Tuesday, May 5, 2015

"ሕይወት ሁለት ጃምቦ ከጠጣሁ በኋላ ያለችው ዓይነት ብትሆን ደስ ይለኛል "

አንድ ወዳጄ፣
"ሕይወት ሁለት ጃምቦ ከጠጣሁ በኋላ ያለችው ዓይነት ብትሆን ደስ ይለኛል " ይላል። ይህ ወዳጄ አለማየሁ ደንድር ይሆናል። ላይሆንም ይችላል። ስለሰከርኩ በደንብ ለይቼ ላላስታውሰው እችላለሁ።

ሰክሬያለሁ።
ስሰክር፣
ህገመንግስቱ የሚናድ የሚናድ አይመስለኝም፤ አሉ የተባሉ ግንበኞች ተሰባስበው ያደሱት ይመስለኛል። 
ስሰክር፣ ሽብር ሲሉ፣ "አብሽር " ያሉ ይመስለኛል።
ስሰክር፣
የፌደራል "ጥቁር " ቆመጥ፣ ከቀይ አበባ ይምታታብኛል። 

ባለጌ ወንበር ላይ ተቀምጦ የሚጠጣ አንድ ጠጪ ከፊት ለፊቴ ይታየኛል። የመጠጥ ቤት ወንበሮችን ማን ባለጌ ብሎ እንደሰየማቸው እንጃ! እቃወማለሁ። የወንበር ባለጌ ካለው፣ ባለጌ መባል ያለበት የቤተመንግስቱ ወንበር ነው። አሁን ሃይለማርያምን የመሰሉ የእግዜር ሰው እዚያ ወንበር ላይ ከተቀመጡ አልተበላሹም? ጨዋውን ሰው አላባለገም? ባለጌ ወንበር ያለው ቤተመንግስት እንጂ፣ መጠጥ ቤት አይደለም። 

በቤቷ ውስጥ አጫጭር ልብስ ለብሰው የጠጪውን ስሜት ለመቀስቀስ የሚሞክሩ ሴተኛ አዳሪዎች ይታያሉ። ስሰክር የሴተኛ አዳሪነት ስራ ከፓርቲዎች ስራ ይመሳሰለብኛል። 
ሁለቱም አጉል አለባበስ ለብሰው የሌላውን ስሜት ለማኖህለል የሚለፉ ናቸው። ሁለቱም ከመረጧቸው በኋላ ያስከፍላሉ። ይህ በስካር ዓለም የሚገለጥልኝ እውነት ነው።

ለምንድነው ግን የምጠጣው?
የምጠጣው፣ አንድ ሰካራም ወዳጄ እንደሚለው ከ "ጠ " ቀጥሎ "ጡ" ስላለ አይደለም። የምጠጣው ለመሰደድ ነው።
ብዙ ኢትዮጵያዊ በባህር አቋርጦ ተስፋ ወደጣለበት ሀገር ሲሰደድ፣ የእኔ አይነቱ በአልኮል ባህር ይሰደዳል (ከስደቱ ጠዋት ቢመለስም)
አክራሪ የጌታ ልጆች፣ በአልኮል ባህር መዘፈቅ ይሉታል።

በተሰደድኩበት ሀገር እቅፍ አበባ እንጂ ዱላ የያዘ ፌደራል ያለ ስለማይመስለኝ ያጫኝን እናገራለሁ። 

ይህንንም አምናለሁ፣
ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የመናገር ነፃነትን ያጎናፀፈው ህገመንግስቱ ሳይሆን አልኮል ነው። አልኮላዊ መብቴን ለማስጠበቅ እጠጣለሁ።

ከተቀመጥኩበት ለውሃ ሽንት ተነሳሁ። ሰውነቴ ሲንገዳገድ አለመስከሬን ላለማስታውቅ ተፍጨረጨርኩ። ሰካራም መስከሩ የሚታወቀው አልሰከርኩም ሲል አይደለም? ሀገርም እንዲያው ናት፣ መብራት በየቀኑ እያጠፋች፣ ውሃ ለወራት እያጠፋች፣ የራስ ደምፅ መልሶ የሚያሰማ ኔትወርክ እየታቀፈች፣ መሽቶ በነጋ ቁጥር እልፍ ስደተኛ እየሸኘች አድጌያለሁ ትላለች። ሰክራ አልሰከርኩም!

ሽንት ቤት ደርሼ ስመለስ፣ ወንበሬ ላይ ሌላ ሰው ተቀምጧል። ገረመኝ። በዚህ የወንበር ሽሚያ አውራ ፓርቲነት እንደምን ይታሰባል? ይሰማል አውራው ፓርቲ? 

ወጣሁ።
በመንገዴ ላይ እዚህም እዛም የተለጠፉ የቅስቀሳ ፓስተሮች ይታዩኛል።
"ለኗሪዎቿ ምች የሆነች አዲስ አበባን እንፈጥራለን " ይላል አንዱ። ስሰክር የሚነበበኝ የተፃፈው "ምቹ " ሳይሆን፣ እየሆነ ያለው "ምች " ነው። ሌሎችም ብዙ አስገራሚ ፖስተሮች። የፖስተርና የፓስተር ቃል አይዋጥልኝም። 

ወደ ሰፈሬ ስደርስ፣ 
"ወደ ምስራቅ ተመለከቱ" የሚለው ቅዳሴያዊ ቃል ትዝ ብሎኝ ወደ ምስራቅ አተኮርኩ። ምንም የንጋት ፀሐይ አይታይም። ዝም ተስፋ! ዜሮ ፀሐይ! የፀሐዩ መንግስት ምልክቶች እንጂ የፀሐይ ዳና በአካባቢው የለም!

Alemayehu Dendir

No comments: