Friday, May 8, 2015

ፖሊስ የፍ/ቤት ትዕዛዝን በመሻር የሰማያዊ አባላትን ዋስትና ከለከለ

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የካዛንቺስ 6ኛ ፖሊስ በእስር ላይ የሚገኙትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የፍርድ ቤት ትዕዛዝን በመሻር ዋስትና ከለከለ፡፡

ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ሊቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን የሽብር ድርጊት ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳትና በመሳተፍ›› ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የፓርቲው አባላት ዛሬ ሚያዝያ 30/2007 ዓ.ም ጠዋት በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርበው የ6000 ብር የሰው ዋስትና ተፈቅዶላቸው ነበር፡፡

በእነ ወይንሸት ሞላ የምርመራ መዝገብ የተካተቱ አምስት ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ዋስትና ከማግኘታቸው በፊት ፖሊስ ‹‹ምርመራየን አልጨረስኩም፣ ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢወጡ በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ይችላሉ›› እና ሌሎች ተደጋጋሚ ምክንያቶችን በማቅረብ ዋስትና እንዳይፈቀድ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ ከሀገር ሊወጡ ይችላሉ የሚለውን ምክንያት ባለመቀበል ከዋስትናው ጋር ለኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ተጠርጣሪዎቹ ከሀገር እንዳይወጡ የሚል ደብዳቤ እንዲጻፍ ትዕዛዝ በመስጠት የ6000 ብር ዋስ አቅርበው እንዲወጡ ሊፈቅድ ችሏል፡፡

በዚህ መሰረት የተጠርጣሪ ቤተሰቦች ዋስትናውን ጨርሰው ለማስፈታት በሄዱ ጊዜ ፖሊስ ‹‹ሰኞ ይግባኝ ብለን ፍርድ ቤት ስለምናቀርባቸው ሊፈቱ አይችሉም›› በሚል ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ተጠርጣሪዎቹ በእስር እንዲቆዩ አድርጓል፡፡
በእነ ወይንሸት የምርመራ መዝገብ የተካተቱት አምስት ሰዎች ወይንሸት ሞላ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ጸጋየ እና ማስተዋል ፈቃዱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ሲሆኑ፣ በዚሁ መዝገብ ላይ ፖሊስ የፓርቲው አባል እንደሆነች የሚገልጸው፣ እሷ ግን አባል አለመሆኗን የገለጸች ቤተልሄም አቃለወርቅም ትገኛለች፡፡

በነገረ ኢትዮጵያ

No comments: