Saturday, May 2, 2015

ኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነትን ቀን እንዴት ታከብረዋለች?

(የትነበርክ ታደለ)
የአለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ቀን የፊታችን እሁድ በመላው አለም ይከበራል። በፕሬሱ ላይ የሚደርሰውን ጫናና በጋዜጠኞ ላይ የሚደርሰው ውክቢያ ይቆም ዘንድ የተባበሩት መንግስታት ይጠይቃል። በዚህ ረገድ እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ጉዳዩ የበልጥ ትኩረት የሚሰጠው ሀገር የለም።
ከዚህ ቀደም ከነበረው በከፋ ሁኔታ መንግስት በዚህ አመት በመገናኛ ብዙሀን ከፍተኛ ተጽእኖ አደርጓል። የአለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት ሲፒጄ (Committee to Protect Journalists) በተለያዩ መስፈርቶች ባወጣቸው የተለያዩ ሪፖርቶች ኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ከማይከበርባቸው ሀገሮች ቀዳሚዋ ሆናለች።
በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ቁጥራቸው ከሰላሳ የማያንሱ ጋዜጠኞች ሀገር ለቀው ተሰደዋል። ስምንት ያህል ጋዜጦችና መጽሄቶች ከህትመት እንዲወጡ ተደርገዋል። ጋዜጠኞችና የድህረ ገጽ ጸሀፊዎች ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል።
በዚህም ጋዜጠኞን ወደ ወህኒ በመወርወር ኢትዮጵያ በአለም ደረጃ አራተኛ በአፍሪካ ደግሞ ጎረቤትዋን ኤርትራን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃን እንደያዘች ሲፒጄ በሪፖርቱ ገልጿል። ይሄው ድርጅት በዚህ ሰሞን ይፋ ባደረገው ሌላ ሪፖርት (10 Most Censored countries) ነጻ ሀሳብን ከሚያፍኑ አስር ሀገራት መካከል እንዲሁ አራተኛና በአፍሪካም ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ መንግስት ግን ዛሬም የሚቀርብበትን ወቀሳ ሁሉ ከማጣጣሉም ባሻገር በሀገሪቱ ላይ የተሟላ የፕሬስ ነጻነት እንደሰፈነ በተደጋጋሚ በመግለጽ ላይ ይገኛል።
ከሁለት ሳምንት በሁዋላ ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አጀንዳቸውን ለህዝብ ለማስተዋወቅ በቂ የሚዲያ ሽፋን በማጣት ሲቸገሩ ታይተዋል። ከጅምሩ የህዝብ መገናኛ ብዙሀን የአየር ሰአት ክፍፍሉን ለገዥው ፓርቲ የአንበሳውን ድርሻ የሰጠው የምርጫ ቦርድ ይባስ ብሎ በዚያችም የአየር ሰአታቸው ላይ ለሚያቀርቡት ፕሮግራሞች ላይ የተለያዩ ሰበቦችን በመፍጠር በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ሲያደርግ ቆይቷል። የራሳቸው ቋሚ ሚዲያ መገንባት ያልቻሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አማራጭ የግል ሚዲያዎችን ለመጠቀም እንዳይችሉ ሆነው ሲቸገሩ ተስተውለዋል።
የሀገሪቱ ፕሬስ በዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ በወደቀበት ሰአት ሀገሪቱ ወደ ምርጫ በመንደርደር ላይ ትገኛለች። ነጻ ሚዲያ በሌለበት ደግሞ ነጻ ምርጫ ማካሄድ ፈጽሞ የሚቻል አይደለም። መራጩ ህዝብ ስለሚመርጠው ፓርቲ አቋምና አጀንዳ ተደራሽ በሆኑ የመገናኛ ብዙሀን በደንብ ሊነገረው ይገባል። ህዝቡ የተሟላ መረጃና ካርዱን ይዞ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ሊሄድ የሚገባው።
ለዚህ ነው ኢትዮጵያ የዚህን አመት የፕሬስ ነጻነት ቀን እንዴት ታከብረዋለች ስል የጠየኩት። ይህን መንግስትም ራሱን ሊጠይቅ ይገባል። እንደ ተለመደው ዛሬም ሀገራችን ዴሞክራሲ አብቦባታል ፕሬሱም እያደገና እየተመነደገ ነው የሚል ንግግሮች የሚሰማባቸው በትልልቅ ሆቴሎች የሚካሄዱ ኮንፈረንሶች መሬት ላይ ያለውን እውነታ አይቀይሩትም። እውነታ በቃላት ሊቀየር አይችልም።
ሀገሪቱ ቢያንስ ጎረቤት ሀገሮች የደረሱበትን የነጻ ሚዲያ ሁኔታ መቃኘትና ከዚያም ልትማር ይገባታል። ጋዜጠኞን ማሰርና ማሳደድ ወይም የተቃውሞ ሀሳብን ማፈን በፍጹም ወደ ፊት አንድ እርምጃ ሊወስደን የሚችል ድርጊት አይደለም።
የሀገሪቱ ልማትና እድገት ሀሳብን በነጻነት ከመግለጽ መብት ውጪ ተደርጎ ማየት የኔነት የማይሰማው ትውልድ ይፈጥራል፤ ይሀም መጨረሻው አፍራሽነት ነው። በመሆኑም የሚዲያ ነጻነት እንዲሁ ከልማት በሁዋላ ተብሎ ቀጠሮ የሚያዝለት ጉዳይ ሳይሆን አሁኑኑ ሊጠበቅ የሚገባው ህገ መንግስታዊ መብት በመሆኑ መንግስት ቆም ብሎ ድርጊቱን ሊያጤነው ይገባል።
Source: eastafricanupdate

No comments: