Friday, May 6, 2016

ከገዢው ፓርቲ ደጋፊ ጋዜጦች መካከል አንደኛው በኪሳራና በድጎሟ እጦት ተዘጋ

ሚያዚያ ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፰ / ኢሳት ዜና :- ገዢው ፓርቲን የሚደግፉና በድጎማ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጋዜጦች በገበያ እጦትና በድጎማ መቀነስ እየተዘጉ ሲሆን፣ በዜድ ፕሬስና ማስታወቂያ ኤጀንሲ /የተ/የግ/ በመባል በሚታወቀው የአቶ ሳምሶን ማሞ ድርጅት አማካይነት በየሳምንቱ ቅዳሜ የሚታተመው «ኢትዮቻናል» ጋዜጣ በኪሳራ ምክንያት መዘጋቱን አሳታሚው እንደገለጸላቸው አንዳንድ ጋዜጠኞች ለኢሳት ተናግረዋል።
ኢትዮቻናል ጋዜጣ የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ ከሼክ አልአሙዲ ጋር መጋጨታቸውን ተከትሎ ከፍተውት የነበረውን ጸረ-አልአሙዲ ዘመቻ ለመከላከል ሲባል የሪፖርተር ጋዜጣን ዘገባ እየተከተለ ምላሽ እንዲሰጥ በሼክ አላሙዲ ወኪል በአቶ አብነት ገብረመስቀል ድጋፍ የተመሰረተ መሆኑንም የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
አቶ አማረ አረጋዊን በጠራራ ጸሐይ በመሀል ቦሌ ለመግደል የተደረገው ሙከራ መክሸፉ በርካታ ነባር የህወሃት ተጋዮችንእንዴት ተደፈርንበሚል አስቆጥቷቸው እንደነበር የሚገልጹት የቅርብ ምንጮች የታጋዮቹ ቁጣ በሼክ ሙሃመድ አላሙዲ ወገን ያሉትን ሰዎች ማስደንገጡን አስታውሰዋል፡፡
እነአቶ አብነት ከአቶ አማረ ጋር የገቡትን ፍጥጫ ለመተው በመገደዳቸው የአቶ ሳምሶም ማሞ የጋዜጣ ድጎማ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ከመጣ በሁዋላ ጨርሶ በመቋረጡ ከነገ ጀምሮ የኢትዮ ቻናል ሳምንታዊ ዕትም እንደማይኖር ታውቆአል፡፡
ኢትዮቻናል ጋዜጣ ገዥውን ፓርቲ በመደገፍ ላለፉት አምስት ኣመታት 2 ባልበለጠ አነስተኛ ዕትም ዘገባዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል።

No comments: