የኦሮሚያና የደቡብ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ለፓርላማ ይወዳደራሉ
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ በዕጩነት ያቀረበው 60 በመቶ በፓርላማ አባልነት ላይ የሚገኙ ተወካዮቹን ነው፡፡ ተወካዮቹ ለምርጫ ቅስቀሳና ሪፖርት ለማድረግ ወደየምርጫ ወረዳዎቻቸው በመሄዳቸውም፣ ፓርላማው ለሁለት ሳምንት መደበኛ ስብሰባውን ሳያካሂድ ቀርቷል፡፡
ፓርላማው መደበኛ ስብሰባውን ዘወትር ማክሰኞና ሐሙስ እንደሚያካሂድ የፓርላማው የሥነ ምግባርና የመተዳደሪያ ደንብ ይደነግጋል፡፡ በአንዳንድ አስቸጋሪ ምክንያቶች መደበኛ ስብሰባዎች ወደ ሌላ ጊዜ ሊተላለፍ እንደሚችልም በፓርላማው የውስጥ አሠራር ይታወቃል፡፡ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ 60 በመቶ የሚሆኑት የምክር ቤቱ አባላት ለአሥር ቀናት በድጋሚ በሚወዳደሩባቸው ወረዳዎች ቅስቀሳ ለማድረግና በየተወከሉባቸው የምርጫ ክልሎች ያለፉት አራት ዓመት ተኩል የሥራ አፈጻጸማቸውን ሪፖርት ለማድረግ በመሰማራታቸው፣ መደበኛ ስብሰባዎች መሰረዛቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡትም፣ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ በሚወዳደሩበት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ኢተያ የምርጫ ክልል ቅስቀሳ ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡
ሪፖርተር ባገኘው የዕጩ ተወዳዳሪዎች ዝርዝር መሠረት ትግራይ ክልል ካሉት 38 መቀመጫዎች ለሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አዲስ ዕጩ ሆነው የቀረቡት አሥር ብቻ ናቸው፡፡
ከአዲሶቹ ዕጩዎች መካከል ሪፖርተር ቀደም ሲል እንደዘገበው ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ወክለው በአደዋ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በአላማጣ፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር መብርሐቱ መለስ በአዲግራት ይወዳደራሉ፡፡
የአማራ ክልል በፓርላማው ውስጥ ካሉት 138 መቀመጫዎች ሁሉንም የያዘው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ለመጪው ምርጫ የሚያወዳድራቸው አዲስ ዕጩዎች 49 ብቻ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 89 ዕጩዎች ነባር የፓርላማ አባል ናቸው፡፡ ከአዲሶቹ የብአዴን ዕጩዎች መካከል ከሁለት ዓመት በፊት የፍትሕ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው አምባዬ በሰሜን ወሎ ዞን በደላንታ ምርጫ ክልል የሚወዳደሩ ሲሆን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ደግሞ በደሴ ከተማ ይወዳደራሉ፡፡
የደቡብ ክልል በፓርላማ ካለው 123 መቀመጫዎች ውስጥ ባለፈው ምርጫ 122 የሚሆኑትን ደሕዴን የያዘ ሲሆን፣ በዚህኛው ምርጫ 56 ነባር የፓርላማ አባላትን ሲያወዳድር 67ቱ ደግሞ አዲስ ዕጩዎች ናቸው፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ዕጩ ካደረጋቸው በርካታ ተወዳዳሪዎች መካከል ታዋቂዎቹ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤና በአሁኑ ወቅት የደቡብ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ታገሰ ጫፎ ይገኙበታል፡፡
በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል በፓርላማ ካለው 178 ወንበሮቹን ሁሉንም ኦሕዴድ የያዘ ሲሆን፣ ለመጪው ምርጫ 60 በመቶ የፓርላማው ነባር አባላቱን ያወዳድራል፡፡ ይህም ማለት 106 ነባር አባላት በድጋሚ የቀረቡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ አዲስ ዕጩዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ፋኩልቲ ምክትል ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ነገሪ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ቃቄ የምርጫ ክልል ይወዳደራሉ፡፡ የኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በሐረማያ፣ እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ደሚቱ ሐምቢሳ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን አይራ ጉሊሶ የምርጫ ክልል ተወዳዳሪ ናቸው፡፡
Source: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment