ደራሲ፡– ሮማን ፕሮቻዝካ
ትርጉም፡– ደበበ እሸቱ
አሳታሚ፡– ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት
ቦታና ዘመን፡- ሎስ አንጀለስ፣ መጋቢት 2007
ዋጋ፡– 10 ዶላር
ባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ ለሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ የኦስትሪያ ቆንስላ ውስጥ ተመድቦ ሠርቷል፡፡ ከአዲስ አበባ የወጣው ከዲፕሎማት ሥራውና መብቱ ጋር የሚፃረር ተግባር ሲያከናውን በመገኘቱ በ1926 ዓም ተባርሮ ነው፡፡ ፕሮቻዝካ Abyssinia the Powder Barrel” በሚል ርእስ በ1927 ቪየና ላይ አውሮፓውያን ትዮጵያን ሊወርሩና ሊይዙ የሚገባበትን ምክንያት የሚያቀርብ መጽሐፍ አሳተመ፡፡ መጽሐፉ ABISSINIA PERICOLO NERO (አቢሲንያ፡- ጥቁሯ አደጋ/ሥጋት) በሚል ርእስ የጣልያን ወረራ ከመጀመሩ አንድ ዓመት በፊት በ1927 ዓም በጣልያንኛ ተተርጉሞ ወጣ፡፡ ጣልያን ሀገሪቱን በወረረበት በ1928 ዓም ከወረራው ትንሽ ወራት ቀደም ብሎ በዋና ዋና የአውሮፓ ቋንቋዎች ተተርጉሞ እየታተመ ተሠራጭቶ ነበር፡፡
ፕሮቻዝካ ኢትዮጵያን አምርሮ የሚጠላ መሆኑን በጽሑፉ ሁሉ ይገልጠዋል፡፡ ነጮችን የሚጠሉ ሕዝቦች ያሉባት፣ የነጮች ክብርና መብት የማይጠበቅባት፣ ሥልጣኔ ያልጎበኛት፣ ብሔረሰቦች የሚጨቆኑባት፣ ጽዳት የሌለባት፣ አረመኔነት የነገሠባት፣ እምነቷ ከጥንቆላ ጋር የተቀላቀለ፣ ዜጎቿ ዓይናቸውን ጨፍነው ፎቶ የሚነሡ፣ መኳንንቱ ባዶ እግራቸውን የሚሄዱ፣ አንድነት የሌላት ሀገር መሆኗን ማስረጃ የሚለውን ሁሉ እየጠቀሰ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ ‹ኢትዮጵያውያን ጠላትን ለመመከት አንድ ናቸው› የሚለውን ሕዝቡ አያምንበትም ይላል፡፡ በንጉሡ የንግሥና በዓል የአውሮፓ መሪዎች ተወካዮች መገኘታቸው እጅግ ራስን ማዋረድና ክብር የማይጋባቸውን ጥቁሮች ከፍ ማድረግ ነው ይላል፡፡
የአድዋ ጦርነት ድል ነጮችን እንዲንቁ እንዳደረጋቸው፣ ነጮች ምኒሊክን በማባበላቸው የተነሣ በሌላ ሀገር ያገኙትን መብት እንዳጡ፣ ስለ ሀገሪቱ በአውሮፓ ቋንቋዎችና ጋዜጦች መልካም ነገር የጻፉት ሁሉ አንድም ገንዘብ ተከፍሏቸው፣ አለያም ደግሞ ለንግዳቸው ሲሉ መሆኑን ያትታል፡፡
ሀገሪቱን ለማስተካከል ሦስት መፍትሔዎችን ያቀርባል፡፡ አገሪቱን የሚገዟትን ጥቂት አማራዎች ማስወገድ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ነገዶች በዘር፣ በቋንቋ፣ በባህል ከኢትዮጵያ ገዥዎች ጋር ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲሰጣቸው (‹እስካሁን ቢሰጣቸው ኖሮ ኢትዮጵያዊነትን አውጥተው ይጥሉት ነበር፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ግን ከአውሮፓውያን ተሰሚነትና ተራማጅ አስተሳሰብ አራርቀው (አማራ ገዥዎች) በተዕጽኖ እየገዟቸው ነው› ይላል)፣ ኢትዮጵያውያን አውሮፓውያን ታላላቅ ሕዝቦች ናቸው ብለው እንዲቀበሉ ቅኝ መግዛትና ማሠልጠን፡፡ ‹ክርስቲያን ያልሆኑት ሕዝቦች በነጻነት ድምጽ ስጡ ቢባሉ በአውሮፓውያን ሥር መሆንን የሚመርጡ ናቸው› ሲል ያስቀምጣል፡፡ ሀገሪቱ መገጣጠሚያዋ የላላ ነው፣ አንድነቷ እንደታሰበው አይደለም ባይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር ጀምራው የነበረው ግንኙነት አውሮፓውያንን በእስያውያን የመተካት ሂደት ነው፡፡ እንደዚያ ከሆነ ደግሞ አውሮፓውያን በኢትዮጵያ ቦታ አይኖራቸውም ይላል፡፡ ጃፓናውያኑ ጥጥና አደንዛዥ ዕጽ እንዲያመርቱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ይኼ ደግሞ የዓለም መንግሥታት ማኅበርን ደንብ ይጻረራል በማለት ይከሳል፡፡
የሮማን ፕሮቻዝካን መጽሐፍ ስታነቡ ሀገሪቱ እንዴት ባለ ጥርስ ውስጥ የገባች ሀገር እንደሆነች ታያላችሁ፡፡ ኢትዮጵያን አምርረው የሚጠሉ ሰዎችን አስተሳሰብና ሀገሪቱን የማዳከሚያ ስልትም ታገኙበታላችሁ፡፡ ከ80 ዓመት በኋላ ዛሬ ላይ ሆናችሁ መጽሐፉን ስታነቡት አንዳንድ ሁኔታዎች የዛሬ እንጂ የጥንት አይመስሉም፡፡ ስለ ሀገራችን በጎ እንጂ ክፉ ለማንወድ ሰዎችም ጽሑፉ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አስደንጋጭም ነው፡፡
ደበበ እሸቱ እኤአ በ1935 የታተመውን የእንግሊዝኛውን ቅጅ ወደ አማርኛ ሲመልሰው አመላለሱ ትርጉም እንዳይመስል የሚያደርግ ነው፡፡ ደበበ መጽሐፉን የተረጎመው ሁኔታው ጠልቆ ተሰምቶት እንጂ ነገሩን ተረድቶት ብቻ እንዳልሆነ ያሳያል፡፡ በዚህ በ54 ገጽ መጽሐፍ ውስጥ የምታዩት ጉድ ከመጽሐፉ ገጽ በላይ ነው፡፡ ሲያጠቃልልም ‹‹አፍሪካ አንድ አህጉር ነው፤ በዚህ ታላቅ አህጉር ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች የአውሮፓ ታላላቆች ከሌሎች ሕዝቦች ያላቸውን ቀዳሚነት ማረጋገጥ አለባቸው››
አንቡና ጉድ በሉ፡፡
አሌክሳንደርያ፣ ቨርጅንያ
Source:: Danielkibret
No comments:
Post a Comment