወደፊት እንሂድ ብንል፤ አንዱ ወደፊት አንዱ ወደ ኋላ እየተጓተትን፤ አንዳችን የሌላችን እንቅፋት መሆናችን የማይካድ ሀቅ ነው። የያዝነው ትግል፤ ከታጋዩ ክፍል አኳያ፤ ፈዞ ተቀምጧል።
እውነቱ ይገለጥና፤ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ተቆርቋሪነት ኖሯቸው፤ የዕለት ተዕለት ጉዳያቸው አድርገው፤ ሌት ተቀን የሚጥሩት፤ በትግል ድርጅቶች ውስጥ ተካተው እየታገሉ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። በመሠረቱ፤ እኒህ አባላቱ ያሉባቸው የትግል ድርጅቶች፤ ዓላማ አድርገው የያዙት፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ነፃነት ነው። መሪዎቻቸው በትክክልም ሆነ ትክክል ባልሆነ መንገድ ያካሂዱት፤ የሚያካሂዱት፤ የሕዝቡን ትግል ነው። በዚህ ከፍ ያለ አድናቆቴን እስጣለሁ። በተለይም በሚያውቁትና በለመዱት የሚያደርጉት ጥረት፤ ተቆርቋሪነታቸውንና ኢትዮጵያዊነታቸውን በግልጽ ያስረዳናል። ሁላችን በትግል ድርጅቶች ያልተካተትን ኢትዮጵያዊያን፤ በነዚህ የትግል ድርጅቶች ውስጥ ለሚገኙ አባላት፤ ባለውለታዎቻቸው ነን። እኒህ አባላት ናቸው ትግሉን ከፊት ለፊት እንዲታይ ችቦ አብርተው፤ ብርሃን በመሥጠት፤ እያውለበለቡ ያቆሙት። በርግጥ በሀገራችን ያለው አምባገነን ወገንተኛ ገዥ ክፍል፤ በኢትዮጵያን ሕዝብ ላይ ማነቆ ሆኖ፤ የሚያደርገው ፀረ-ኢትዮጵያ እርምጃ፤ ለትግሉ መሠረታዊ ሕይወቱ ነው። ያ ባይኖር ትግሉ አይኖርም። ትግሉ ደግሞ አቀጣጣይና መስዋዕት የሚከፍሉና ችቦውን የሚያበሩ ታታሪ ኢትዮጵያዊያንን ጠይቋል። ይህን በሀገር ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በመክፈል ላይ ያሉት፤ የሰማያዊ ፓርቲ፣ የአንድነት ፓርቲ፣ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ናቸው። ከሀገር ውጭ ደግሞ አባሎቻቸውን አሰባስበው በትግሉ መድረክ ላይ ያሉት፤ የኢሕአፓ (ዴሞክራሲ)፣ የኢሕአፓ፣ የአርበኞች ግንባር፣ የግንቦት ሰባት፣ በሸንጎና በሽግግር መንግሥት ድርጅቶች ናቸው። ያ እንዳለ ሆኖ፤ የትግል መድረኩን አጣበው የያዙት እኒሁ የትግል ድርጅቶች፤ ትግሉን ወደፊት በመግፋት ደረጃ ጉድለት አሳይተዋል። ይህ መመርመር አለበት። ትግሉ ወደፊት ከመሄድ ይልቅ ባለበት እየረገጠ ነው። ለምን?
በመድረክ ብቅ ብለው የጠፉትን ትተን፤ አሁን በትግሉ ላይ ያሉትን የትግል ድርጅቶች ብንመረምር፤ በትግሉ የቆዩና አዲስ የመጡ ናቸው። መቆየታቸው የሚያስመሰግናቸው፤ አዲስ መሆናቸው የሚጎዳቸው አይደለም። ይልቁንስ የትግል ታሪክን እንደ መመኪያና መኩሪያ፤ አዲስነትን እንደ ንጽሕናና አዲስ ሃሳብ አቅራቢነት ማውለብለቡ ጎጂ ነው። ሁሉም ቢሆኑ ወደፊት ለመሄድ ፈላጊዎች፤ በአንድነት ለመሥራት ተጎታቾች ናቸው። እዚህ ላይ፤ በድጋሚ፤ ትኩረት አድርጌ የምንመለከታቸው፤ ኢትዮጵያዊ ታጋይ ድርጅቶችን ነው። እያንዳንዱን የትግል ድርጅት፣ ይህ የትግል ድርጅት የያዘውን እምነትና ያከናወነውን ተግባር ካደረገው ግስጋሴ ጋር እንመልከት።
ታጋይ ድርጅቶች፤
ሰማያዊ ፓርቲ፤ የሰማያዊ ፓርቲ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መወገድ ያለበት በትጥቅ ትግል ሳይሆን፤ በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው ብሎ ያምናል። ከገዥው መንግሥት የሚለይበትን ሀገራዊ አቋሞች በግልጽ ለሕዝብ አስቀምጦ፤ ሕዝቡን በማሰለፍ ከግቡ ለመድረስ ተነስቷል። ለዚህም በሕገ መንግሥቱ መሠረት፤ ደንቡን ተከትሎ፤ ድርጅታዊ መብቱን በማስከበር፤ ትግሉ ከሚጠይቀው በላይ ከባድ መስዋዕትነት እየከፈለ፤ በመታገል ላይ ነው። በመግለጫዎቹ፤ የገዥው ቡድን ዕለት በዕለት በድርጅቱና በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰውን በደል ይዘረዝራል። የራሱን እንቅስቃሴ ያትታል። ትግሉ ያስገኘውን ድልና የወደፊት ሂደቱን በሚመለከት ወደፊት አመልካች እምነቱን አልሠጠንም። የ “ወጣቱ ሰዓት” የሚል ትርጉም የሌለው ሰንደቅ ያውለበልባል። የሀገር ጉዳይ የወጣቱ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ሁሉም እኩል ተቆርቋሪ ነው። ሀገርን በአንድነት እንጂ በአንድ የኅብረተሰብ ወገን የሚያዝና የሚዘወር አይደለም። የወጣቱን ድርሻ ማጉላትና “የወጣቶች ፓርቲ” ማለት የተለያዩ ናቸው።
ትክክለኛው የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት እና ከአንድነት ፓርቲ በትክክል የተረፈው ክፍል፤ እኒህ ሁለት ክፍሎች፤ በዚሁ በሰማያዊ ፓርቲ ግላጼ የሚካተቱ ናቸው። አንድነት በመጨረሻ የወሰደው የግዴታ ውሳኔ፤ አኩሪ ነው። ከዚያም ሰማያዊን እንዲቀላቀሉ አባላቱን ማበረታታቱ ሀቀኛነቱን ያሳያል።
በተረፈ፤ በገዥው ቡድን ተጠልፈው፤ እሱኑ ለማገልገል የተኮለኮሉት ተቀጽላዎቹን፤ የገዥው ቡድን ቡችሎች ናቸው ብሎ ማለፍ ይቻላል። አዲስ በገዥው ቡድን የተፈጠሩም አገልጋዮች አሉ። ጥፍሩን ከሰውየው መለየት አይቻልም።
መድረክ፤ ከተለያዩ የትውልድ ቆጣሪ ወገንተኛ የፖለቲካ ድርጅቶች የተዋቀረው መድረክ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መወገድ አለበት ብሎ ያምናል። መወገድ ያለበትም በትክክለኛ ምርጫ ነው፤ ይላል። ተወዳዳሪን ሁሉ ጠላት ብሎ የፈረጀው ገዥ ቡድን፤ ይኼንና ሌሎች ተቃዋሚዎቹን በጭፍን እያደነ ለማጥፋት ሌት ተቀን ይጥራል። እናም ይህ መድረክ፤ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር፤ ሥልጣን ለመውሰድ፤ “እወዳደራለሁ!” ብሎ ቆሟል። “ልዩነታችን መሠረታዊ ሳይሆን፤ እነሱ በሥልጣን ላይ መሆናቸውና እኛ ተቃዋሚ መሆናችን ነው!” በማለት፤ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት በፓርላማ አቸንፈው ሥልጣን ለመያዝ፤ ከፍተኛ መስዋዕት እየከፈሉ በፖለቲካው መድረክ አሉ። ምን ዓይነት ስምምነት በመድረክ አባል ድርጅቶች መካከል እንዳለ እኔ አላውቅም። መድረክ ሥልጣን ቢወስድ፤ መድረክ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በተጻራሪ፤ በፖለቲካ ፍልስፍናም ሆነ በአስተዳደር መመሪያ፤ ምን እንደሚያቀርብ አይታወቅም። አባላቱ በምን ተስማምተው በምን እንደሚለያዩ አላውቅም። እናም መድረክ ከገዥው ቡድን ጋር ያለው ልዩነት ሆነ አንድነት ምን እንደሆነ፤ ግልጽ አይደለም። በርግጥ አባል ድርጅቶቹ ሙሉ ጊዜያቸውን፤ የገዥውን ቡድን በማውገዝና በማጋለጥ ያውላሉ።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ፤ ዴሞክራሲያዊ (ኢሕአፓ ዴሞክራሲያዊ ) እና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፤ እኒህ ሁለት ድርጅቶች፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንድ የትግል ድርጅት ነበሩ። ይህ የትግል ድርጅት፤ ከአርባ ዓመት በላይ የትግል ታሪክ ያለውና የመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲ ነበር። አሁን ያሉት እኒህ ሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች፤ በመካከላቸው ያለው ልዩነት፤ እንኳንስ ለውጭ ኢትዮጵያዊያን፤ ለራሳቸው አባላት እንኳ ግልጽ ሳይሆን፤ ግማሽ እግራቸውን በትላንት ትግላቸው፤ ሌላውን ደግሞ በምኞታቸው ተክለው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ በሰላምም ሆነ በትጥቅ ትግልም መወገድ አለበት ብለው በፖለቲካ ምኅዳሩ አሉ። ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ያላቸውን ልዩነት እንደ ሰላማዊ ፓርቲው ግልጽ አውጥተውና ሕዝቡ እንዲያውቀው ባያደርጉም፤ እንደ ግንቦት ሰባት የተሸፋፈነ አይደለም። እንደሌሎቹ ሁሉ አብዛኛዎቹ መግለጫዎቻቸው የወጡትና ሕዝቡ የሚያውቃቸው፤ የገዥውን ቡድን በማውገዝና ወንጀሉን በመዘርዘር ላይ ያተኮሩ ናቸው። ለምን አመርቂ የሆነ ትብብር ከሌሎች የትግል ድርጅቶች ጋር ፈጥረው መሄድ እንዳልቻሉና በተለይም በመካከላቸው ስምምነት ፈጥረው ለምን ወደፊት እንደማይሄዱ ለኔ ግልጽ አይደለም። በቅርብ ጊዜ ከውጭ ሁለቱን ለማቀራረብ የተደረገው ጥረት በአንደኛው ወገን ተቀባይነት እንዳላገኘ ተረድቻለሁ። የሚገርም ነው!
ምናልባት አለሁ ካለ፤ የመላ ኢትዮጵያ ሶሺያሊስት ንቅናቄ ( መኢሶን ) በዚሁ በኢሕአፓ ምዘና ይካተታል።
ግንቦት ሰባት፤ ግንቦት ሰባት በቅርብ ከተቋቋሙት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው። ይኼም ለሁለት ተከፍሎ ግንቦት ሰባት ዴሞክራሲ የሚባል ክፍል መኖሩን ተገንዝቤያለሁ። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መወገድ ያለበት በሰላማዊ መንገድ ሳይሆን፤ በትጥቅ ትግል ብቻ ነው ብሎ ያምናል። የሰላማዊ ትግሉ ወቅት አብቅቶለታል ብሎ ፈርጇል። “እኔ ንቅናቄ እንጂ ፓርቲ አይደለሁም!” በማለት፤ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የሚለይበትን የመርኀ ግብር ልዩነት በደንብ ሳያስቀምጥ፤ መሠረታዊ በሆኑ ሀገር አቀፍ ጉዳዮች ላይ አቋም ሳይወስድ ወይንም አቋሙ ሳይታወቅ፤ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ማስወገድና መተካት ላይ ብቻ በተመሠረተ የትጥቅ ትግል መርኅ፤ ተነስቷል። ለዚህም የግድ የጎረቤት መንግሥት መጠጊያና ዕርዳታ ያስፈልገናልና፤ ኤርትራ ብቸኛ አማራጫችን ናት፤ በማለት ኤርትራ ከትሟል። መግለጫዎቹና ትንተናው የሚያተኩረው በገዥው ቡድን ወንጀል ላይ ብቻ ነው። ከዚያ በተረፈ፤ ስለ ትጥቅ ትግል አስፈጻሚ አካሉ ትልቅነትና ጉልበት ብዙ ሲተርክ፤ ስለ አከናወናቸው ተግባራትና ግኝቶቹ ግን የተጨበጠ ነገር አልገለጸልንም።
አሁን የዚህ ድርጅት የሜዳ ወታደር የሆነውን የአርበኞች ግንባር፤ ከዚህ ጋር ለጥፈን የምናየው ይሆናል።
እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት ድርጅቶች፤ በሙሉ ልባቸው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱ እንዳልተከበረለትና መከበር እንዳለባቸው ሁሉም ይናገራሉ። የሕዝቡ ድምጽ እንደተሰረቀና፤ ገዥው ቡድን እንዳፈተተው ሀገሪቱን መግዛቱን ይናገራሉ። “እኔ የያዝኩት ትግል ነው ትክክል!” ብለው ጽኑ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል። ሁሉም ደግሞ በውስጣቸው፤ በግልጽ ባያወጡትምና ባደባባይ ባያቀነቅኑትም፤ “ሌሎች ትክክል አይደሉም!” የሚል እምነት አላቸው። ከዚህም የተነሳ፤ እንኳንስ ሁሉም በአንድነት የሚካተቱበት፤ በጣም ተቀራራቢ የሆኑ ሁለቱ እንኳን የሚናቆሩበት ሠፈር ላይ ነው ያሉት። እስኪ እምነታቸውንና ተግባራቸውን እንመርምር።
እምነታቸውና ተግባራቸው፤
ግንቦት ሰባት፣ ግንቦት ሰባት ዴሞክራሲና፣ አርበኞች ግንባር፤ በአሁን ሰዓት፤ ግንቦት ሰባት የፖለቲካ ክፍል ሆኖና፤ አርበኞች ግንባር ወታደራዊ ክፍሉ ሆኖ፤ ባንድነት ተጣምረው ግንቦት ሰባት አርበኞች ግንባር መባላቸውን ገልጸውልናል። ግንቦት ሰባት ዴሞክራሲ ደግሞ ዋናውን ትግሉን በግንቦት ሰባት ላይ ወድሮ ተነስቷል። በመጀመሪያ ግንቦት ሰባት ፓርቲ ስላልሆነ፤ ምንድን ነው ፕሮግራሙ ብለን እንዳንመረምር እጃችን ተይዟል። ቀጥሎ ደግሞ በትጥቅ ትግል ነው የማምነው ብሎ ተነስቷል። በመሠረቱ የትጥቅ ትግል፤ አጠቃላይ ትግሉን በሚመራው ድርጅት ስሌት፤ የትግሉ አንድ ክፍል ሆኖ፤ ይህ ድርጅት ሥልጣን ከገዥው ቡድን ነጥቆ ለመውሰድ በሚደረገው የፖለቲካ ትግል፤ ትግሉ አንድ ደረጃ ላይ ሲደርስ፤ ወሳኝ ሚና ለመጫወት የሚወሰድ የፖለቲካ ጎዳና ነው። የትጥቅ ትግሉ፤ የፖለቲካ ትግሉ መደጎሚያ እንጂ፤ ራሱን የቻለ ብቸኛ መሣሪያ አይደለም። የትጥቅ ትግሉ የበላይነትን የሚወስድበት ቦታ አለ። ትግሉ የነፃነት ነው ተብሎ ከተፈረጀና፤ ሀገር ነፃ አውጪ አንድና አንድ ብቻ ድርጅት በትግሉ መድረክ ሲወጣ፤ አማራጭ በሌለው መንገድ ትጥቅ ትግሉ ወሳኝና ብቸኛ ሆኖ ይወሰዳል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ አምባገነን መንግሥት በሀገር ሲበቅልና የሰላማዊ ትግሉ መተንፈሻ ቀዳዳው ሲዘጋ፤ አሁንም ሕዝቡ በአንድነት ተነስቶ፤ አንድ ድርጅት አበጅቶ፤ ይኼን አምባገነን መንግሥት ለመጣል፤ ታጥቆ ሊነሳ ይችላል። በዚያ ወቅት ያለው ግብግብ፤ በሕዝቡና በወራሪው መንግሥት መካከል ብቻ ይሆናል። ሶስተኛ ድርጅት ወይንም ሠፈር የለም።
አሁን ባለው የሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ፤ ይህ ተጨባጭ ሁኔታ አልተከሰተም። አንድነት ሁሉን ያስተባበረ ድርጅት የለም። እናም ትግሉ በየድርጅቶቹና በገዥው ቡድን መካከል ሆኗል። አንዱ ድርጅት ቢያቸንፍ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ወታደርን በራሱ ወታደር ለመተካት የሚሯሯጥበት ሁኔታ ነው ያለው። በመጀመሪያ፤ ይህ ጸሐፊ፤ በሀገራችን አሁን ያለው የነፃነት ትግል ነው ብሎ ቢያምንም፤ ባጠቃላይ ይህ ሃሳብ ተቀባይነቱ አልተረጋገጠም። ከዚያ በላይ ደግሞ፤ ይህን ትግል አቅፎና የኔ ብሎ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ድርጅት ብቻ አሰልፎ አልተነሳም። ስለዚህ፤ ግንቦት ሰባት እያደረገ ያለው ትግል፤ የግንቦት ሰባት እንጂ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል አይደለም። ከዚያ አልፎ፤ በኤርትራ በመመሸጉ፤ ፍጹም ሕዝባዊና ኢትዮጵያዊ ያልሆነ አቋም ወስዷል፤ ፀረ-ኢትዮጵያ ተግባር ፈጽሟል።
እንመልከት፤ የወደፊቱን ለመወሰን ያለፈውን ማጥናት ግዴታ ነው። በርግጥ ያለፈ ድርጊት የወደፊት ሂደትን አይወስንም። ነገር ግን፤ ባጠቃላይ ስንመረምር፤ ታሪካችን ማንነታችንን ይነግረናል። በኤርትራ ያለው መንግሥት በምንም መለኪያ ቢታይ፤ አምባገነንና ፀረ-ኢትዮጵያ ነው። በዚህ ላይ መተማመን አለብን። ፀረ-የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የሆነ ሁሉ፤ የኢትዮጵያዊያን ወገን አይደለም። አል ሸባብም ፀረ-የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ነው። ይህ ግን፤ የኢትዮጵያዊያን ወገን አያደርገውም። ስለዚህ የኢሳያስ አፈወርቂ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥትን ተቃዋሚነት መመርመር ያለበት፤ ከምን ተነስቶ ነው ከሚለው ምንጭ ነው። አለያ “እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው።” ይሆናል። ኢሳያስ ፀረ-የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የሆነው፤ እኔ አግዣችሁ አዲስ አበባ ገብታችሁ፤ ለምን በኢትዮጵያዊያን ላይ እንደልቤ አልጨፍርባችሁም ብሎ ነው። ለዚህ ደግሞ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ዝግጁ ነበር። በውስጡ ያሉ ኢትዮጵያዊያን አስቸገሩ። በመንግሥት ውስጥ ያሉም፣ በትግራይ ውስጥ ያሉም፣ በቀሪው ኢትዮጵያ ያሉትም፤ ከትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር አባላትም ጭምር፤ በመለሰ ዜናዊና አፍቃሪ-ኤርትራ ቅርንጫፉ ላይ ተቃውሞ ተነሳበት። እናም የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ ሳይወድ የፀረ-ኢሳያስ ጥብቆ ለበሰ። ስለዚህ ኢሳያስ አኮረፈ። አሁንም ኢሳያስ የሚደግፈው፤ እሱ እንደልቡ የሚጨፍርበትን መንግሥት አዲስ አበባ ላይ ለማቆም ነው።
የኢሳያስን ጥቅም ተኮር ፀረ-የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መሆን እንደ መሠረታዊ ልዩነት ቆጥሮ የትግል ስልትን መቀመር፤ ጉዳት አለው። በመሠረቱ ኤርትራ ሄዶ መመሸግ፤ የትግሉን አጠቃላይ ሂደትና ተጨባጩን የፖለቲካ ሀቅ የማገናዘብ ጉድለት መኖሩን ያሳያል። በትግል ስልት ስሌት፤ በኢትዮጵያ ያለው የገዥ ቡድን፤ ከላይ የተንጠለጠለ ግልጽ ጠላት ነው። እናም በፍርሃት የተዋጠ፤ በሕዝቡ የተተፋ ነው። ስለዚህ የትግል ስልቱ ከዚህ መነሳት አለበት። በርግጥ አምስት ለአንድ ሕዝቡን ጠፍርቆ፤ በስለላ ድርጅቱ ተማምኖ፤ ወታደራዊ ኃይሉን በታማኝ አባላቱ አዋቅሮ፤ የሀገሪቱን ንብረት በጥፍሩ ሽብሽቦ፤ ሀገራችንን እስር ቤት አድርጓታል። ይህ ግን ውስጡ ለቄስ ነው። ገልቦ ሲያዩት ውስጡ ባዶ ነው። ይህን በስሌት ማስገባት ግድ ይላል። ሰላማዊም ሆነ ትጥቅ ትግሉ፤ የግድ የውጭ ሀገርን ምሽግና ድጋፍ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያዊያንን የትግል አንድነት ነው የሚሻው። ሕዝቡ በአንድነት የተነሳ ዕለት፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የቀብር ደወል ይደወላል። ስለዚህ የትናንቱ “ከገጠር ወደ ከተማ ዘመቻ!” የትናንት ነው።
በተጨማሪ ደግሞ፤ የዓለም አቀፉ የፖለቲካ ተጨባጭ ሀቅ፤ በሀገራችን ለምናደርገው ትግል ያለው ተፅዕኖ መጠናት አለበት። በአሁኑ ሰዓት የዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ፤ የዓለምን የፖለቲካ እውነታ በትንሽ ጣቷ ጥፍር እያሽከረከረችው ነው። እናም “ፀረ-ሽብር” በሚል ደመና ሽፋን፤ አምባገነኖችን መደገፍ፤ ለጥቅሟ ያልሰገዱላትንና የምትጠላቸውን ማግለል፤ ደንታ በሌለው መንገድ የሀገራትን ሕልውና በመበጥበጥ ላይ ነች። አፍጋኒስታንን፣ ኢራቅን፣ ሊቢያን፣ ግብጽን፣ የመንን፣ በምን ዓይነት ሁኔታ እንዳስቀመጠቻቸው ለሁላችን ግልጽ ነው። ስለዚህ ይህ በኛ ሁኔታ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ሀቅ፤ በተለይም “ከኢሳያስ ጋር አብሮ መገኘቱ፤ ይህን ታጋዩ ክፍል ምን ላይ ሊስቀምጠው ይችላል?” የሚለውን ማጥናት አለብን። ወሳኝ አይደለም፤ ነገር ግን በትግል ሂደቱ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጫና ማንሰላሰል ያስፈልጋል።
ሰማያዊ ፓርቲና ሀገር ውስጥ ያሉ ታጋይ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች፤ እኒህ ድርጅቶች፤ በሀገሪቱ ውስጥ ባለው የምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ የሚተዳደሩ ናቸው። በሰላም ከመታገል ይልቅ፤ በተቃዋሚነት በሕገ-መንግሥቱ ሥር እንዲተዳደሩ በሁሉም አቅጣጫ እየተወገሩ ናቸው። የውጭ መንግሥታትም ይሄኑ ነው የሚወዱት። ችግሩ፤ የራሱን ሕገ-መንግሥት የማያከብር የገዥ ቡድን ስለነገሠ፤ የሕግ የበላይነት በኢትዮጵያ የለም። እናም ትግላቸውን፤ ሕጉ በፈቀደው መሠረት ለማከናወን ቢሯሯጡም፤ ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነው ገዥ ቡድን፤ ቀዳዳ ላለመሥጠት፤ ሊያጠፋቸው ቀን ከሌት ይጥራል። በውጭ መንግሥታት ዴሞክራሲያዊ አሠራርን የሚከተል መስሎ ለመታየት ሕልውናቸውን ይቀበል እንጂ፤ እንደ ጠላት መቁጠሩና ሊያጫጫቸው መጣሩ ግልጽ ነው። ግራ የገባው፤ ለምን በሱ ፈቃድ አጃቢ ድርጅቶቹ አልሆኑለት እንዳሉ ነው። በዚህም ሰላማዊ ትግሉን ይዘውታል። በርግጥ ዕለት ከዕለት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥትን የግፍ ፅዋ የሚቀበሉት፤ ሀገር ቤት ያሉት እኒሁ ወገናችን ነው። እናም ትግሉ መሆንና መመራት ያለበት በሀገራችን ውስጥ ነው። ይህ ማለት ግን፤ ገዥው ቡድን በሚፈቅደውና በሚፈልገው መንገድ መንጎድ ማለት አይደለም። ትግላቸው ወደፊት ሊጓዝ የሚያስፈልገውን መስዋዕትነት እየከፈሉ ቢሆኑም፤ ትግሉን ወደፊት ከመግፋት አኳያ መተለም ያለበትንና መከተል ያለባቸውን የትግል መርኅ፤ መሪዎቻቸው እንደገና መመርመር አለባቸው። የትግሉን ሂደት ማሳመርና የሕዝቡን ተሳትፎ ማሳደግ የሚችል ቅየሳ ያስፈልጋል።
መቃወም ማለት እምቢተኛ መሆን ማለት ነው። ሰላማዊ ትግል ማለት፤ በእምቢተኛነት የሚከተለውን መስዋዕትነት እየከፈሉ፤ ሕዝብን ለትግል ማነሳሳት ማለት ነው። በዚህ ረገድ የሚችሉትን እያደረጉ ነው። ይህ ግን በቂ አይደለም። መስዋዕትነቱን ከማንም በላይ እየከፈሉ ነው። ጥረት እያደረጉ ነው። መንገዳቸውን ደጋግመው መመርመር አለባቸው። በተቻለ መንገድ ትኩረታቸው ሕዝቡን በማደራጀትና ወደ ትግሉ ጎዳና በመሳብ የታጋዩን ቁጥር የሚያሳድግ መሆን አለበት።
ቀሪዎቹ በውጭ ሀገር ያሉ የትግል ድርጅቶች፤ መቀመጫቸውን ከሀገር ውጪ በማድረግ ትግሉን የሚገፉ ድርጅቶች አሉ። እኒህ ድርጅቶች፤ አባላትን በመመልመል፤ ድርጅታዊ ስነ ሥርዓትን በማስከበርና በውጭ መንግሥታት ዘንድ መኖራቸውን በማሳወቅ ተጠምደዋል። የገዥውን ቡድን የዕለት ተዕለት ግፍ ባይጎነትላቸውም፤ ይህንና የሀገሪቱን ንብረት ዘረፋ በማጋለጥ ላይ ናቸው። ሕጋዊነታቸውን በሀገር ውስጥ ስለተነፈጉና ከሰላማዊ ትግሉ በተጨማሪ አስፈላጊ ከሆነ በትጥቅም ትግል ለመሳተፍ ዝግጁ ስለሆኑ፤ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሀገር ቤት ጋር ካለው ሕዝባዊ አመጽ ጋር ምን ያህል እንደተቆራኘ ማወቅ ያስቸግራል። ሀገር ቤት ውስጥ በሕቡዕ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ምን ያህል ያን በተግባር አውለውታል? የሚለውን መገምገም አይቻልም።
ማሳረጊያ፤
እያንዳንዱ የትግል ድርጅት በትግሉ ላይ፤ የራሱን መርኀ-ግብር ጠምዶ እየተሯሯጠ ነው። ይህ ትግል፤ በድርጅቶችና በግለሰቦች ጥረት አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ደርሷል። አሁን ያለበት ደረጃ ደግሞ ባለህበት እርገጥ ነው። ከዚህ መውጣት አለብን። ለዚህ ደግሞ፤ በሀገራችን ላይ ያለው ተጨባጭ የፖለቲካ ሀቅ ምንድን ነው? ያለው መንግሥት ምን ዓይነት መንግሥት ነው? ሕዝቡ አሁን በምን ዓይነት የኑሮ እውነታ እየተገዛ ነው? ምን ዓይነት ትግል ነው ማካሄድ የሚያስፈልገው? ምን ዓይነት ድርጅት ነው የሚሻለው? እንዴት እንታገል? የሚከተለው መንግሥት ምን መሆን አለበት? እና እነዚህን ለመሳሰሉት ጥያቄዎች፤ ድርጅቶች ተሰብስበው ሀገራዊ መልስ አልሠጧቸውም። እናም ትግሉ ሀገራዊ አልሆነም። ሁላችን እንደምንረዳው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሀገራችን በጣም አስጊ ወደ ሆነ ሁኔታ እየዘቀጠች ነው። ስለዚህ አሁን ኃላፊነቱ፤ በድርጅቶች ውስጥ በተካተቱት ኢትዮጵያዊያን ብቻ የተወሰነ አይደለም። ሀገሪቱ የሁላችን ናት። ስለዚህ፤ ሁላችንም ሀገራዊ ትግሉን የራሳችን አድርገን ለመሰባሰብ፤ ጊዜው አሁን ነው። ተጠያቂዎቹ እኛው ነን። እናም ሀገራዊ ስብስቡ፤ አሁን መደረግ አለበት። ድርጅቶች በየድርጅቶቻቸው መርኀ-ግብር መሠረት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፤ ትግሉን ሀገራዊ አያደርገውም። ሀገራዊ ትግሉ የሚቀጥሉትን የትግል መርኆዎች ያዘለ ነው።
፩ኛ. የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነን – የፖለቲካ ተሳትፏችን በትውልዳችን ሳይሆን በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ ይወሰናል።
፪ኛ. ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ለም መሬቷና ዳር ደንበሯ የሚጠበቅና የኢትዮጵያዊያን ነው።
፫ኛ. እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን፤ በትውልድ፣ በፆታ፣ በእምነት ሳንለያይ፤ እኩል የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብታችን የተከበረበት መሆን አለበት።
፬ኝ. በሀገራችን በኢትዮጵያ፤ የሕግ የበላይነት መስፈን አለበት።
በነዚህ ነጥቦች ዙሪያ፤ ሁላችንን ታጋይ ኢትዮጵያዊያንን ያጠቃለለ ሕዝባዊ ንቅናቄ ማድረግ አለብን። ይህ ሁላችንን ያሰባስባል። ይህ የወደፊቱን በአስተማማኝ ሁኔታ ትክክለኛና ኢትዮጵያዊ ያደርገዋል።። እያንዳንዳችን ወደንና አምነንበት ከተስማማንና ሁላችን በአንድ ከተጠቃለልን፤ የግድ ዴሞክራሲያዊ ነው። ኢትዮጵያዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የምንፈልጋቸው ዕሴቶች ናቸው። ስለዚህ ለዚህ ሁላችን መጣር አለብን። በርግጥ ይህ አዲስ አይደለም። በተደጋጋሚ የተባለና የታወቀ ነው። ችግሩ ግን ለዚህ ሁሉ፤ ሁላችን በአንድነት ጥረት አለማድረጋችን ነው። “ሌሎች እሽ አይሉም እንጂ እኔማ አስማማለሁ። መቼ እምቢ ብዬ!” ባዩ ብዙ ነው። ጥሩ፤ እንግዲያውስ እሽ ባዮች እንሰባሰብ።
በአሁኑ ሰዓት “አለቀለት!” ብለው እጃቸውን ለገዥው ቡድን የሠጡ አሉ። በድርጅቶች አመካኝተው፤ ትርፍራፊ ለመቃረም ፊታቸውን ወደ አዲስ አበባ ያዞሩ አሉ። ይህ ትግል ዘለቄታ የለውም ብለው ተስፋ የቆረጡ አሉ። ትናንት “አካኬ ዘራፍ!” ሲሉ እንዳልነበሩ ሁሉ፤ ዛሬ “እኔ ከፖለቲካው ዓለም ወጥቻለሁ!” ብለው፤ ሆዳቸውን ለመሙላት ለባርነት ወደ ገዥው የተጠጉ አሉ። ይህ ትግል በግለሰቦች ፍላጎትና ምርጫ የሚካሄድ ሳይሆን፤ ሀገራችን ባለው የፖለቲካ ሀቅ የሚሽከረከር ነው። ትግሉ ይቀጥላል። ስኬትን የማሳመር ኃላፊነት እንጂ፤ ትግሉን የማካሄድ ኃላፊነት አይደለም የተጣለብን። ትግሉ ምንም ይሁን ምንም! ይቀጥላል። ስኬቱ እንዲያምር ድርሻችንን እናሳምር። ድርጅቶች ይሄን ዕድል ተጠቅመው ማስተባበሩን ቢያመቻቹ የተሻለ ነው። እነሱ ያድረጉት ብለን ሌሎች ነፃ ልንወጣ አንችልም። ሌሎችም እኩል ኃላፊነቱ አለብን። መተባበር ለሀገር ሲባል ነው። መለያየት ለራስ የግል ጥቅም ሲባል ነው። ትግሉ ማዕከል ካልኖረው፤ ትግሉ ወደፊት አይሄድም። ሸንጎ ይህን ትልቅ ኃላፊነት መውሰድ ይቻላል። የሚችለው ግን፤ ከላይ እንደጠቆምኩት ኢትዮጵያዊ ግለሰቦችንና ኢትዮጵያዊ ድርጅቶችን በማሰባሰብ ብቻ ነው። ትውልዱን ከቆጠረ፤ ከገዥው ምን ለየው? ለነገ የሚተርፍ ትግል ዛሬ እየቀመምን፤ ወደፊት መሄድ አንችልም።
ከያንዳንዱ ድርጅት ጥሩ ጥሩ ወገኑን በመውሰድ የበለጠ አንድ ጠንካራ ድርጅት መመሥረት እንችላል። ያሉት ወደዚህ ድርጅት እንዲመጡ ማድረግ አለብን። የትግል ማዕከል መኖሩ ወሳኝ ነው። ወሳኝ ከሆነ ደግሞ፤ ያንን ማድረጉ የርስዎና የኔ ኃላፊነት ነው። እናድርገው።
Source: eske.meche

No comments: