Sunday, May 10, 2015

ኢትዮጵያዊ ማንነታችን የሚፈተንበት ቁጥር ፩ (እጅግ አስቸኳይ በደንብ በጥሞና እስከመጨረሻው ድረስ መነበብን የሚፈልግ ታሪክ)


zemedkun 1
የቤተክርስቲያን ታሪክ ተመራማሪውና የማከብረው ለእርሱም የተለየ ቦታ የምሰጠው ወንድሜ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትና የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ በሊብያ ስለተሰዋ አንድ ኢትዮጵያዊ ወንድማችን ጉዳይ ሰሞኑን ጽፈው አንብቤ ነበር ።
ይህ ሰው 2 የሚያማምሩ ልጆቹን ትቶ ማለፉንም እነዳኒ በጽሑፋቸው ጠቅሰውታል ። እውነት ለመናገር ሌሎቹ የሰማዕታት ቤተሰቦች ጋር እንደሄድኩት ሁሉ እዚህም ለመሄድ ኃሳቡ የነበረኝ ቢሆንም የግል ስንፍናዬም ተጨምሮ ጥቂት እረፍት አጥቼም ስለነበር ለሜሄድ ከማሰብ በቀር አልተሳካልኝም ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከልጆቼ ጋር በሰማዕታቱ ጉዳይ ስናወራ ልጆቼ የዚህ ሟች ከሌሎቹ ይልቅ በጣም የሚያሳዝን እንደሆነ ደጋግመው ይነግሩኛል ። እኔም የሁሉም ሰማዕታት ክብር አንድ እነደሆነ ፣ ሁሉም ቢሆኑ በግፍ መገደላቸው አሳዛኝ እነደሆነ ብነግራቸውም ለምን በዚህኛው ኢትዮጵያዊ አሟሟት ላይ በተለየ ሁኔታ ልባቸው እንደተነካ ግን በውስጤ ተረድቻቸዋለሁ ። ምክንያት አድርጌም ያየሁት ደግሞ የሟችን ህፃናት ልጆች ፎቶ በማየታቸው እንደሆነና ከእንግዲህ እነዚህ ህፃናት አባት የላቸውም በሚል በውስጣቸው የተፈጠረባቸው የሐዘን ስሜት እንደሆነም ገምቻለሁ ።
በእንዲህ አይነት ሁኔታ ላይ ስንፍ ብዬ በተቀመጥኩ ሰዓት ላይ ግን የሚያነቃ ሰው አገኘሁ። በአካል የማላውቃት “መስቱ” የምትባል በአረቢያ ምድር የምትኖር እህት እያለቀሰች እባክህ ከተቻለህ ሂድና ህፃናቱን እያቸው ፣ ለምንድነው መንግሥትም ህዝቡም የማይጠይቃቸው ብላ እያለቀሰች የድምጽ መልእክት በ what’s up አስቀመጠችልኝና ለመሄድ ወሰንኩ ።
ውድ ጓደኞቼ እስቲ አብረን ወደ አዋሬ እንሂድ ። ኑ በዓይነ ህሊናችሁም ተከተሉኝ ።
አድራሻውን ለማግኘት ብዙም አልተቸገርኩም ። ዲን ዳንኤል በማስታወሻው ላይ መሐመድ ካሳ የሚባል ልጅ ይረዳችኋል ብሎ ስልክ ቁጥሩን አስቀምጦ ስለነበር ከመሐመድ ካሣ የኃዘን ቤት አድራሻውን ተቀብዬ ከወንድሜ ከዘማሪ ዲ/ልዑልሰገድ ጌታቸው/ቋንቋዬ ነሽ/ ጋር ወደ ኃዘኑ ቤት ሄድን ።
የሟች ባለቤት በቅርቡ የባለቤቷን ሞት የተረዳች ቢሆንም እኔና ሉሌ በደረስን ሰዓት ግን 11 ሰዎችን ብቻ ነው በኃዘኑ ቤት ለማስተዛዘን ኃዘን ተቀምጠው ያገኘናቸው ። በየትም ቦታ ሰውን መርዳት መለያቸው የሆነው የቂርቆስ ሠፈር ልጆች ያመጡት የአበባ ጉንጉን እና የሟችን ፎቶ ከሚያሳይ ባነር በቀር እንደሌሎቹ ሟቾች የአበባና የኃዘን መግለጫ ምልክቶችም በሥፍራው አይታዩም ። ይህም ሟችን አለማወቅ ሳይሆን የሆነ ነገር እንዳለ እንድጠረጥር አደረገኝ ። ምክንያቱም ሌሎቹ አደጋው የደረሰባቸው ሰዎች ቤት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ እስላም ክርስቲያን ሳይል በአካል በመገኘት ጭምር ሲያጽኗኗቸው እንደነበር ተመልክተናል ።
አርቲስት ዮሴፍ ገብሬ /ጆሲም/ ከአዲስ አበባ ጎንደር ከጎንደር ትግራይ ከትግራይ ወልቂጤ እየዞረ ያዘኑትን ሲያረጋጋም አይቻለሁ እዚህ ግን ማንም ድርሽ አላለም ። ጆሲ እዚህም እንደሚሄድና ታሪክ እንደሚሠራ ተስፋ አደርጋለሁ ። ጋዜጠኞች ፣ አርቲስቶች ፣ ፖለቲከኞች ፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ አንዳቸውም ድርሽ አላሉም ። ይህ የሆነበት ምክንያቱ ምንድነው ? ይህ ሟች ኢትዮጵያዊ አይደለም እንዴ ? ባይሆንስ ሰው እኮ ነው ሰው ። ዜናው በደንብ አልተሰራም እንዳንል በደንብ ተሰርቷል ። ያውም እንዲያውም በራዲዮ ፋና ፣ በኢቲቪ ና በኅትመት ሚድያዎች ሁሉ ተነግሯል ። ከዚህ በተጨማሪም ብዙ አንባቢያን ባለው በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ብሎግ እና በብዙ የፌስቡክ ጸሐፍያን ዜናው ተሰራጭቷል ። እንዲህም ሆኖም ግን ጠያቂ የለም ።
ባለቤቱ “ብርቱካን ጌቱ ትባላለች ” ሰሜን ሸዋ ሸኖ አካባቢ ነው የትውልድ ሀገሯ ። በስፍራው በደረስኩ ጊዜ ኩርምት ብላ በተሰበረ መንፈስ አንገቷን ደፍታ ተቀምጣለች ። ስለእውነት ማርያምን እላችኋለሁ ኃዘን ድቅቅ አድርጓታል ። ከአብራኳ ሁለት የሚያማምሩ ልጆችን ከሟች ባለቤቷ አፍርታለች ።
ብርቱኳን ህፃን ኢየሩስ ብርሃኑ የተባለች የ8 ዓመት ቆንጅዬ ሴት ልጅና ህፃን ዮናታን ብርሃኑ አሁን የ4 ዓመቱ ላይ የሚገኝ ከፊታችን በሚመጣው ነሐሴ 24 የተክለሃይማኖት ዕለት 5ተኛ ዓመት የልደት በዓሉን ለማክበር በዝግጅት ላይ የሚገኝ የሚያምር ወንድ ልጆች እናት ናት ። በዚህ ደግሞ እድለኛም ናት ። ምክንያቱም እስካሁን ባለኝ መረጃ መሰረት በግፍ ከተሰውት ውስጥ ዘር ተክቶ ያለፈው አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ብቻ ነው ። ህፃናቱ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ወዲያ ወዲህ እያሉ በዚያች ጠባብ ግቢ ውስጥ መቦረቃቸውን ቀጥለዋል ።
እኔም ተገብቶኝ ሳይሆን ከመጣሁ አይቀር በማለት ለማጽናናት ያህል ጥቂት የእግዚአብሔር ቃል መናገር ስጀምር የሟች ቆንጅዬ የምታምረዋ ሕፃን ኢየሩስ ቆሎ ይዛ መጥታ ልቅሶ ለመድረስ የመጡትን ሁሉ እየዞረች በፈገግታ ታዘግናለች ። ትንሹ ወንዱ ልጅ ዮናታን ግን ካለበት ሮጦ በመምጣት ከላዬ ላይ ተለጠፈ ። እኔም እቅፍ በማድረግ በኃዘን ስሜት ውስጥ ብሆንም እንደምንም ብዬ ማጽናናቱን ቀጠልኩና በግድ የማጽናኛ ቃሉን ፈፀምኩ ።
በወቅቱ የህጻኑ ሁኔታ ሌሎችን ቢያስለቅስም እኔ ግን በሀሳቤ ስንት ቦታ ሄድኩ መሰላችሁ ። ስለእውነት እኔ ብሆንስ ብዬ ልጆቼ እንዳሰቡት አሰብኩ ። በመጨረሻም የሟችን ባለቤት ብርቱካንን እና ታናሽ እህቷን ወደ ተከራየችው መኖሪያ ቤት በምትመስል ትንሽዬ ቤት ገብተን ብዙ ተወያየን ። በውይይታችን መኃልም ሟችን ለምን ብዙ ሰው ኃዘኑን እንደማይደርሰውም አሁን ፍንጭ አገኘሁ ። የሚገርም ነው ። በጣም ያሳዝናልም ።
ሟች በሃይማኖቱ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነው ። ይሄ ደግሞ መብቱ ነው ። ሚስት ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ። ፍቅር አንድ ላይ አብሮ 12 ዓመት ያህል ያኖራቸው ። የሚያኖራቸው ፣ በዚህም ምክንያት ያልተለያዩና በአብሮነታቸውም ሁለት የሚያማምሩ ሕጻናት ልጆችን ያፈሩ ናቸው ። እነዚህ ህፃናት ምንም እንኳን አባታቸው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ቢሆንም ወላጅ አባት ሟች አቶ ብርሃኑ ጌትነት የእናትየውን የወይዘሮ ብርቱኳንን መብት ሳይጋፋ ፍላጎቷን ጠብቆላት በባለቤቱ ወ/ሮ ብርቱኳን የእምነት ሥርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀኖና መሠረት በመንበረ መንግሥት/ ግቢ / ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሴቷን በ80 ወንዱን በ40 ቀኑ ክርስትና አስነስታ ሰርተፍኬታቸውን በእጇ የያዘች እናት ናት ።
የሚያሳዝነው የቀበሌው ሴቶች ማኅበር እንግዳ ቢመጣ ብለው የቆሎ መግዣ ከሰጧትና ባለቤቷ ከሚከታተልበት የሃይማኖት ተቋም ከተሰጣት አነስተኛ ገንዘብ በቀር ማንም ዞር ብሎ አላያትም ።
የሚገርመው ሟችን ከባለቤቱና ከእህቷ ጋር በመጫወት እየቆየሁ ስመጣ በተለይ እህቷን የማውቅበት ቦታ ጠፋብኝ እንጂ የምንተዋወቅ እንደሚመስለኝ ስነግራት ” ሟች እኮ ደንበኛህ ነው ። የሚሠራቸውን ጥቅሶች እያስረከበህ ትሸጥለት ነበር ። እኔንም የምታውቀኝ አንዳንዴ እሱ ባልተመቸው ጊዜ ጥቅሶችን አመጣልህ ስለነበር ነው ብላ ስትነግረኝ ጊዜ የባሰ ደነገጥኩ ፣ አዘንኩም ።
birhanu getaneh
እውነት ነው “ብርሃኑ” ብዙ ሺህ በእንጨት ላይ የተቀረፁ ግሩም የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለ ” ጌልገላ መዝሙር “ቤቴ ያስረክበኝ ነበር ። እኔም እነዚያን ጥቅሶች ሽጬያቸዋለሁ ። ምናልባትም ይህን ጽሑፍ እያነበባችሁ ያላችሁ በኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ የምትኖሩ ሰዎች በቤታችንም ሆነ በሥራ ቦታችን ተንጠልጥሎ የሚገኘው ጥቅስ የብርሃኑ የእጅሥራ ውጤት ሊሆን ይችላል ።
ይህ ኑሮ ነው እንግዲህ ከእጅ ወደ አፍ ለመሆን እንኳን አላደርሰው ቢለው ነው ብርሃኑ እነዚህን እንቦቀቅላና የሚያማምሩ ፍቅር የሆኑ ህፃናት ልጆቹን እና ወድ ባለቤቱን ሜዳ ላይ በትኖ የተሻለ ኑሮ ይኖሩ ዘንድ በማሰብ በሕይወቱ ተወራርዶ ስደትን የመረጠው ። ወንድማችን አውሮፓን በማሰብ ወደ ሊቢያ ሄዶ በዚያም በአራጆች እጅ ወድቆ እጁን የኋሊት ታስሮ ርኅራሄ በሌላቸው ጨካኞች አናቱ በጥይት ፈራርሶ ነው በሊብያ በበረሃ የቀረው ።
ብርሃኑ ይህ ይመጣል ብሎ ባለማሰቡ ቢያንስ ከ3 ወር በኋላ አውሮፓ ስገባ የተሻለ ገንዘብ እልካለሁ በማለት የ3 ወር የቤት ኪራይ ከፍሎላቸው ነበር የሄደው ። እንዳሰበው ሳይሆንለት ቀረ እንጂ ።
ይህን በሰማን ጊዜም እኔና ልዑልሰገድም ወሰንን ። ብናጣ ብናጣ ለምነንም እንኳን ቢሆን እኒህን አባታቸውን በግፈኞች የተነጠቁ ሕጻናት ለማስተማር ባንችል ዩኒፎርማቸውን እና ለበዓል የሚሆን ልብስ መግዛት አያቅተንም በማለት የሚቻለንን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል ገብተን ተመለስን ።
ልዑልሰገድ /ቋንቋዬነሽ/ እንዲህ አላቸው ” እኔ ሞቼ አበቃልህ ተብሎ እንዲያውም አንዳንዶች ” ቀብረነው እኮ መጣን ” ብለው እስኪናገሩ ድረስ በሰው ዘንድ የተፈረደብኝ ሰው ነበርኩ ። ለእኔ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይሉ ሁሉም ተረባርቦልኝ በጸሎታቸውም አግዘውኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጭምር ነፃ የአየር ትኬት ሰጥቶኝ ይኸው ታክሜ በእግዚአብሔር ቸርነት በድንግል ማርያም አማላጅነት በእናንተ ሁሉ ልቅሶና እንባ ድኜ እድሜ ሰጥቶኝ እዚህ ደርሻለሁ ። ቋሚ የሆነ ገቢ ባይኖረኝም ከማገኘው ላይ ለጊዜው አንድ ሺህ ብር እሰጣለሁ ። ለወደፊቱ ግን ዘመድኩን እንዳለው ለህፃናቱ ቢያንስ እኔና ዘመድኩን የተቻለንን እናደርጋለን በማለት ቃል የገባውን ዛሬ ፈጽሟል ።
ከሁሉም በላይ በእነ ያሬድ ሹመቴ አሳሳቢነት አዋሬ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃዘኑ ቤት ድረስ በመሄድ ራሳቸው የባንኩ ሠራተኞች በሟች ሚስት ስም አካውንት ከመክፈትም አልፈው በባንክ ሂሳቧ ላይ 600 ብር ጨምረው አስረክበዋታል ። ታዲያ የእኔ ልጆች ማኅተመ ዘመድኩን እና ማርያማዊት ዘመድኩን በስማቸው የሰጡት 1000 ብርና ዘማሪ ልዑልሰገድ የሰጠው 1000 ብር ሲደመር ከአሁኑ 2600 ብር ሆነላቸው ማለትም አይደል ። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን እና ይህን መልእክቴን ማንበብ ሳትፈልጉ በግድ ያነበባችሁ ብትሆንም ኢትዮጵያዊ የሆናችሁ በሙሉ ። እግዚአብሔር በረከቱን የሰጣችሁ በሰጣችሁ መጠን በብዙ ፣ ምንም በቂ የሆነ ገቢ የሌላችሁ በጥቂቱ ፣ ብትሰጡና የየአቅማችንን ከ10 ብር ጀምሮ ብናዋጣ በእርግጠኝነት የተሳካ ሥራን ሠርተን የልጆቹን ሕይወት በመለወጥ እግረመንገዳችንንም የጽድቅ ሥራን ሠራምን ማለት ነው ።
※※※ማሳሰቢያ ለአንዳንድ የፌስቡክ ጸሐፍት※※※
እንደሚታወቀው በሊብያ በረሃ ውስጥ በአሸባሪው ISIS አማካኝነት አንገታቸውን ተቀልተው ስለታረዱትና በጥይት ተረሽንው ስለሞቱት ሰዎች ማንነት በጻፍንበት አንቀጽ ላይ ከኦርቶዶክሳውያን በቀር ሌላ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ወገኖች አልሞቱም ብለን ሽንጣችንን ገትረን ስንሟገት እንደነበር ይታወሳል ። ዋቢ ያደረጋችሁትም ራሱን ISIS የተናገረውን ሰምተን ነው ብላችሁ ነበር ። ማርያምን ነው የምላችሁ እኔ በበኩሌ ISIS የተናገረውን አላምነውም ። ደግሞም መብቴ ነው ። ካልጠፋ መረጃ አሸባሪ የተናገረውን የማመን ግዴታ የለብኝም ። ISIS እንደሁ የተበቀለ የመሰለው ኢትዮጵያን ነው ። የተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞችንም እንዲሁ ። ነገር ግን እንዲያም ብለን የተሟገትን ቢሆንም እንኳ ነገር ግን አስካሁን የሟቾ ማንነት ገና በጥቂቱ ነው እየታወቀ ያለው ። የሟቾቹ ዜግነትም ቢሆን ይኸው ቀስ በቀስ እየታየና እየተለየም ነው ። እንዲያውም አብዛኛውን ቁጥር እየያዙ የመጡት ወንድሞቻችን ኤርትራውያን መሆናቸውም እየታየ ነው ።
እናም እኔ በበኩሌ ሙሉው ሰማዕታት ኢትዮጵያውያን ፣ ሃይማኖታቸውም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ብቻ ናቸው ብዬ አልደመድምም ። በደንብ ማንነታቸው ተጣርቶ የመጨረሻውን ይፋዊ ውጤት እስክናገኝ ድረስ ረጋ እንበል የምለውም ለዚህ ነው ። አንዳንዶቻችን ግድያው ሲፈጸም ስምዝርዝር የሰጠን እና በቦታው የነበርን እስኪመስል ድረስ ከኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ውጪ የሌላ እምነት ተከታይ የሆነ ማንም አልሞተም እያልን የምንለውን ጽንፍ የያዘና ከሃይማኖተኛ ሰዎች የማይጠበቅ ድርጊት ከመፈጸምም ብንቆጠብ መልካም ነው ።
ቅዱስ ሲኖዶሳችንም በዚህ ላይ ያሳየውን ጥንቃቄ በግል ሳላደንቅ አላልፍም ። በአሁኑ የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔም ላይ እነዚህን የሊቢያውን ሰማዕታት ” ሰማዕት ” እንዲባሉ መወሰኑ ተነገሯል ። ደስ የሚል ዜናም ነው ። እኒህን ብቻ ሳይሆን እንዲያውም በ1999 ዓም በጅማ በሻሻ በሰማዕትነት ያለፉትን ወገኖቻችንም ጨምሮ የሰማዕትነት ማዕረግ ይሰጣቸዋል ብዬም እጠብቃለሁ ።
ለሁሉም ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ማንነታቸውን ለይቶ የክብር ማዕረጉን ለመስጠት ለጥቅምቱ የሲኖዶስ ጉባዔ አሸጋግሮታል ። እውነት ነው በቀኖና ቤተክርስቲያን መሠረት አስፈላጊውን መረጃ መሰብሰቡ የግድ ስለሆነ እንዲህ ማድረጉ አግባብም ነው ። የሞቱት ሰዎች ቢሆንም ቤተክርስቲያናችን በቀኖናዋ መሠረት ” ሰማዕት ” ብላ ሰይማቸዋለች ። ነገር ግን የቅድስናውንና የክብራቸውን ነገር የምታውጀው ግን ቀኖና ቤተክርስቲያን በሚያዘው መሠረት መስፈርቱን ያሟሉትን ብቻ ነው ።
ለዚህም እስከ ጥቅምት 2008 ዓም ድረስ ተጣርተው እንዲቀርቡ ብዙ አማራጮች ቀርበዋል ። ውይይት ተደርጎም ሰማዕታቱን የሚመጥናቸውን መልካም የሆነ ዜና እንሰማለን ። ሴኖዶሳችን ።
፩ኛ፦ ” ወበዛቲ ዕለት ” ተብሎ ዜናቸው በሚያዝያው ስንክሳር ላይ ተጽፈው የሚታሰቡ ፣
፪ኛ፦ በሰማዕታቱ ስም ቤተ ጸሎት በማነጽ የሚታሰቡ
፫ኛ፦ገድላቸውን በመጽሐፍ መልክ በማጻፍ የሚታሰቡ
፬ኛ፦ ምን አይነት ሃይማኖታዊ ግኑኝነት እንዳለው ባላውቅም የሃውልት ጉዳይም ተነስቷል ።
ይህን ለማድረግ ደግሞ ቤተክርስቲያን የልጆቹን ሙሉ የዓለም ስማቸውን ከነ ክርስትና ስማቸው ፣ የልጆቹን በወቅቱ ያሳዩትን የእምነት ተጋድሎ የመሳሰሉት ነገሮች በሙሉ በተሟላ መልኩ ተደራጅተው ተጽፈው ይቀርባሉ ። ቅዱስ ሲኖዶሳችን የግብጾቹን ሰማዕታት የግብጽ ኦርቶዶክስ ብሎ የተቀበለ ሲሆን የኢትዮጵያን ግን የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ብሎ ነው የተቀበለው ። ምክንያቱም እንዲህ አይነት ተጋድሎ በተፈፀመ ጊዜ የሰማዕትነትን ክብር ሰጥተው ፣ ገድላቸውንም ጽፈው ለትውልድ የማቆየት ታሪክ ያላቸው አምስቱ ጥንታውያኑ የኦረንትያል አብያተክርስቲያናት ብቻ ስለሆኑ ነው ። ይህም ማለት እንዲህ አይነት ባህልም ሆነ ስርአት በሌሎች ዘንድ አይታወቅም ማለት ነው ። ከሟቾቹ ውስጥ ከላይ የጠቀስናቸውን ሃይማኖታዊ ስርዓቶችን ከመፈጸም ማሟላት ግድ ነው ።
አሁን እኒህን የሟች ልጆችን እንርዳ ። እናቋቁም ። እኛ ጀምረናል እናነተ ደግሞ ቀጥሉ ። ውጤቱን በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እናየዋለን ። የዛሬው 2600 ብር እመቤቴ ምስክሬ ናት ማርያምን ነው የምላችሁ ተትረፍርፎ ባናየው ምን አለ በሉኝ ።
ጅማ እያለሁ ለኮሄ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን ከመንበር ጀምሮ አብዛኛውን ንዋያተ ቅዱሳት እችላለሁ ያለችኝ እህቴ አሁንም ልጆቹ ጋር ይዘኸኝ ሂድ ብላኛለች ። ምን እንደሚከሰት አላውቅም ። ደስ ሲል ሐብት ከክርስትና ጋር ሲስማማ ። አረ እንደው የእኔ እህት ለአንቺ ወለተ አማኑኤልና ለባለቤትሽ ፍቅረ ሥላሴ እንዲያው ልዑል እግዚአብሔር ጨምሮ ጨማምሮ እድሜውን ፣ ሀብቱንና ጤናውን ይስጣችሁ ። አሜን ።
ማን ነበር ” ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻውን በቂ ነው ” ያለው ? ጀምሩ እንግዲህ ።
ቤተክርስቲያንም ኃላፊነቷን ትወጣ ። በመንፈስቅዱስ የወለደቻቸውን ልጆቿን ትከታተል ። ህጻናቱ አሁንም ኦርቶዶክሳውያን ናቸው ። ባለቤቱም ብርቱኳንም እንዲሁ ።
ኃሣቡን ያፈለቀው እስካሁን በአካል የማላውቀው በስልክ ብቻ የማውቀው ወንድማችን መሐመድ ካሳ ነው ። እኔም የመሐመድን ሐሳብ በመደገፍና በማጠናከር እንዲሁ እላለሁ ።
ማኅበረ ቅዱሳን ልጆቹን በማስተማር በኩል ያውም በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤት እስከ መጨረሻው ኃላፊነት ብትወስዱ ። ምክንያቱም ካሁኑ በልጆቹ ላይ ሌሎች ሽሚያ የመጀመር አዝማሚያ እየታየ ስለሆነ ብዬ ነው ። እስካሁንም የእናትየው የእምነት ጥንካሬ ይዞ ነው እንጂ ችግር አለ ። ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራል አይደል የሚባለው ። እናም መፍጠን ነው ።
ይህች የልጆች እናት አሁን በተከራየችበት ቤት እንኳን እንግዶችን በደንብ እና በአግባቡ ለማስተናገድ አልቻለችም ። ትናንት የልደታ ሰንበት ትምህርት ቤት ሰንበት ተማሪዎች አንዲት ጠቦት አርደን የማጽናኛ መርሐግብር እንፈጽም ቢሉ አከራዩ ከኢትዮጵያዊነት ባህል ባፈነገጠ መልኩ አይደረግም ብሎ ሁሉን ማሳዘኑ አግባብም አይደለም ። የግድ ፕሮቴስታንት መሆን አለባት እንዴ ? ተው እንጂ ጎበዝ ። የከፋ ነገር ከመጣ ቤት እስክታገኝ እኔ እራሴ ቤቴን እለቅላታለሁ እንጂ የምን ማቨማቀቅ ነው ። እማምላክ ምስክሬ ናት ደግሞም ቤቴ አሳምሮ ይበቃናል ። ፓስተሮቹ መጥተው ሲዘምሩ ፣ ሲጸልዩም ፣ ማንም አልተቃወመም ። ምክንያቱም ሟች ሃይማኖቱ ስለሆነ መብታቸው ነው ። ኦርቶዶክሳውያኑ ሲመጡ የምን ማኩረፍና ያዙኝ ልቀቁኝ ነው ። እሷ የባሏን መብት ጠብቃ እናንተ እንፀልይ ስትሉ ሳትቃወም በክብር ተቀብላ እንደሸኘቻችሁ እናንተም የልጅቷን መብት አክብሩላት እንጂ ። መሐመድ ካሣ እኮ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው እንዲህ በዚህ ጉዳይ መከራውን የሚበላው ኢትዮጵያዊነቱ አስገድዶት እኮ ነው ። ተው እንጂ እንዲህ አይነት ኢትዮጵያዊ ባህል የለንም ።
እዚያው በቅርብ ያላችሁ አገልጋይ ካህናትና መምህራን ይህች እናት ቤት አግኝታ እስክትወጣ ድረስ አፅናኗት ። ልጆቿን ጎብኙ ። በተለይ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርት ፣ የግቢ ገብርኤል ፣ የበአታ ማርያም ፣ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራልና የቀበና መድኃኔዓለም ሰንበት ተማሪዎች ምን ትጠብቃለችሁ ። እዚያው ከስራችሁ የተቀመጠችን እህት አጽናኗት እንጂ አይዞሽም በሏት ። እባካችሁ ሂዱና ዘምሩ ። “ማርያም ኃዘነ ልቡና ታቀልል” ብላችሁ ዘምሩ ። ዘምሩ እውነቴን ነው ። ዘማሪ ዲያቆን ልዑልሰገድ ዛሬ ብሩንም ሰጥቶ የደረገው እንዲሁ ነው ። ዘምሮ አፅናንቶ ፣ ነው የወጣው ።
እንደተለመደው ይህ ጽሑፍ ብዙ ሰዎች እንዲያዩት Share መደረግን ይፈልጋል ። በጉዳዩ ዙሪያ ተሳትፎ እያደረግህ ያለኸውና በእምነት ባትመስለንም በኢትዮጵያዊነትህ መልካሙን ሁሉ በማድረግ ላይ ያለኸው ወንድማችን መሐመድ ካሣ ፣ በሥነ ጽሑፋችሁ ችግራቸውን ለዓለም ሕዝብ ያሳወቃችሁ ዲን ዳንኤል ክብረትና ያሬድ ሹመቴን ሳላመሰግን አላልፍም ።
ይኸኛውን ጽሑፌን ቁጥር ፩ም አይደል ያልኩት ። ቁጥር ፪ ጽሑፌንም ይከተላል ። እንዲሁ ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ ፣ ነገር ግን በሚያምነው እምነቱና በንጹሕ ኢትዮጵያዊነቱ ብቻ በግፍ ስለተሰዋ ሌላ ኢትዮጵያዊ አሳዛኝ ታሪክ ይዤላችሁ እቀርባለሁ ። በጣም አሳዛኝ ጉዳይም አለውና ጠብቁኝ ።
ቁጥር 3 ም አለኝ በግፍ የተገደለ ሌላውን አሳዛኝና ተደብቆ እንዳይቀር የምፈልገው እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ተጠርቼ ከዘማሪ ዲን ልዑል ሰገድ ጋር በመሄድ ስናለቅስ ውለን ስለመጣንበት ታሪክም ደግሞ በቀጣይ ይዤላችሁ እቀርባለሁ ። እስከዚያው ሰላም ሁኑልኝ ጓደኞቼ ። አሜን በቸር ያቆየን ።
★★★ እነሆ የባንክ ሂሳብ ቁጥሩ ★★★
ወ/ሮ ብርቱካን ጌቱ ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
አዋሬ ቅርንጫፍ የባንክ ሂሳብ ቁጥር
1000126433108
+251911608054 የእጅ ስልኬ ነው ። ማንኛውንም አስተያየት ለመቀበል ፈቃደኛ ነኝ ። አክባሪ ወንድማችሁ ።
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ሚያዝያ 30/8/2007 ዓም
አዲስ አበባ — ኢትዮጵያ

Source: Zehabesha

No comments: