Thursday, August 1, 2013

ደሴዎች የመንግስትን የጭካኔ በትር የተቀበሉበት እለት!

ደሴዎች የመንግስትን የጭካኔ በትር የተቀበሉበት እለት!

ይህን ቀን ከቶ እንደምን እንረሳዋለን?!

ባለፈው ዓመት 2004 ላይ ልክ በዚህ ወቅት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸመው በደል ጣራ የነካበት ወቅት ነበር፡፡ ልክ እንደአሁኑ ጊዜ እስር ድብደባ ግድያ ሙስሊሞች ላይ በርትቷል፡፡ የረመዳኑን የመጀሪያ እለት ጀምሮ መሪዎቻችን ወደ እስር ተሸኙ፣ በአንዋር መስጂድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በፖሊስ ታፍሰው ወደ ሰንዳፋ እና ዝዋይ ተጫኑ፡፡ ሙስሊሞች በዱላ ሰውነታቸው ደቀቀ፣ በውድቅት ለሊት ወህኒ የተጋዙት በእንብርክካቸው አሸዋ ላይ እንዲሄዱ ተገደዱ፣ ሴቶች ሂጃባቸው ተነጠቀ፣ ወንዶች ጺማቸው በጭካኔ ተነጨ፡፡ ይሄ ሁሉ የደረሰው በታጠቁ እና አመጽ ላይ በነበሩ ሙስሊሞች ላይ አልነበረም፡፡ ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› በሚል መፈክር በሰላማዊ መንገድ በሚጠይቁ ሙስሊሞች ላይ ነበር፡፡

የረመዳን የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት በዚህ መልኩ ሙስሊሞች በስቃይ በትር እየተመቱ፣ ወደ ወህኒ
እየተጋዙ ሲዘልቁ፤ መንግስትን ሕግ አንዲያከብር የሚጠይቁ ድምጾች ግን ተቀጣጥለው ከፍ ብለው ይሰሙ ነበር፡፡ በወቅቱ ሰላማዊ የተቃውሞ ድምጽ የማይሰማበት ክልል እና ከተማ አልነበረም ለማለት ይቸግራል፤ ግን እንዲያም ሆኖ መንግስት እነዚሁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ልክ አሁን እያደረገ እንዳለው የግዳጅ ሰልፍ እያስወጣ ‹‹አሸባሪዎችን እንታገላለን›› እያለ በሚዲያ ያስፎክር ነበር፡፡ ተቃውሞው ግን አልበረደም፡፡ ረመዳን ሁለተኛ ሳምንቱን አገባዶ ሶስተኛውን አጋመሰ፤ አሁንም ተቃውሞው ያለ እረፍት ኢትዮጵያን ከጫፍ እስከ ጫፍ እየናጣት ነው፡፡ ሶስተኛው ሳምንት አለቀና የአራተኛው ሳምንት መጀመሪያ እለት በደሴ ይህ ተከሰተ፡፡ ክስተቱ ትውልድም ሆነ ታሪክ የማይረሳው የግፍ የበደልና የጭካኔ ምሳሌ ነው፡፡ 22ኛው የረመዳን ቀን የጁምአ እለት ነው፡፡ የደሴ ሙሰሊሞች በማለዳ ነበር ወደ አረብ ገንዳ መስጂድ መትመም የጀመሩት፡፡ ጊዜው የአሸረል አዋኺር ነው፤ሕዝቡ ስለ ተገፈፈው መብት ከሌሎች ኢትዮጵያዊ የእምነት ወንድሞቹ ጋር ሆኖ ለመሟገት ወደ አረብ ገንዳ አመራ፡፡

የመንግስት ወታደሮችም ገና ከረፋዱ አረብ ገንዳና አካባቢውን ከበቡት፡፡ የሰው መምጣት ግን አላቆመም፡፡ በማስፋፊያ ስራ ላይ የነበረው የአረብ ገንዳ መስጂድ ገና የሰላት ሰአት ሳይደርስ ሞልቶ ሕዝቡ ወደ ውጭ መፍሰስ ጀመረ፡፡ የመስጂዱ በር፣ በረንዳ እያለ አካባቢው እየሞላ ሰዉ ውጭ ላይ ማንጠፍ እና ሱና ሰላቱን መስገድ ጀመረ፡፡ አንድ የፖሊስ አባል መጥቶ ግን ሰጋጆቹን ከቦታው እንዲነሱ መጠየቅ ጀመረ፡፡ ‹‹ለምንድን ነው ከመስጂድ ክልል አልፋችሁ የወጣችሁት?›› ብሎ ሙግት ጀመረ፡፡ ሙስሊሞቹ መስጂዱ በሰው መሙላቱንና ያላቸው አመራጭ ከመስጂዱ ውጪ በሆኑ ቦታዎች ላይ መስገድ መሆኑንና ይህ የተለመደ መሆኑን ቢያስረዱትም ሊሰማቸው አልፈቀደም፡፡ ይልቅ ፖሊሱ በተጠንቀቅ ይጠብቁት ለነበሩት አዣዦቹ በሬዲዮ መልእክት ሰደደላቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነውን ግን ለመንገርና ለማስታወስ የሚቸግር ሆነ፡፡ ከርቀት ሆነው ሲጠባበቁ የነበሩት ፌደራል ፖሊሶች መጥተው የደሴን ሙስሊም በያዙት ቆመጥ መደብደብ ጀመሩ፡፡ ሕዝቡ በድንጋጤ እንዲሸበር ጥይት ወደ ሰማይ ተከታትሎ ተተኮሰ፡፡ በመስጂዱ ውስጥም ውጪም ያሉት ሙስሊሞች ጭካኔ የተሞላበት የፌዴራል ፖሊሶች ሰደፍና ዱላ
ተደጋግሞ አረፈባቸው፡፡ ዋይታና እሪታ ነገሰ፡፡ ብዙዎች እንደዚያ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶባቸውም ጁምአን ሳይሰግዱ መመለስ አልፈለጉም ነበር፡፡

የአረብ ገንዳ ሙአዚን ባህረዲን የሙስሊሙ በአገሩ ያውም በመስጂዱ ውስጥ እንዲህ ያለው ዘግናኝ ድርጊትሲፈጸምበት በማየቱ በሐዘን በተሰበረ አንደበቱ እያለቀሰ ኢቃም አደረገ፡፡ በአረብ ገንዳ መስጂድ 30 ዓመታት ያሰገዱትና መንግስታዊውን ሃይማኖት አልቀበልም በማለታቸው ከቦታቸው በመንግስት የተነሱት ኢማም ሼኽ አደም ሙሳ ያለ ሩኩዕ በቁኑት ብቻ የታጀበውን ታሪካዊ የሀዘን ሰላት አሰገዱ፡፡ 

ሙሰሊሙ ሰላቱን ቢጨርስም አሁንም ወደቤቱ እንዳይመለስ በፌደራሎች ከበባ ስር ወደቀ፤ ያሻቸውን እያስወጡ ማሰሩንም ተያያዙት፡፡ ሰዐታት በዚያው ሁኔታ ቆይተው ውጥረቱ ሳይረግብ የአሱር ሰላት ደርሶ በሼኽ አደም ሙሳ ኢማምነት ተሰገደ፡፡ ከአሱር በኋላም እስሩ ተጧጡፎ ቀጠለ፡፡ የመንግስት ታጣቂዎች ያሻቸውን ያህል ሰው ከመስጂዱ እየወሰዱ ወደ መኪናችው መጫኑን ተያያዙት፡፡ በርካታ ሙሰሊም ወንድሞቻችንም ታሰሩ፡፡ ሴቶችም የእስሩና ድብደባው ሰለባ ነበሩ፡፡መንግስት ግን ከሕዝቡ አልፎ የስግደት ሪዎቹን ሙአዚኑን ባህረዲን እና አረጋዊውን ኢማም ሼኽ አደምን ወደ አስር ቤት አጋዟቸው፡፡

ሙአዚን ባህረዲን ስምንት ወራቶችን በእስርና በስቃይ አሳለፈ፡፡ ያውም ያለምንም ክስ፡፡በእስርም ላይ እያለ በደረሰበት ድብደባ እጁ ተሰበረ፡፡ እነ ሼኽ ሐሰን ሐሚዲንም የእስር ሰላባ ሆኑ፡፡ አረብ ገንዳና አካባቢው በጨለማ የተዋጡበት፤ ደሴ ከተማ በሐዘን ተመታችበት ያንን ወቅት ፈጽሞ አንረሳውም፡፡ አዎ! ፈጽሞ አንዘነጋውም፡፡

No comments: