Monday, May 4, 2015

የኢህአዴግ ከፍተኛ ካድሬዎች በድርጅታቸው ግራ ተጋብተዋል

ሚያዝያ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ የተገደሉትን ኢትዮጵያውያንን ለመዘከር የወጣው ህዝብ ተቃውሞውን ወደ ኢህአዴግ መንግስት ካዞረ በሁዋላ፣ ገዢው ፓርቲ ተቃውሞውን ያስነሳው በአገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ
የሚታገለው ሰማያዊ ፓርቲ ነው በማለት የከፈተው ሰፊና አሰልቺ ፕሮፖጋንዳ የህዝቡን አመለካከት ሊቀይር አለመቻሉ ከፍተኛ ካድሬዎችን ስጋት ላይ ጥሎአቸዋል፡፡
በመስቀል አደባባይ የታየውን ህዝባዊ ቁጣ ሰማያዊ ፓርቲ የቀሰቀሰው የመንደር ሁከት ለማስመሰል በስሩ በሚገኙ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ፕሮፖጋንዳ የሰራ ቢሆንም ፣ ፕሮፓጋንዳው ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን የራሱን አባሎች ማሳመን አለመቻሉ ከፍተኛ
ካድሬዎችን ድንጋጤ ላይ ጥሎአቸዋል።
በአዲስአበባ አስተዳደር በተለያዩ የመንግስት ቢሮዎች ይህንኑ የሕዝብ ተቃውሞ በማስመልከት ሰማያዊ ፓርቲ ያቀነባበረው መሆኑን በመግለጽ ሁኔታውን ለማውገዝ ታስቦ ሰሞኑን ተከታታይ ስብሰባዎች የተካሄዱ ቢሆንም አጥጋቢ ውጤት ሊገኝባቸው አልቻለም፡፡
በተለይ የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ጭምር ፍረጃው አሳማኝ አለመሆኑን በመጥቀስ ሕዝቡ በተለይ በመልካም አስተዳደርና በኑሮ ውድነት ችግሮች ውስጥ ሆኖ መቃወሙ የሚጠበቅ እንደነበር፣ ከሰማያዊ ፓርቲ ይልቅ ወደውስጣችን በመመልከት ችግሩን ካልቀረፍን
ከዚህም የባሰ ችግር ሊገጥመን ይችላል በሚል የተንጸባረቁ ደፈር ያሉ አስተያየቶች ያልተጠበቁ በመሆናቸው የመድረክ መሪ ካድሬዎችን ጭምር አስደንግጦአል፡፡
አንድ የሰብሰባው ተካፋይ “በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ አንድ በወር 3 ሺህ ብር የሚያገኝ መካከለኛ ገቢ ያለው የሚባል ደመወዝተኛ ቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት፣ የቤተሰብ ቀለብና የመሳሰሉ ወጪዎችን መሸፈን ጨርሶ አይችልም፡፡ አነስተኛ ወርሃዊ ገቢ ያለው ሰፊ
የህብረተሰብ ክፍል ከሞቱት በላይ ፣ከቆሙት በታች ሆኖ የሰቆቃ ኑሮ እየገፋ በመሆኑ ተቃውሞ ሲያንሰው ነው” ሲሉ ለዘጋቢያችን ገልጸውለታል፡፡ በአንጻሩ ግን ቤት መኪናና የተሻለ ገቢ ያላቸው ሹማምንት ከደሃውን ጉሮሮ እየነጠቁ በሙስና የሚከብሩበት ስርኣት
መፈጠሩ ግልጽ ሆኖአል ሲሉ አክለዋል።
ኢህአዴግ በተለያዩ መዋቅሮቹ ሰማያዊ ፓርቲ ከግንቦት 7 ጋር በማበር ሁከት በመቀስቀስ ላይ ነው በሚል የተጠናከረ ፕሮፖጋንዳ ከሰራ በሃላ ያለችግር ፓርቲውን ከምርጫ ለማስወጣትና የተወሰኑ አመራሮችንም ለማሰር አቅዶ የነበረ መሆኑን የጠቀሰው ለጉዳዩ ቅርበት
ያለው ምንጫችን ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይህ ዕቅዱ እንዳሰበው በቀላሉ የሚሳካለት ባለመሆኑ ከፍተኛ ካድሬዎቹ በድንጋጤና በግራ መጋባት ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል ብሎአል።
በሌላ በኩል በግፍ የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን ለመዘከር የሻማ ማብራትና የጸሎት ስነስርአቶች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው። በደቡብ ኮሪያ ሴኡል ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያኞች ለሟቾች ሀዘናቸውን ገልጸው፣ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው በስልጣን ላይ ያለው ሃይል ነው ብለዋል። ኢትዮጵያኑ በፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ እድል በማጣታቸው መሰደዳቸውን የገለጹት ኢትዮጵያኑ ፣ ከዚህ ችግር የምንላቀቀው ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርአት ሲመሰረት ብቻ ነው ብለዋል።
በሻርሎቴ ኖርዝ ካሮላይና የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንም በተመሳሳይ ሻማ ማብራትና ጸሎት ስነስርአት በማድረግ የተገደሉትን ኢትዮጵያውያንን አስበዋል። ኮንግረስ ማን ሮበርት ፒተንገር እና የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች በስፍራው ተገኝተው መልእከቶችን አስተላልፈዋል።
Source: Esat

No comments: