Tuesday, May 12, 2015

ህሊና። – ከሥርጉተ ሥላሴ

andargachew new picture
ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ
እንዴትናችሁ ተክሊሎቼ? ከወር በፊት በተከታታይ ሞቢንግ (Mobbing) በእጅ ስልኬ ተላከልኝ፤ የመጀመሪያው እናታችን ቅድስ ድንግል ማርያምን (x) ተደርጎ ከአድህኖ ምስሏ ጋር፤ ቀጥሎ ደግሞ (No more Andargachaw Tsige) በሳቅና በስላቅ የተንቆጠቆጠ በደስታ – ፈንድቆ ። አልሰረዝኩትም አለ። አይደለም የአውሬው ግንድ ቅርንጫፎችም ሳይቀር ያውቁታል – የብቀላና የጭካኔ ጥንስስ ሆነ ዝልልሉን። እኛ ነን ሁልጊዜ እንደ አዲስ የሚገርመን – እንደሰማን በዛ ዙሪያ ብቻ እርብርብ በማድረግ መሠረታዊና የችግሩ ምንጭ ለሆነው፤ መፍትሄ ሊሆን ዬሚገባውን አቅም የምናባክንው።
ናፍቆት እስክንድር የጽንስ ጊዜው ከ ዓለም ጽንሶች ሁሉ ተለይቶ በእስር ነበር 9 ወራት ከ5 ቀናት ያሳለፈው። መሬትን ሲያያትም በእስር ነበር። ዛሬም – በስደት በወላጅ አባትና በባዕት ፍቅር ናፍቆት – እስር። ጋዜጠኛና መምህር ርዕዮት ዓለሙን የሚጠብቃት ምንድነው ብለን ይሆን የምናስበው። ሴቶች እጅግ ከምንፈራው በሽታ ጋር ካለምንም መልካም አያያዝ በር ተዝግቶባት ሞትን የምትጠበቅ የቅኔ ቀንበጥ ናት። ጋዜጠኛ ውብሸት ሆነ ጋዜጠኛ ተመስገንም የከፋውን የእስር መከራ እንዲቀበሉ ህማማቸው በበለጠ ስቃይ እንዲወቃቸው የተበዬነባቸው ናቸው፤ እጅግ ብዙ ሥማቸው የማናውቀው ከቀበሌ እስከ ክፍለሀገር ያሉ የበቀል ማወራረጃ ድውለት የሆኑ፤ በዕምነታቸው በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ወይንም በጎሳቸው የተሰቃዩ የሥጋና የደም መንፈሶቻችን በዚህ መልክ ሁሉንም መከራ ተቀብለው አልፋዋል። የጎጥ ማንፌስቶ እንዲቀጥል በድምጽ እስከሞሸርነው ድረስ ከሮና ከፍቶ ሰቀቀኑ ይቀጥላል። ቢመረንም ሃቁ ይሄው ነው።
ትውልድ ከቶውንም ደግሞ የማይተካቸው እኒያ ግልጽና ቀጥተኛ፤ ወደፊትና ወደ ኋላ የማይሉት ሰማዕቱ ሙሑር ፕ/አስራት ወልደዬስን ማነው ሁለመናቸውን ድቅቅ አድርጎ በአካላቸው ላይ የከፋ የቋሳ ጉዳት አድርሶ ለሞት የዳረጋቸው? የቋሳና የጎሳ ፖለቲካ አስዲ ፈል የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ነው።
ቀድሞ በማዬት፤ በታማኝነት አደራን አብቅሎ በመወጣት አንቱ የነበሩት አርበኛ ሻ/ አጠናው ዋሴ ለሞት ያበቃው ማን ይሆን? የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ነው። እና ሌሎችንም እስር ላይ እያሉ ያለፉትን የኛዎችን ሁሉ በምልሰት እንቃኛቸው የነፃነት ቃናና ቅኝት ናቸውና – ለእኛ፤
የዛሬ 70 ዓመት በናዚ ሂትለር ማንፌስቶ ወደ 26 ሚሊዮን ሰብዕዊ ፍጡራን አልፈዋል። የተደፈሩ ታዳጊ ወጣት ሴቶች፤ በራህብ ያለቁ ሰብዕዊ ፍጡራን፤ የፈረሰውን ማህበራዊ የህዝብ መገልገያ ሳይጨምር ስንት ዕንባ ከደም ጋር እንደ ወንዝ ፈሰሰ። ውቅያኖሶች፤ ወንዞች፣ ተራሮች፣ መሬት – ተቃጠሉ ነደዱ። ይህን አድራጊው አውሮፓን የናጠው የናዚ ወልጋዳ ማንፌስቶ ነበር። ዛሬ ከዛ ተላቆ አውሮፓ የሚሊዮኖች መጠለያ ለመሆን ችሏል። የተከፈለው መስዋዕትነት ካሳው በብልጫ ማዬት እንድንችል የሚያስገድደን ሁኔታም ይሄው ነው። በአንፃራዊ ያሉ ችግሮችን እረፍት ሰጥተን ሁለንትናዊ ፊቱን ስትመለከቱት በወቅቱ የነበሩ ዬኃያላን መንግሥታት መሪዎች ለማንፌስቶው ሳቢያ ሳይሆን ምክንያት በሆነው በቫተውና በተወጠረው የትምክህት ጉዳይ ላይ በትጋትና በተከታታይነት በቅንጅት ተባብረው፤ የተደራጀ ተግባር በመከወናቸው ነበር ለድል መብቃት ብቻ ሳይሆን ናዚዝምን የማከኑት።
ሰዎች ይፈጠራሉ። ሲፈጠሩ አቀባበል የሚያደርግላቸው የማህበረሰባቸው ወይንም የአስተዳደጋቸው መልካምና መልካም ያልሆኑ፤ አሉታዊና አዎንታዊ ጉዳዮች ናቸው። ለምሳሌ ዕውቅና ካለው ቤተሰብ የሚፈጠር አንደ ልጅ አቀባበል የሚያደርግለት ዕውቅና ክብር ዝና ነው። አስተዳደጉም በዕውቅና ሞራልና ሥነምግባር ፈክቶ ነው። ወላጅ አልባ ሆነው መንገድ ላይ የሚያድጉ ልጆች ዕድል አግኝተው ከፍ ካለ ደረጃ ቢደርሱ አብዛኞቹ ያን የተነሱበትን የበታችነት ስሜት መካስ የሚችሉት፤ ከልክ በላይ በሆነ በተንጠራራ መንፈስ ሊሆን ይችላል። ሌላው ቀርቶ ከመልካም ቤተስብ የሚያድጉ ልጆች ሲያድጉም ያንኑ ይከተላሉ። ለትዳራቸው ሆነ ለልጆቻቸው እንደ ወላጆቻቸው ጥንቁቁና አብነታዊ ይሆናል መንገዳቸው ሆነ አያያዛቸው። ልጆች ከሚሰሙት ይልቅ ለሚያዩት ቅድሚያ ይሰጣሉና።
ምን ለማለት ነው በጭካኔ፤ በአረመኔነት፤ በሰቅጣጭና ዘግናኝ የሰብዕዊ መብት ረገጣ የሚበቅሉ ሰዎችም ከመወለዳቸው በፊት አይደለም ይህን ጥቁር ጨላማዊ ሰብዕና ለብሰው የሚወለዱት፤ አቀባበል ከሚደርጋቸው አዎንታዊ ወይንም አሉታዊ ሁኔታዎች ይሆናል። እነሱ ፈለጉትም አልፈለጉትም አመዛኙ እጅ ወዳለበት ያመዝኑና ወይ የጥፋት ወይ የልማት መለያ ይሆናሉ።
ኖሮውይ ውስጥ Anders Behring Breivik, የሚባል ወጣት ጀርመን ውስጥ Andreas Lubitz: Co-pilot ዬሚባል ወጣት ያቀኑት ወደ ረግረጉ ነው። የተከተሉት መንገድ የፈርዖንን፤ የሄሮድስን፤ የአዶልፍ ሂትለርንና የሞሰሎኒ …. ነው። በመንፈሳቸው ያለው ሰሌዳ መግደል ራዕዩ ነበር። በመግድል መታወቅ የተሳሳተ ህልም ነበራቸው። ሰው የተፈጠረው ለመኖርና ትውልድን ለመተካት ነው። እነሱ ደግሞ ከዚህ ወጥተው ወይንም ይህንን ዘለው እነሱን እራሳቸውን ተፈጥሯቸውን ሳይተረጉሙት ተፃረው ሞትን መርጠዋል። የተሳሳተ፣ ግድፈትን ያዘለ ራዕይና የግል ኑሯቸው ግጭቱን ያሰከኑት በሰው ልጆች ኢ – ፍትሃዊ ዕልቂት ነው። አንዱ አጥፍቶ ጠፍቷል ሌላው እስር ላይ ነው። እነኝህ ሁለት የ21ኛው ምዕተ ዓመት ወጣቶችና መሰሎቻቸው የጠፉ ናቸው – ከሰው ተፈጥሮ ሥነ – አመክንዮ።
የእኛም ዕጣ ፈንታ ይሄው ነው። ከዓለም ውጪ አይደለንምና፤ የኢትዮጵያ መሬት ሄሮድስ መለሰን የመሰለ የበታችነት መስኖ አበቀለ። አጋጣሚውን ሲያገኝ የበታችነቱ ተወጠረ። በትዕቢት በጭካኔ በባላይነትና በገዥነት በጨቋኝ ጭካኔያዊ መንፈስ ማንፌስቶው ተቀነባበረ። የእኛ ዬዛሬው መከራ የሚሠፈረው እጅግም የሚዘገንነው በፖሊሲ ደረጃ፣ አቅም ባለው ኃይል የሚከውን በመሆኑ፤ የጥፋቱ ልክ ሥር ሰደድና ነቀርሳውም ሁሉንም ዓይነት መልካም ነገሮች አይምሬነቱ ህጋዊ ዕውቅና ያለው ከመሆኑ ላይ ነው።
አንድ ቆንጆ ቢላ ቤት በሚገባ አጽድታችሁ፤ አቧራውን በአጉሊ መነጸር ተቆጣጥራችሁ፤ እናም የጸዳ መሆኑን አረጋግጣችሁ ሰው አልባ ለአንድ ወር ዘግታችሁ ብትከፍቱት አቧራ ለብሶ ታገኙታላችሁ። ከዬት መጣ ይህ አዲስ – ገብ አቧራ? እኔ አቅም የለኝም ውዶቼ ሂዱበት ….
ዛሬ በሁለገብ ፈተና ችግር ምጥ የምትናጣው እናት ምድር ሆነች ዬልጆቿ ፍዳና መከራም ከሁለንትናዊው አካባቢያዊና ጭብጣዊ ሁኔታ ያፈነገጠ ሊሆን አይችልም። መፍትሄው በሽፋኑ ላይ ሳይሆን በገማው እንቁላል ወይንም ቀጣይ ጥቅም ሊሰጥ በማይችለው ዬእንቁላል አስኳል መሆን አለበት ባይ ነኝ። ስለምን? የታላቁን ሰው ተፈጥሮና ሥጦታዎች ተፃራሪ ስለሆነ። ለእኔ አንድ መምህር ለተማሪዎቹ የፈለግኽውን ውሰድ ብሎ ቢያስተምር መወስን ያልቻለ በግል ክብር እግርብረት የታሠረ በመሆኑ አይደለም ለመሪነት ለጉርብትናም አይታጫም። የማስተማር መቅኖውም የአልዛይመር ቁራኛ ስለሆነ። ዳኛም ቢሆን የመወሰን አቅሙን ‚ሀ‘ንም ‚ለ‘ንም ያሻችሁትን ቢል ችሎቱ ይከረቸማል። ጎሳና ጦሱ ይሄው ነው።
እና ምን አዲስ ነገር አለው? ከወያኔ ምህረት ብንጠብቅ የማይከፋ ቢሆንም፤ እሰከ አሁን በሳለፈው ከሰልማ ዕድሜው መማር መቻል ግን ያለብን ይመስለኛል። ጉዳዩ „የረባ መረጃ የማግኘትና ያለማግኘት ጉዳይ አይደለም – ዘረፈው። እእ! ነገን መመስጠር በመቻል ድህነት – ምህረት – ፍሰኃና – ሰናይ እቅም ነው። ተፈሪን በእጁ ያሰገባ ድርጀት በቀላል ድርድር መፍትሄ ይሰጠዋል ብሎ ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም። ሌሎችም ተዛማጅ የሆኑ ፈጣሪ ብቻ የሚያውቀው ጉዳይም አለበት። ለማንኛውም ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ አስተዳደር ማደረግ በሚችለው ሁሉ ሰብዕናውን አሳስቶ፤ አባዝቶ ወደሚፈልገው አቅጣጫ መሸኘት ትልሙ ነው። መቋረጥ ያለባቸው ተስፋዎች ሁሉ ድልድያቸውን መስመበር የወያኔ ሃርነት ትግራይ የሰለጠነበት ነው።
ለዚህም ነው ነገም በጠቆረ ወይንም በበቀል በተቋጠረ ዕራይ አንዳንጓዝ አንድ ቦታ ላይ የዜጎች መከራ ማቆም ስላለበት፤ ከግብታዊነት ሆነ ከቁርሾ ጭንጋፋዊ ዕይታ ወጥቶ የሰውን ተፈጥሮ በአግባቡ በመመርመር፤ በማዳመጥ የተፈጠረበትን መሰረታዊ አምክንዮ በቂ ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ የሚሆነው። ሰሞኑን አንድ አሰቃቂ ግድያ እዚህ ሲዊዝ ተፈጥሯል። ጋዜጠኛው ዜናውን ሲጨርስ „በዚህ መልክ ሰው መሞት ከዚህ ሥፍራ የተለመደ ነው“ ብሎ ነበር። ይህን የተለመደ ነገር ለማስቆም እያደገ እንዳይሄድ ለማድረግ፤ ወደ ባህል ወደ መሆን ደረጃም እንዳይዘልቅ በማደረግ እረገድ ከሥሩ ለመንቀል ምን መደረግ አለበት? ለሚለው ግን እንደ ጋዜጠኛ፤ ጋዜጠኛው አልጠቆመም … እንደገናም ሞት በግፍ በቤት ውስጥ በባሩድ እጅግ አሰቃቂ ሆኖ ተፈጽሞ ሳለ አቀራረቡ ከመንፈሱ አልነበር ከሰው፤ ከውስጤ ነበር ያዘንኩት … ዓለም ተሸፈነች ወይንስ በአንዳች ነገር ተጠቀለለች ልበል ይሆን?
አሉታዊ ነገሮች መንገድ መሪዎች ናቸው። አሉታዊ ስለሆኑ ብቻ ተጠቅልለው ቆሻሻ ውስጥ መጣል የለባቸውም። ተመራማሪዎች ጎጅ ቫይረስ ይሁን ሌላ ባክተሪያ አፈጣጠሩን ብቻ ሳይሆን የበቃውን ያህል አድጎ የሚያስከትለውን የጉዳት መጠን መለካት ይችሉ ዘንድ ነው የምርምር ተቋማት የተገነቡት። እርግጥ ሙከራው በጥንቸል ወይንም በአይጥ ወይንም ብቻውን ቫይረሱን ካለምንም ተጽዕኖ እንዳሻው እንዲሰፋ እንዲያድግ አድርገው ሊሆን ይችላል። የሰው ልጅም ፈተናዎች ጋር ቁጭ ብሎ ፈተናዎቹን እንደ እራሱ አድርጎ በመመልከት መፍትሄውን ከህሊናው ጋር ተጨንቆ ተጠቦ ማፍለቅ አለበት። ዓለም የተዘጋችበት ታላቁ ነገር ይህ ነው። ለሁሉ ነገር እድገት የኛይቱ ዓለም ሥልጣኔ ላይ ናት። ግን እንዲህ የሰው ልጅ በመርዝና በግፍ በሚሰቃይበት መሠረታዊ ጉዳይ ላይ እርምጃዋ የዓሊ አይነት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ስለ ሁለንትናዊ የችግሮች መነሻና መደረሻ ከፖለቲካ ጋር ብቻ ሆኗል – ድርድሩ። ዓለም ካለሰው ልጅ ድንብር ናት። የተፈጠረችው ለሰው አገልግሎት ሆኖ ሰውን እዬበላች አለች።
ለማንኛውም የከፋውን ነገር አስቦ መንፈስን ማሰናዳት ከብዙ ነገር ይታደጋል። ከሁሉ በላይ ትጥቅ ፈቺነትን ይታደጋል። የተከበሩ ፕ/አስራት ወልደዬስ በህክምና ሙያቸው እጃቸው የቅድስና ያህል መድህን ስለነበረው፤ የሁሉም በሽተኛ ህልም በእሳቸው ብሩክ እጅ መዳሰስን ይመኝ ነበር። ነገር ግን ከዚህ የፋፋና የህዝብ ፍቅር እጅግ ወደ ለማበት የገቡት ‚ሰው‘ የሚለውን ትርጉም ከንባብ አልፈው አቡጊዳንም የዳዊትንም ትርጉም ሰክነውበት ወደ ላቀው የሥነ ተፈጥሮን ረቂቅ ጸጋ ማመሳጠርን መንፈስ ቅዱስ ስላደላቸው፤ የሚሊዮኖችን ልብ በፍቅር ሥጋቸው አፈር ሆኖም እንሆ ይገዛናል። ገደል ለበላቸው፤ ጭካኔ ለቆረጠማቸው ሲሉ እራሳቸውን ሰጡ።
የተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ይበቃኛልን የተማሩት ለእኔ ከቅዱሱ፤ ከሰማዕቱ፤ ከሀዋርያው ከመምህሩ ከሰማዕቱ አባታችን ከቅዱስ ጳውሎስ ሲሆን ቃሉ እንዲህ ይላል ….“ ማሰብስ፡ ታስቡ፡ ነበር። ይህን፡ ስል፡ ስለ፡ ጕድለት፡ አልልም፤ የምኖርበት፡ ኑሮ፡ ይበቃኛል፡ ማለትን፡ ተምሬያለሁና። መዋረድንም፡ አውቀዋለሁ፣ መብዛትንም፡ አውቀዋለሁ፤ በእያንዳንዱ፡ ነገር በነገርም፡ ሁሉ፡ መጥገብንና፡ መራብንም፡ መብዛትንና፡ መጕደልን፡ ተምሬያለሁ። ኃይልን፡ በሚሰጠኝ፡ በክርስቶስ፡ ሁሉን፡ እችለዋለሁ“ /ወደ ቈላስይ ሰዎች አንደኛይቱ መልዕክት ምዕራፍ 4 ከቁጥር 11 እስከ 13/
መከራ ለመቀበል፤ ሞትን የደፈረ መንፈስ ሁልጊዜም ህያው ነው። ትናንትም ነገም ወደፊትም የራዕይ መንገድና የመግባቢያ ቋንቋ ነው ልፍጡራን ክብር ላላቸው የሰው ልጆች ሁሉ። ለእኔ አሁንም የተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የመንፈስ ቋንቋዬ፤ ሽልማቴና ጀግናዬ ናቸው። የማይሞት መንፈስ አይሞትም። ስለምን መንገድ መሪነቱ ዘለዓለማዊ ነውና ….
ክውና የአያያዝ ጥበብ ለተጠቀለለበት ወይንም ለሚያቀልጥ ወይንም ለጣለ ሥጦታን መንፈግ ወይንም ተከፍተው የነበሩ ልቦችን ከደን ማደረግ ትርፍ ነው። ከብዙ ነገር ይታደጋል። ይሆናል መስሎት የኢትዮጵያ ህዝብ ለታላቋ ትግራይ ዕራይ አብሮ 24 ዓመት ታከተ፤ መንገድም መራ፤ ደከመ ፍቅርን ሰጠ፤ ከቀን አደረሰ፤ ልጆቹን አበረከተ። ነገር ግን ጎጥና ጥላቻ፤ ጎሰኝነትና ትምክህት፤ መንደርተኝነትና ቋሳ ደምና ሥጋ በመሆናቸው ከቁጥር በላይ የሆኑ መከራዎችንና ፍዳዎችን መፈተኛ ሆኖ ወገን። ሁሉንም ችሎ አስተናገደ። ዛሬስ? ግንቦት ለወያኔ ሳቅና ፈንድሻ መርጫ – ለወያኔ ሃርነት የጎጥ እስር ዳግሚያ ትንሳኤ ውድ መንፈሱንና ህሊናውን አሳልፎ ይሰጥ ይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ – መከራን ለማሽሞንሞን ድምፁን ለጎጥ ማንፌስቶ ይሸልም ይሆን?
እኔ እህታችሁ ሁለመናዬን ሰጥቼ አያያዝ የማያውቅ ማናቸውም ግንኙነት ከገጠመኝ የተከፈተው ልቤ ካለ ቀነ ቀጠሮ ይዘጋል። የንክኪ መስመሩ ሁሉ ይቋረጣል። ፈጽሞ የመርፌ ቀዳዳ ታክል መግቢያ ክፍተት አይኖርም። አልመለስበትም – ፈጽሞ። ሰላምና – ጸጥታ፤ ደህንነትና ሐሤት በገፍ ለጻዕዳው መንፈሴ ይሸመትበታል። መወሰንና መቁረጥ ያልቻለች ነፍስ ነቅዛ ትኖራለች፤ ብታልፍ እንኳን ብትን የላትም …. ለነበርን መሸቢያ ጊዜ ናፍቆትን በፍቅር ሸልሜ መልካም ጊዜ ተመኘሁ። ደህና ሁኑሉኝ የእኔዎቹ።
ምርቃት
Tsegaye Radio or www.tsegaye.ethio.info Aktuelle Sendung በርካታ ፈተናዎች ጋር ፍልሚያው ቢቀጥልም፤ ነገር ግን ከሚዚያ ወር መጨረሻ ጀምሮ ራዲዮ ፕሮግራሙ በአዲሱ ስትዲዮ የመጀመሪያውን አዬር ላይ አውሏል። በሚዚያ ወር ማለትም 23.04.2015 ቀጣዩንም 07.05.2015 አቅርቧል። እርግጥ አዲስ ስቱዲዮ ጋር እስኪለማመዱ ትንሽም ውስብስብ ያሉ ቴክኒኮች አሉበትና ግድፈቶ ሊኖሩበት ስለሚችሉ ይቅርታችሁን – ይጠይቃል። … አሁን እንደ ድሮው አርኬቡ ላይ ረጅም ጊዜ ፕሮግራሙ ሊኖር ስለማይችል፤ በወር ሁለት ጊዜ ዕለተ ሃሙስ ከ15 እስከ 16 ሰዓት የተለመደ የወግ ገበታውን በዘንካታ ትህትና ኑልኝ አድምጡኝ ይላል – ክብረቶቹን። እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ቀጣዩ ዬአዬር ላይ ዝግጅት ግንቦት 21.2015 ይሆናል።
የሰማዕታት ረድኤትና በረከት አይለዬን፤ አሜን!
ከበቀል የጸዳ ልቦና አምላካችን ይስጠን – ሰውን የመተርጎም ምራቁን የዋጠ አቅልም፤ አሜን!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
Source: Zehabesha

No comments: