Saturday, May 9, 2015

“የፍትህ ማሽቆልቆል ጉዞ በኢትዮጵያ” ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም

“የፍትህ ማሽቆልቆል ጉዞ በኢትዮጵያ” ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም

“የፍትህ ማሽቆልቆል ጉዞ በኢትዮጵያ” ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም

<በየትኛውም ጥንታውያን አገሮች እንደነበረው ሁሉ በኢትዮጵያም በሕግ ከለላ የተሰጣቸው፣ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ በደል ያደረሱ እንደ ባሪያ ንግድና እንደ ባለርስትና ጭሰኛ የመሳሰሉ አጸያፊ ሥርዓቶችና ሕጋዊ ግንኙነቶች እንደነበሩ አይካድም። ይህም ሆኖ ግን ጥንታውያን ሕጎች፣ የኃይማኖት ድንጋጌዎችና ባህላዊ ሕጎች መኖርና በሥራ ላይ መዋል በጥቅሉ በሀገራችን ፍትሃዊነት በህዝብ አዕምሮ እንዲሰርጽ አድርገዋል። ህዝቡ ለሕግ ከበሬታ እንዲኖረውና ግፍና በደልን እንዲጠላ፣ በጠቅላላው ፍትሃዊነት እንደ አንድ ብርቅዬ ዕሴት እንዲቆጠር በህዝብ እምነት ውስጥ ተቀርጿል።
ህዝቡ ለሕግ ከፍተኛ ከበሬታ እንደነበረው የሚገልጹ አያሌ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ሁለት ባላጋራዎች መንገድ ላይ ቢገናኙ ተበደልኩ ባዩ ምንም ኃይል ሳይጠቀም “በሕግ አምላክ ቁም!” በማለት ብቻ ባላጋራውን አስቁሞ የነጠላዎቻቸውን ጫፍ ቋጥረው (ተቆራኝተው) ያለ ፖሊስ አጃቢ ወደ መረጡት ዳኛ ዘንድ ሄደው ፍርዳቸውን ይቀበሉ ነበር። ለዚህም ነው እስከዛሬ “በቆረጥከው ዱላ ብትመታ፣ በመረጥከው ዳኛ ብትረታ” እንዲቆጭህ አይገባም የሚባለው። “በሕግ አምላክ!” ሲባል ውሃ እንኳን ይቆማል ይባል ነበር።
በአገራችን የዳኝነት ሥራ በጣም የተከበረና ዳኞች የተለዩ ፍጡራን ሆነው ይታዩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የዳኝነት ሥራ እንደ መንፈሣዊ ተግባር ተቆጥሮ ከዳኛው ነፍስ ጋር ትስስር ነበረው። ፍርደ ገምድል ዳኛ በቀጥታ ወደ ገሃነም እንደሚወርድ ይታመን ነበር። ለዚህም ነው “ፍረድ ለነፍስህ፣ ብላ ለከርስህ” ይባል የነበረው። ስለዚህ ዳኞች በገንዘብ፣ በእጅ መንሻ እንዳይታለሉ ኅሊናቸውና ፈሪሃ እግዚአብሔርም ይገድባቸው ነበር። ጉቦና እጅ መንሻ ቢቀበሉም እንደ ዛሬው የባለጉዳይ ቆዳን ገፍፎ በአንድ ጀምበር ቱጃር የሚያደርግ ሳይሆን፤ ከአንድ ጉንዶ ማር ወይም ከአንድ ሽንጥ ጥሬ ሥጋና ጠርሙስ አረቄ የሚዘል አልነበረም።
ዛሬ በአገራችን የፍትህ ሥርዓቱ ተሰብሯል ማለት ይቻላል። ለሕግ የነበረው ከበሬታ እየተሸረሸረ፣ ሕጉ ነፃነቱን ተገፍፎ፣ በፖለቲካ ተቀፍድዶ ህዝቡ ለፍትህ ያለው እምነት እየተሟጠጠ ነው። የሕግ ከበሬታ እያሽቆለቆለ የመጣው በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት መገባደጃ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም። በሀገራችን ቀርቶ በአፍሪቃም ተወዳዳሪ የማይገኝለት የቀይ ሽብር “ነፃ እርምጃ” አካብቶት የነበረው ሕጋዊነትና የፍትሕ ዕሴት ከህዝቡ ኅሊና ጠራርጎ አወጣው። እመቤት ሕግ ዓይኗን የተሸፈነች፣ በአንድ እጇ ሚዛን፣ በሌላው ሰይፍ ያነገተች ሳትሆን፤ ዓይኗን ብልጥጥ አድርጋ እየመተረች፣ ሰይፉ አድሃርያንን መርጣ የምትቀላበት መሣሪያ ሆነ። ሰው ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ነው የሚለው ዓለማቀፋዊ መርኅ ተሽሮ ሕግ አንድን የኅብረተሰብ ክፍል (መደብ) መመንጠርያ መሆኑ በገሃድ ተሰበከ፣ በሥራ ላይም ዋለ። ከጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ ጊዜ አንስቶ ደም የሚገበርለት ዛር ውላጅ ያለ ይመስል በዚች ሀገር ያለ ፍርድ በፈረቃ፣ በየጎዳናዎች የፈሰሰው የንጹኀን ደም ቤቱ ይቁጠረው። አንዲት ከአሜሪካ ለእረፍት ሀገርዋ የመጣች ኢትዮጵያዊት ስልክ ደውለው ‘ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ርካሽ ነገር አለ?’ ብለው ቢጠይቋት ‘ርካሽ ነገር ቢኖር የሰው ሕይወት ብቻ ነው’ ማለቷ በራሱ ብዙ ይናገራል።

No comments: